«በሕዝብ አመኔታ ያላቸው የምርጫ ቦርድ የሥራ አመራርና አባላት እንዲመረጡ እንሠራለን» – ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የምርጫ ቦርድ መልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢ

አዲስ አበባ፡በሕዝብ አመኔታ ያላቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራርና አባላት እንዲመረጡ እንሠራለን ሲል የብሔራዊ በምርጫ ቦርድ እጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ አመለከቱ፡፡

ሰብሳቢው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢና የሁለት አባላት ምርጫ በሕዝብ አመኔታ ያላቸው እንዲሆኑ እንሠራለን፡፡ ተመራጮቹ የሀገር ኃላፊነት የሚጣልባቸው በመሆኑ ለምርጫ የሚቀርቡት ሰዎች በሕዝብ አመኔታ የሚጣልባቸው ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ኮሚቴው ሶስት የማጣሪያ መንገዶችን በመጠቀም ሥራውን የሚያከናውን መሆኑን አመልክተው፤ ዜግነትን ፤ገለልተኝነትና ሌሎች መስፈርቶችን ሙሉ ለሙሉ ተጣርተው ከተረጋገጡ በኋላ እጩዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

ግልጽነት ባለውና አወዳዳሪ በሆነ አካሄድ እጩዎችን ለማቅረብ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ለፖለቲካ ድርጅቶችና ለሲቪል ማህበረሰብ ከዛሬ ሚያዚያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ይፋዊ የእጩዎች ጥቆማ ጥሪ መቅረቡን ተናግረዋል።

ጥቆማው ከረቡዕ ሚያዚያ አንድ ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ሚያዚያ 21 ቀን 2017ዓ.ም ከቀኑ አስራአንድ ሰአት ድረስ ብቻ የሚቆይ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። ከዚህ የጊዜ ገደብ ውጪ የሚቀርቡ ጥቆማዎች ተቀባይነት የሌላቸው በመሆኑ ውድቅ የሚደረጉ ናቸው ብለዋል።

ጥቆማዎች የሚቀርቡትም በጽሁፍ ሲሆን ለዚህም ኢሜይል erc@hopr.gov.et ዋትስአፕ፤ +251900357507 ቴሌግራም +251900357507 ወይንም በፖስታ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ እጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ የመልእክት ሳጥን ቁጥር 80001 አዲስ አበባ የሚሉ አድራሻዎች መጠቀም እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም በአካል ማቅረብ ለሚፈልጉም አራት ኪሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእንግዳ መቀበያ ቢሮ በሚዘጋጅ ዝግ ሳጥን ውስጥ የጥቆማ ወረቀታቸውን ማስቀመጥ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ተጠቋሚዎች ማሟላት አለባቸው የተባሉት መስፈርቶችም መካከልም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ ፤ ገለልተኝነት የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ / ያልሆነች ፤ ሙያዊ ብቃት ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በሕግ ፤ በፖለቲካል ሳይንስ ፤ በሕዝብ አስተዳደር ፤ በስታስቲክስ፤ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ተዛማች ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያለው / ያላት፤ መልካም ሥነ ምግባርንየተላበሰ መሆን እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡

ሰብዕናን በተመለከተም በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙሃኑ በሚስማማባቸው የግብረ ገብ እሴቶች በሕጎችና በሙያ ሥነ ምግባሮች ላይ የተመሠረቱ መርሆዎችን የሚጥሱ ተግባራትን ፈጽመው ያልተገኙ፤ ኃላፊነት የመሸከም ብቃት፤ የሚሰጠውን ወይም የሚሰጣትን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር ብቃት ያለው ወይም ያላት መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና ሁለት አባላትን ለመመልመል የሚያስችል ኮሚቴ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You