
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለያዩ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸው አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል። የፕሬዚዳንቱ ርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአክሲዮን ገበያዎች ድርሻ ቅናሽ እንዲያሳይ አድርጓል። ውሳኔን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገርና የንግድ ድርድር አድርገው ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥያቄ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረጉት የታሪፍ ዝርዝር ከፍተኛ ታሪፍ ከተጣለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ቻይና ናት። ትራምፕ ስለምጣኔ ሀብታዊም ሆኑ ስሌሎች ጉዳዮች ሲያወሩ ከአፋቸው የማይለዩዋትን ቻይናን እስካሁን የ54 በመቶ ታሪፍ ጥለውባታል። ከአንድ ወር ገደማ በፊት ከተጣለባት የ20 በመቶ ታሪፍ በተጨማሪ ምርቶቿ ባለፈው ሳምንት 34 በመቶ ታሪፍ ተጨምሮባቸዋል።
የትራምፕ የታሪፍ ሰለባ የሆነችው ቻይና የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ በፅኑ ያወገዘችው ገና በጠዋቱ ነው። ትራምፕ ከስድስት ሳምንታት በፊት አሜሪካ ከቻይና በምታስገባቸው ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንደምታደርግ ባሳወቁበት ወቅት ቻይና የአሜሪካን ድርጊት ኮንና ጉዳዩን ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት እንደምትወስደው ገልፃ እንደነበር ይታወሳል። መላው ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው በነበረውና ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገው የፕሬዚዳንቱ የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶች የ34 በመቶ ጭማሪ ተጥሎባቸዋል።
ቻይናም ይህን የፕሬዚዳንቱን ርምጃ ተከትሎ ባወጣችው መግለጫ ውሳኔውን እንደምትቃወም ገልፃ፣ ‹‹ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ቆራጥ›› መሆኗን አሳውቃለች። የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር አሜሪካ ታሪፉን በፍጥነት እንድትሰርዝ ጠይቆ፣ ቻይና ‹‹የራሷን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት የአፀፋ ርምጃዎችን ትወስዳለች›› ማለቱ ይታወሳል።
ቻይና የአፀፋ ርምጃዎችን እንደምትወስድ ቃል በገባችው መሠረት ቀደም ሲል ለተጣለባት ታሪፍ እንዲሆን ከአሜሪካ ወደ ቻይና በሚላኩ የድንጋይ ከሰልና የተፈጥሮ ጋዝ ምርቶች ላይ የ 15 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጓን አሳውቃ ነበር። ባለፈው ሳምንት ይፋ ለተደረገው የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ደግሞ በአሜሪካ ምርቶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር የ34 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንደምትጥል ከቀናት በፊት ይፋ አድርጋለች።
በዚህ የቻይና ምላሽ ክፉኛ የተበሳጩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ቻይና ውሳኔዋን የማትቀለብስ ከሆነ ከትናንት ጀምሮ የሚተገበር የ50 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀዋል። ከአቋሜ ፍንክች አልልም ያለችው ቻይና ግን በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችውን የታሪፍ ጭማሪ ወደ 84 በመቶ አሳድጋዋለች። ይህ ማለት አሜሪካ በቻይና ላይ የ 104 በመቶ፣ ቻይና ደግሞ በአሜሪካ ላይ የ84 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ አድርገዋል ማለት ነው።
ቻይና ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ የ 34 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ምላሽ ከሰጠችና ትራምፕም ቻይናን ካስጠነቀቁ በኋላ ቻይና የንግድ ድርድር ማድረግ እንደምትፈልግ ተናግረው ነበር። ‹‹ብዙ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ድርድር ማድረግ ይፈልጋሉ። እንዴት እንደሚጀምሩት አላወቁትም እንጂ ቻይናውያኑም ስምምነት ይፈልጋሉ። እየጠበቅናቸው ነው፤ መነጋገራችን አይቀርም›› ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ ግን የአሜሪካ የንግድ ድርድር ወኪል ጃሚሰን ግሪር ቻይና ከአሜሪካ ጋር የንግድ ድርድር ለማድረግ ባላት ፍላጎት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። ‹‹ቻይና የታሪፍ ጭማሪ ምላሽ መስጠትን መርጣለች፤ ሌሎች ሀገራት ግን እንደዚያ አላደረጉም። ምን ሊፈጠር እንደሚችል ወደፊት እናያለን›› ነው ያሉት።
ሁለቱ የዓለም ባለግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤቶች እንዲህ ያለ የንግድ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል። ፍጥጫቸውም የመቀዛቀዝ ምልክት የሚያሳይ አይመስልም። ቻይና ለአሜሪካ ከፍተኛ ምርት በመላክ በቀዳሚነት ተቀምጣለች። የአሜሪካ ገበያ ለቻይና ምርት ትልቅ ስፍራ አለው።
በፒተርሰን ኢንስቲትዩት የአሜሪካ- ቻይና የንግድ ጉዳዮች ጥናት ባለሙያ ሜሪ ላቭሊ፣ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለው ጨዋታ ቀውሱን መሸከም የሚችለው ማን ነው የሚለው ጉዳይ እንደሆነና በየትኛውም በኩል የሚያተርፍ እንደሌለ ይገልፃሉ። ‹‹ቻይና የምጣኔ ሀብቷ ቢያሽቆለቁል እንኳን የአሜሪካ ጥቃት ነው ብላ የምታምነውን ይህን ርምጃ ላለመቀበል የትኛውንም ሁኔታ ልትቋቋም ትችላለች›› ይላሉ።
ቻይና የወጪ ንግዷ የሚያሽቆለቁል ከሆነ ወሳኝ የሆነው የገቢ ምንጯ መጎዳቱ የማይቀር ነው። ለቻይና ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ መመንደግ የወጪ ንግዷ ለረጅም ጊዜ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ሀገሪቱ ምንም እንኳ የቴክኖሎጂ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍንና የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመጨመር የገቢ አቅሟን ለማስፋፋት እየሞከረች ቢሆንም፣ የወጪ ንግዷ አሁንም መሠረታዊ የገቢ ምንጯ ነው።
በሃርቫርድ ኬኔዲ ትምህርት ቤት (John F. Kennedy School of Government) ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት አንድሪው ኮሊየር፣ በቻይና ላይ የተጣሉት ታሪፎች ተጽዕኗቸው በቅርቡ ሊታይ እንደሚችል ያስረዳሉ። ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ እና ገቢ መቀነስ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ አጣብቂኝ የሆነ ምርጫ ሊገጥማቸው እንደሚችልም ያስጠነቅቃሉ።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ የ438 ቢሊዮን ዶላር ምርት ከቻይና ያስገባች ሲሆን፣ ቻይና ደግሞ 143 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአሜሪካ ሸምታለች። በዚህም አሜሪካ ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ የ 295 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ገጥሟታል። አሜሪካ ከቻይና የምታስገባቸውን ምርቶች በአጭር ጊዜ ከየትኞቹ ሀገራት በሚገኙ ምርቶች እንደምትተካቸው ግልጽ አይደለም።
‹‹ሁለቱ ሀገራት በምጣኔ ሀብት ረገድ በብዙ መንገዶች የተሳሰሩ ናቸው። በሀገራቱ መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው የኢንቨስትመንት፣ የዲጂታል ንግድ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ አለ›› ሲሉ የሚናገሩት ደግሞ በሲንጋፖር የሂንሪሽ ፋውንዴሽን የንግድ ፖሊሲ ኃላፊ ዲቦራ ኤልምስ ናቸው። ‹‹ታሪፍ መጣል የሚቻለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። ነገር ግን አንዱ ሀገር ሌላውን ሊጎዳበት የሚችልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ምናልባት ነገሮች የከፉ ሊሆኑ ይችላሉ›› ሲሉ ያክላሉ።
ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶቿን ወደየት ልትልክ እንደምትችል ቀሪው ዓለም እየጠበቀ መሆኑን ተናግረው፣ ምናልባትም እንደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ ወዳሉ ገበያዎች ሊሄዱ እንደሚችሉ ኃላፊዋ ያስረዳሉ።
ፕሬዚዳንቱ ለአሜሪካ ንግድ ‹‹ነፃነት››ን እንደሚያጎናጽፍ የተናገሩለት አዲሱ እቅዳቸው አሜሪካን ተጠቃሚና በድጋሚ ባለጸጋ እንደሚያደርጋት ቢናገሩም፣ በውሳኔያቸው በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚን በመገንባት ላይ የሚገኙት የደቡብ አሜሪካ እና የደቡባዊና ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚደርስባቸው ተገልጿል። ትራምፕ ከመቶ በላይ በሚሆኑ ሀገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ የዓለም አክሲዮን ገበያ አሽቆልቁሏል። በተለይም የእስያ የአክሲዮን ገበያ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ የከፋ ማሽቆልቆል አጋጥሞታል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም