
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር የሚቃወሙ ሰልፎች ሰሞኑን በአሜሪካና በአውሮፓ ዋና ዋና ከተሞች ተካሂደዋል። ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር የፕሬዚዳንትነት መንበረ ሥልጣኑን ከተረከቡ ወዲህ የታየ ትልቅ ሰልፍ ነው የተባለው የተቃውሞ ትዕይንቱ ‹‹እጃችሁን አንሱ›› (Hands Offs) በሚል የንቅናቄ መሪ ቃል ተካሂዷል።
‹‹የእጃችሁን አንሱ›› የተቃውሞ መሪዎች በ50 የአሜሪካ ግዛቶች በሚገኙ በአንድ ሺህ 200 አካባቢዎች ሰልፎችን ለማድረግ አስበው ነበር። በቦስተን፣ ቺካጎ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ኒው ዮርክ እና ዋሺንግተን ዲሲን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ ተሳትፈዋል። በመላው አሜሪካ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች በሰልፎቹ ላይ መሳተፋቸውን የተቃውሞው አዘጋጆች ተናግረዋል።
የአልጀዚራው ማይክ ሃና ከዋሺንግተን ዲሲ ባሰራጨው ዘገባ እንዳመለከተው፣ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የመንግሥት አሠራር ቅልጥፍናን እንዲመዝን የተደራጀውን ተቋም (Department of Government Efficiency – DOGE) በሚመሩት ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ላይ ቁጣቸውን አሰምተዋል። ተቃዋሚዎቹ ትራምፕ ከማኅበራዊ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚያራምዱት አጀንዳ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።
‹‹ትራምፕ በድጋሚ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ ከታዩ ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች መካከል አንዱ ነው። ሰልፎቹ አሜሪካውያን የገባቸውን ስጋትና ጥርጣሬ የሚያሳዩ ሳሆኑ አይቀሩም ተብሏል። የሰልፎቹ አስተባባሪዎች እንደተናገሩት ሰልፎቹ ፈጣን ለውጥ ባያመጡም አሜሪካውያን ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚያደርጓቸውን ነገሮች እየተቃወሙ እንደሆነ ግን ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። ሰልፈኞቹ በተለያዩ የእድሜ ክልሎች ውስጥ ያሉ ሰዎች የተሳተፉባቸው መሆናቸውም ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው›› በማለት ገልጿል።
በዋሺንግተን ዲሲ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሕግ አውጪዎችን ንግግር ሲያዳምጡ ታይተዋል። ብዙዎቹ አስተያየቶች ያተኮሩት በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ሀብታሞች በሚጫወቱት ሚና ላይ ነበር። ዋነኛው ትኩረት ደግሞ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ በመሆን በሚያገለግሉት እና ወጪዎችን እና የፌዴራል የሥራ ሃይልን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ጥረት በሚያደርጉት ኤለን መስክ ላይ ነው። መስክ የሚመራው ተቋም በወሰዳቸው ርምጃዎች በአሜሪካ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በርካታ የሥራ መደቦች እንዲታጠፉ ተደርገዋል።
የፍሎሪዳ ኮንግረስማን ማክስዌል ፍሮስት ‹‹መንግሥታችን በቢሊየነር ተወሯል›› ሲሉ የትራምፕን አስተዳደርና መስክን አውግዘዋል። ‹‹ከሕዝብ ስትሰርቁ ሕዝቡ እንደሚነሳ ጠብቁ። ይህ ደግሞ በምርጫ ኮሮጆ እና በጎዳና ላይ ይገለጻል›› ብለዋል። በዋሺንግተኑ ሰልፍ ላይ የፍልስጤም ደጋፊ ቡኖችም የተሳተፉ ሲሆን፣ የትራምፕ አስተዳደር ለእስራኤል የሚያደርገውን ድጋፍ እና ለፍልስጤማያን ድምጻቸውን እያሰሙ ባሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለውን ርምጃ አውግዘዋል።
