
በኢትዮጵያ የካፍን ደረጃ የሚያሟሉ ስታዲየሞች ባለመኖራቸው አሕጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሀገር ውስጥ ማካሄድ አትችልም ከተባለ ዓመታት መቆጠራቸው ይታወቃል። ይህንን ውሳኔ ተከትሎም ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በስደት በማከናወን ላይ ይገኛል። በእነዚህ ጊዜያትም አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች ያካሄደው በሞሮኮ የተውሶ ስታዲየሞች ነው። ታዲያ በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ለአንድ ጨዋታ ብቻ እስከ 70ሺ ዶላር ወጪ ይጠበቅባታል። ይህ ገንዘብ በተወሰኑ ጨዋታዎች ቢሰላ ደግሞ ምናልባትም አዲስ ስታዲየም ለመገንባት የሚያስችላት ነው፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር የስፖርት አመራሮች ጋር በፈጠሩት መልካም ግንኙነት ከወጪዋ ከ40 እስከ 50 ሺ ዶላር የሚደርሰው በሞሮኮ መንግሥት ተሸፍኖላታል። እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር ይህ ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም ካላት የስታዲየሞች ቁጥር አንጻር ግን የሚያስቆጭ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ለስፖርቱ በጎ ተግባር እየፈጸመችላት ካለችው ሞሮኮ መማር ያለባት ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ። በሰሜን አፍሪካም ሆነ እንደአጠቃላይ በአሕጉሪቱ በስፖርት መልካም ስምና ዝና መገንባት የቻለችው ሀገሪቷ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ቅድሚያ ተመራጭ መሆኗ ይታወቃል። በእግር ኳስ እአአ የ2030 ዓለም ዋንጫን ከስፔንና ከፖርቹጋል ጋር እንድታዘጋጅ (ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል በአሕጉሩ ሁለተኛዋ ሀገር) ከመመረጧ አስቀድሞ በርካታ ትልልቅ ውድድሮችን አስተናግዳለች። በአትሌቲክስም ቢሆን በአፍሪካ ብቸኛው የዳይመንድ ሊግ መዳረሻ የሆነችው ዋና ከተማዋ ራባት ናት።
በሌሎች ስፖርቶችም ቢሆን ትልልቅ ሻምፒዮናዎችን ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳድራ የማስተናገድ አቅም መገንባት የቻለች የስፖርት ወዳዶች ሀገር ናት። የስፖርቱ ፍቅር ከሕዝቡ ባለፈ በመንግሥቷም ዘንድ የሰረጸ መሆኑ ደግሞ ለለውጡ መሠረታዊ የሆነ ጉዳይ ነው። በስፖርት ኢኮኖሚዋን ለመደገፍና የቱሪዝም መስሕብነቷን ለማሳደግ ቆርጣ የተነሳችው ሀገሪቷ በአፍሪካ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች (32 ስታዲየሞች) ካሏቸው ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ከአምስት ዓመታት በኋላ ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መያዝ የሚያስችል እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ ስታዲየም በመገንባት ላይ ትገኛለች። ይኸውም አፍሪካን ብቻም ሳይሆን የበለፀጉትን ሀገራት ጭምር ያስገረመና ለስፖርቱ የሰጠችውን ትኩረት ያመላከተ ሆኗል።
እጅግ አስደናቂውና ሀገሪቷን ለተቀረው ዓለም ማሳያ የሚያደርጋት ጉዳይ ደግሞ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ሁለት አስርተ ዓመታትን እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ ነው። እአአ ከ2007 አንስቶ የሞሮኮ ሕዝብ በስፋት ወደ ስፖርት ተሳትፎ የገባ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ እጅ ኳስ፣ ቴኒስ፣ ጎልፍ፣ ቅርጫት ኳስ በመሳሰሉት ስፖርቶች ተፎካካሪ መሆን ችሏል። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታትም ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችንና አካዳሚዎችን በስፋትና በጥራት መገንባት ችላለች። የሀገሪቷ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ አፍሪካንና አውሮፓን ማገናኘት የሚያስችል መሆኑ ተመራጭ የሚያደርጋት እንደመሆኑ ስፖርትን እንደ አንድ ኢኮኖሚያዊ ስትራቴጂ በመጠቀም በትኩረት እየሠራችበት ትገኛለች። ይህ ወቅት ደግሞ በቢሊየን የሚቆጠር ገቢን የማግኘት ዓላማዋን ወደ ተግባር የምትቀይርበት ነው።
ይህንን ድንቅ ተሞክሮም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት መጋራት ቢችሉ ተጠቃሚነታቸው እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠራጥርም። የአፍሪካ መዲና እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) ከቦታ አቀማመጧና ሌሎች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች አንጻር ትልልቅ ውድድሮችን ለማስተናገድ እንደ ሞሮኮ ሁሉ ተመራጭ መሆኗ አያጠራጥርም። በመሆኑም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ በተለይም የተጀመሩ ስታዲየሞችን የፊፋና የካፍ ደረጃን ባሟላ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ማድረግ ቢቻል እንደሀገር ተጠቃሚ ብቻም ሳይሆን እንደ ምሥራቅ አፍሪካም ኢትዮጵያን የስፖርት ማዕከል ማድረግ ይቻላል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በወጣ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ 11 ስታዲየሞች ያሏት ሲሆን ይህም ቁጥር በአፍሪካ መካከለኛ ስፍራ ላይ ያስቀምጣታል። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ስታዲየም አንድም የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት ማሟላት የቻለ አለመኖሩ አሳፋሪም አነጋጋሪም ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ስፖርት ወዳድ፣ ባገኘው አጋጣሚ ተሳታፊ እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎችን ቢያገኝ በበርካታ ስፖርቶች ተፎካካሪ እንደመሆኑ መሰል ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ይገባዋል። በመሆኑም መንግሥት በዘርፉ የሚያገኘውን ጥቅም በማገናዘብ የተጀመሩትን በማስፈጸምና በሃሳብ ደረጃ ያሉትንም ወደ ተግባር በማሸጋገር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ስፖርት ያላትን የጀማሪነት ታሪክ ሊደግፍ የሚችል ርምጃ መውሰድ ይገባዋል።
በእርግጥም በብሔራዊ (አደይ አበባ ስታዲየም) እና በባሕርዳር ስታዲየም እየተከናወኑ የሚገኙት ማስፈጸሚያ ሥራዎች እጅግ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ናቸው። ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ተደርገው እየተሠሩ የሚገኙት ስታዲየሞች ከሚደረግባቸው ርብርብ አንጻር በቅርቡ ተጠናቀው ብሔራዊ ቡድኑን ከስደት እንደሚመልሱት ይጠበቃል። በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣበትና ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ የሀገሪቷ ትልቁ ፕሮጀክት የሆነው የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያረጋግጥ ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት ካለመው የ2029ኙ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ጋር በተያያዘ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ፣ በተባለው የጥራት ደረጃና ወቅቱን ከጠበቀ ቴክኖሎጂ እንዲጠናቀቅ ልዩ ክትትል ሊያደርግበት ይገባል።
በ2008 ዓ.ም የተጀመረው የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ሲሸጋገር በርካታ አላስፈላጊ ጉዳዮች መከሰታቸው ዋጋ አስከፍለዋል። የተመደበው ገንዘብ በሚጠበቀው ልክ ሥራ ላይ ካለመዋሉ ባለፈ የተቀመጠው ጊዜ መባከኑ የስፖርት ቤተሰቡን የሚያስቆጭና እስካሁንም ድረስ ስፖርቱን እየጎዳ ያለ ነው። በመሆኑም እጅግ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የወጣበት ግንባታ መሰል ስህተት እንዳይፈጸምበት እንዲሁም በየዕለቱ በሚንረው የቁሳቁስ ዋጋ ምክንያት ተጨማሪ ወጪ ከመጠየቁ አስቀድሞ በውል ስምምነቱ ላይ በተቀመጠው ሁኔታ እንዲገነባ ለማድረግ ክትትል ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነቱ ጋር በተያያዘም ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነው። በመሆኑም የታሪካዊውንና እድሜ ጠገቡን የአዲስ አበባ ስታዲየምን እድሳት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲከናወን ማድረግ አስፈላጊ ነው። በየክልሉ ያሉ ሌሎች ስታዲየሞችንም የአፍሪካ ዋንጫውን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ በአግባቡ እንዲገነቡን የበኩሉን ድጋፍና ክትትል ሊያደርግ ይገባል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም