ለወጣቱ የተፈጠረው የኢኖቬሽን ምህዳር

ወጣትነት የሕይወት ዘመን አንዱ ምዕራፍ ነው። በሰው ልጅ የሕይወት ዘመን ወርቃማ የእድሜ ዘመን ይባላል። ይህ ወርቃማ የእድሜ ዘመን ትኩስ ኃይልና እምቅ አቅም በአንድነት አጣምሮ ይዟል።

ወጣትነት ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን ለመኖር የሚያስችል ሕይወት ለመምራት መሠረት የሚጣልበት ዋንኛ የእድሜ ክልል ሲሆን፣ በጎውም ሆነ ክፉው ፊት ለፊቱ የሚቀርቡበት የሕይወት ዘመን ነው። በዚህ ወቅት ወጣቱ ወይ እድል ሊቀናው ፣ ራሱን ካልገዛ ደግሞ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ የሚጠለፍበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።

በጎው በበጎነቱ እንዲቀጥል፤ መጥፎውን አሽቀንጥሮ በመጣል ወደፊት ለመጓዝ በከፍተኛ ትግልና ጥረት ውስጥ ማለፍ የግድ ይላል። አላስፈላጊውን መተው በጎውን መከተልና ማስቀጠል ያስፈልጋልና በዚህ የሕይወት መስመር ለመጓዝ ብልሃት የተሟላበት አካሄድ መከተል ያስፈልጋል።

እነዚህ ሁለት ተቃራኒ መንገዶች ወጣቱን ወደ የተለያዩ መንገዶች ሊመሩት ይችላሉ። በጎ ዓላማን አንግቦ ለነገ የሚሆን የሕይወት ስንቅ ለመቋጠር ቀን ከሌሊት የሚለፋና የሚሯሯጥ ሊያደርጉት ሲችሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ ጊዜውን በዋዛ በፈዛዛ በከንቱ በማሳለፍ ወደ ሱሶችና ሌሎች ያልተገቡ መንገዶች እንዲያመራ ሊያደርጉ ይችላሉ። ወጣቱ እነዚህን መንገዶች በሚገባ አስተውሎ ያለውን ኃይልና አቅም ተጠቅሞ ሠርቶ ለመለወጥ፤ ከራሱ አልፎ ሀገርን ለመጥቀም ዝግጁ መሆን ይኖርበታል።

ወጣትነት ከተሠራበት ምርጥ የእድሜ ዘመን ነው፤ ሳይጠቀሙበት ካመለጠ ግን ሊደገምም ወይም ወደ ኋላ ሊመለስ አይችልም፤ ይባክናል። የወጣትነት ጊዜን በአግባቡ ይዘን በጥልቀት አስቦ ለመሥራት መንፈስንና አቅም አቀናጅቶ ለሥራ ዝግጁ እስካልተሆነ ድረስ በከንቱ ካለፈ ከቁጭት በዘለለ ሌላ ምንም አይነት ትርፍ ሊያስገኝ አይችልም።

መሥራት ባለበት ጊዜ ካልተሠራ፣ መሮጥ በሚቻልበት እድሜ ካልተሮጠ ሁሉም በጊዜው ያልፍና በኋላ ወደሰማይ ቢያንጋጥጡ፣ ምድር ላይ ቢፈጠፈጡ፤ በመውደቅ በመነሳት ከላይ ታች ቢሯሯጡ ትርፉ ከንቱ ልፋት ነው። ወጣትነት ካለፈ በኋላ የሚደረግ ሩጫም እንደወጣትነቱ ጊዜ ሩጫ አይሆንም።

‹‹ወጣት የነብር ጣት›› እንዲሉ አበው፤ ነብር ከእንጨት ወደ እንጨት ለመዝለል ጣቶቹ ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው ሁሉ፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣትም በዚያው ልክ ለሀገር ተፈላጊ ሞተር ነው። ይህ ሠርቶ መለወጥና ሀገር መለወጥ የሚችል ሞተር የሆነ ኃይል በደንብ ማሠራትና ማንቃት ከሁሉም በላይ እጅግ ያስፈልጋል።

በተለይ አሁን ባለንበት ‹‹ዘመነ ቴክኖሎጂ›› ወጣቱን እንዳይሠራና እንዳይለወጥ የሚያደርጉ ብዙ ነጣቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደአሸን ፈልተዋል። ወጣቱን በማይሆን መንገድ እንዲጓዝ ከሚያደርጉ ነጣቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ዋንኛዎቹ የማህበራዊ ሚዲያዎች አማራጮች ናቸው። ቴክኖሎጂዎቹ በራሳቸው ችግር የለባቸውም፤ ባልተገባ መልኩ ላልተፈለገ ዓላማ እንዲውሉ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ወጣቱ የሚጠበቅበትን እንዳይሆን የሚያደርጉት። ወጣቶች አጠቃቀሙን እስካለወቁበት ድረስ የትኛውም አይነት የማህበራዊ ሚዲያ አማራጭ ቢስፋፉ ወጣቱ በአግባቡ ካልተጠቀመበት ትርፍ የለውም።

ከዚህም ሌላ ወጣቱ ሌሎች በሠሩት ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ውጤት እየተገረመና እየተደመመ ጊዜውን በከንቱ እንዲያሳልፍና እጅና እግሩን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ሊያደርጉት ይችላሉ።

ችግሩ ከዚህም ሊሻገር ይችላል። የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳና ጥቅም ለሚያሳድዱ ኃይሎች መጠቀሚያ በመሆን በማያውቀው ጉዳይ ገብቶ ሀገሩንና ወገኑን ሊጎዳ የሚችል ድርጊትም ሊፈጽም ይችላል። ቴክኖሎጂ ለበጎ ዓላማ ከዋለ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ እንደሚችለው ሁሉ ለመጥፎ ተግባር ከዋለም ጉዳቱ የዚያኑ ያህል የከፋ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

በመሆኑም ወጣቱ ሳያስበው ባላስፈላጊ መንገድ ተጉዞ አቅጣጫ ስቶ አጓጉል አወዳደቅ ከመውደቅ ሊጠበቅ ይገባል። ‹‹ቀድሞ ነበር እንጂ አልሞ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ›› እንደተባለው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን አስቀድሞ መለየት ይኖርበታል። ወጣቱን ከእዚህ አይነቱ ችግር ለመታደግ አስቀድመን ማንቃት፣ መስመር ማስያዝ፣ ማስተማርና መምከር ይገባል። በተለይ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ሰፊ የዲጂታል እውቀት እንዲያገኝና ያንን ተጠቅሞ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን መምራትና ማመላከት ይሻል።

ከጠቅላላ ሕዝቧ ከ70 በመቶ በላይ የወጣት ኃይል ያላት ኢትዮጵያ ወጣቱ የቴክኖሎጂውን ዓለም በሚገባ እንዲቀላቀል በማገዝ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለሀገር የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠራና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ማድረግ ይገባል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥትም የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ወጣቱ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን እየሠራ ይገኛል። ምቹ የኢኖቬሽን ምህዳር በመገንባት ወጣቱ በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል እውቀት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው። ለዚህም በዚህ በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የተጀመረው ‹የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ይጠቀሳል።

በዚህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)አነሳሽነት የተጀመረው የአምስት ሚሊዮን ዜጎች የኮዲንግ ሥልጠና በርካታ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። ባለፉት ስድስት ወራት ከ422ሺህ በላይ ዜጎች ሥልጠናውን ተከታትለዋል፤ ከ104 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሰርተፍኬት ማግኘታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ይህንን ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የመጣ ወርቃማ እድል መጠቀም መቻል ደግሞ ወርቃማውን የእድሜ ዘመን እንደመዋጀት ይቆጠራል። ሥልጠናውን ወስደው ያጠናቀቁ ዜጎችም በሀገር ውስጥና በውጭ በቀላሉ ሥራ ሊያገኙ ወይም ሥራ ሊፈጥሩ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው። ከዚህም ባሻገር ዓለም በዲጂታል ዘርፍ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ጥግ በመገንዘብ የህብረተሰቡን ብሎም የሀገርን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችና የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩም በር እንደሚከፍትም ይታመናል።

እዚህ ላይ ወጣቱ ልብ ሊል የሚገባው ትልቁ ጉዳይ ይህን መሰሉ ታላቅ እድል እንዳያመልጠው ተሽቀዳድሞ ሥልጠናውን መውሰድ የሚኖርበት መሆኑን ነው። ከዚያም ሥልጠናውን መሠረት አድርጎ ሥራ በመፍጠር ከራሱም አልፎ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥር ይችላል።

ይህ በየዕለቱ አዳዲስ፣ ተቀያያሪና ተለዋዋጭ ክስተቶች የሚስተናገዱበት ዘመነ ቴክኖሎጂ ከዘመኑ ጋር ዘምኖ የዓለምን አካሄድ ተረድቶ አብሮ መጓዝን ይጠይቃል። ለነገ ተብሎ የሚተው ቴክኖሎጂ የለም፤ ዛሬውኑ ሊዚያውም በፍጥነት ወደ የዲጂታል ዓለሙ በመቀላቀል ይህን ወሳኝ እድሜውን ሊጠቀምበት ይገባል።

ወጣቱ በፍጥነት የተፈጠረለትን ምቹ እድል ተጠቅሞ እውቀቱን በእጁ ለማስገባት ጊዜው አሁን ነው። ለዚህም ደግሞ መምህራንን፣ ወላጆች፣ የሚመለከታቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በሙሉ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል።

ቸር እንሰንብት።

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You