በቦስተን ደግሞ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ለእስር እና ከሀገር ለመውጣት በመገደዳቸው ሰልፉን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተናግረዋል።
ፀረ- ትራምፕ የተቃውሞ ሰልፎቹ ከአሜሪካ በተጨማሪ በአውሮፓ ታላላቅ ከተሞችም ተደርገዋል። ፓሪስ፣ ለንደን፣ ፍራንክፈርትና በርሊን መሰል ሰልፎችን አስተናግደዋል። በፓሪስ አብዛኞቹ አሜሪካውያን የሆኑ ከ200 በላይ ሰልፈኞች በፕሌስ ዴ ላ ሪፐብሊክ አደባባይ በመገኘት የትራምፕን አስተዳደር የሚያወግዙ መፈክሮችን ሲያሰሙ ታይተዋል።
የለንደን ሰልፈኞች ደግሞ ትራምፕ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያደረጓቸውን ለውጦች በመጥቀስ ‹‹ከካናዳ ላይ እጃችሁን አንሱ፣ ከግሪንላንድ ላይ እጃችሁን አንሱ፣ ከዩክሬን ላይ እጃችሁን አንሱ…›› ሲሉ ተሰምቷል። ትራምፕ ካናዳ እና ግሪንላንድን ለመጠቅለል ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል። በቅርቡ ትራምፕ በሀገራት ላይ ያደረጉት የታሪፍ ጭማሪም ወደ ሌላ የንግድ ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል ነው የተባለው።
ዋይት ሃውስ የትራምፕን አቋምና ርምጃዎችን ትክክለኛ ስለመሆናቸው ገልጿል። ረዳት የፕሬስ ኃላፊዋ ሊዝ ሂዩስተን ‹‹የፕሬዚዳንት ትራምፕ አቋም ግልጽ ነው። የማኅበራዊ ዋስትና፣ የሜዲኬር እና የሜዲክኤይድ አገልግሎቶች ለሚገባቸው ዜጎች ሁልጊዜም ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል። የዴሞክራቶች አቋም ደግሞ እነዚህን አገልግሎቶችና ጥቅማጥቅሞችን ለሕገ-ወጥ የውጭ ዜጎች በመስጠት እነዚህን ፕሮግራሞች ከማክሰር ባለፈ የአሜሪካ ዜጎችን ይጎዳል›› ብለዋል።
ከትራምፕ ከፍተኛ የኢሚግሬሽን አማካሪዎች አንዱ ቶም ሆማን ለ ‹ፎክስ ኒውስ› እንደተናገሩት፣ ተቃዋሚዎች ከኒው ዮርክ መኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ሰልፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ‹‹ተቃውሞና ሰልፍ ምንም ማለት አይደለም። ስለዚህ ይቀጥሉ እና የመናገር ነፃነት መብቶቻቸውን ይጠቀሙ። ይህ እውነታውን አይለውጥም›› ብለዋል።
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አንዳንድ የሕዝብ አስተያየት ውጤቶች የፕሬዚዳንት ትራምፕ ተቀባይነት በጥቂቱ መቀነሱን አሳይተዋል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተለቀቀው ‹‹ዋን ሮይተርስ/አይፕሶስ›› የሕዝብ አስተያየት የትራምፕ ሕዝባዊ ቅቡልነት ወደ 43 በመቶ ዝቅ ማለቱን እና ይህም ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ጥር ወር ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ ወዲህ ዝቅተኛው ነጥብ መሆኑን አሳይቷል። በወቅቱ የትራምፕ ተቀባይነት 47 በመቶ ነበር።
ተመሳሳይ ጥናት እንዳመለከተው 37 በመቶ አሜሪካውያን የኢኮኖሚውን አያያዝ ሲደግፉ፣ 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ያላቸውን ስትራቴጂ ደግፈዋል። ‹‹በሃርቫርድ ካፕ/ሃሪስ›› የሕዝብ አስተያየት ውጤት ደግሞ ለትራምፕ አፈጻጸም ድጋፍ የቸሩት 49 በመቶ ቢሆኑም ባለፈው ወር ከነበረበት ከ52 በመቶ መቀነሱ ታይቷል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም