በሁሉም ዘርፍ የምግብ ሥርዓትን የማጠናከር ጉዞ

ኢትዮጵያ የምግብ ሽግግር ተግባር የተሳለጠ ለማድረግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተቀመጠው መስፈርት መሠረት የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ይነገራል፡፡ እንደ ሀገር በተሠሩ ሥራዎች አርዓያ በመሆን፤ በዘንድሮ ዓመት የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የምግብ ሽግግር ስብሰባን ለማዘጋጀት ታጭታለች፡፡

የምግብ ሽግግር የ2016 በጀት ዓመት የግማሽ ወራት ትግበራ አፈጻጸም፤ ሥርዓተ ምግብ እና የሰቆጣ ቃልኪዳን የዘንድሮ በጀት ዓመት የግማሽ ወር አፈጻጸም ግምገማ እንዲሁም፤ በሐምሌ ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የሥርዓተ ምግብ ስብሰባ አስመልክቶ የሚኒስትሮች የምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን ዐቢይ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ውይይት አድርጓል፡፡

በወቅቱ የጤና ሚኒስትር እና የዐቢይ ኮሚቴው የጋራ ሰብሳቢ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደሚገልጹት፤ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፤ በጉዳዩ ላይ ስልታዊ ትግበራን ማከናወን ዋናው ተግባር ነው፡፡ ይህን ሥራ መሥራት ከተጀመረ አራት ዓመታት የተቆጠረ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት በፌዴራል እንዲሁም በክልሎች በርካታ ሥራዎች እስከታች ድረስ በማውረድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በተለይ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በተሠራው ሥራ፤ ከ240 ወረዳዎች በማደግ፤ አሁን ላይ በ334 ወረዳዎች የሥርዓተ ምግብ ትግበራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በ2022 ዓ.ም ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የመቀንጨር ምጣኔ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት በ2007 ዓ.ም የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ15 ዓመት እቅድ ይዞ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ በ2014 ዓ.ም ወደ ማስፋፋት ምዕራፍ ለመግባት መንግሥት ትልቅ ትኩረት በመስጠቱ፤ አሁን የማስፋፊያ ሥራው ከደረሰበት በላይ ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ለ15 ዓመታት የተቀመጠውን ፍኖተ ካርታ ከመተግበር እና በከፍተኛ አመራር ደረጃ ትኩረት ከመስጠት አንጻር ብዙ ስኬቶች ቢስተዋሉም፤ ከሥርዓተ ምግብ አንጻር በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማነስ ይታያል፡፡ ለዚህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፤ የሥርዓት ምግብን ለማስተካከል የግንዛቤ መስጫ መድረኮች ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት እድገት መከታተል እና ማበልፀግ በተመለከተ ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ይታወቃል የሚሉት ሚኒስትሯ፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የእድገት ክትትል ማበልፀግ 80 በመቶ ከፍ ማለቱን ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርና ኒውትሪሽን ኮሚቴ፤ የአየር ንብረት ለውጥ አስተባባሪ ከፈለኝ ጌታሁን (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች ጋር መጣጣም ካልተቻለ ችግር ውስጥ ሊያስገባን ይችላል። የዓለም የምግብ ድርጅት ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት የመጀመሪያው ዓላማ የአየር ንብረት ለውጥ ሥራን እና የምግብ ሽግግርን በጋራ እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል።

የሥርዓተ ምግብ ኮሚቴው ከአየር ንብረት እና ከምግብ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ምን ሠራ የሚለው ሲነሳ፤ እንደ አጠቃላይ በአምስት ዘርፎች፤ በግብርና፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፤ በአካባቢ እና መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ለመሥራት ሞክሯል። የአየር ንብረት እና የምግብ ሥርዓቱ የቱ ጋር ነው የሚገናኙት በሚለው ዙሪያም ሥራዎች እየተከናወኑ እንዳሉም ያስረዳሉ ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ማመላከት የሚስችል ጥናት መካሄዱን ያነሱት አስተባባሪው፤ የአየር ንብረት ለውጥ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ እንደአጠቃላይ ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ ለአብነትም በ2050፤ 35በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ መሬት በድርቅ እንደሚጎዳ ይገመታል፡፡ ይህ ደግሞ ለሥርዓተ ምግቡ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከፈለኝ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ሥርዓተ ምግብ ሲታሰብ የአፈር ጥበቃ ሊታሰብ ይገባል፡፡ በሀገሪቱ 20 በመቶ የሚሆነው መሬት በሚቀጥሉት ዓመታት የመሸርሸር አደጋ እንደሚገጥመው ይገመታል፡፡ በተጨማሪም 50 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ የውሃ እጥረት እንደሚያጋመው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

እነዚህ ሁሉ ሲታዩ በምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ከሀገሪቱ ሕዝብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆነው በርዳታ ሰጪዎች ላይ ተንተርሰው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣው ችግር ነው ማለት ነው ይላሉ፡፡

እነዚህ ቁጥሮች ሊያስደነግጡ ይችላሉ ነገር ግን በሌላ በኩል ችግሩን ለመቅረፍ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ እንደመልካም ጎን የሚወሰድ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት በኒውዮርክ ከተማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባስቀመጠው መሠረት የራሷን የሥርዓተ ምግብና ኒውትሪሽን ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታለች፡፡

ይህን ፍኖተ ካርታ ካዘጋጀች በኋላ፤ በካርታው መሠረት እንደሀገር በራሷም ሆነ፤ ከልማት አጋሮች ጋር በምትሠራው ሥራ ምን ያክል ከዚህ ፍኖተ ካርታ ጋር ይናበባል የሚለው ሀገራዊ ዳሰሳ ተደርጓል። በዚህም እየተሠሩ ያሉ ሌማት ትሩፋት፤ አረንጓዴ ዐሻራ፣ የትምህርት ቤት ምገባ ጨምሮ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሥራዎች ፍኖተ ካርታውን ለማስፈጸም የሚያግዙ መሆናቸው መለየቱን ይጠቁማሉ፡፡

ሚኒስትሩ እንደሚገልጹት፤ በሦስተኛ ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ከመገንባት ጋር እንዲናበብ የተደረገበት ሥራ በዘንድሮ ዓመት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ቀጣይ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ስብስባም ኢትዮጵያ በሥነ ምግብ የሠራችውን ሥራ በተለያዩ ጽሑፎች፤ በጉብኝቶች እና ኤግዚቢሽኖች የምታሳይ ይሆናል፡፡

የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ እና የምግብ ሥርዓተ- ምግብ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሕይወት ዳርሰኔ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ፤ በሰቆጣ ቃል ኪዳን የስድስት ወር አፈጻጸም በጤና ዘርፍ ከ400 ሺህ በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች የአይረን እንክብል፤ ከ800 ሺህ በላይ ሕጻናት የእድገት ክትትል አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡

በግብርና ዘርፍም ከ700 ሺህ በላይ ቤተሰቦች የጓሮ አትክልት እንዲያለሙ፤ ለሚያጠቡ እና ነፍሰጡር እናቶች ከ138 ሺህ በላይ የወተት ፍየሎች እንዲሁም፤ ከ500 ሺህ በላይ ዶሮች ተደራሽ ለማድረግ መቻሉን ያስረዳሉ፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You