በተግዳሮቶች ያልተበገረው የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ

የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ የሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም ሁሉም ማለት በሚቻልበት ደረጃ የሰው ልጆችን መሠረት ያደረጉ እና ማኅበረሰቡ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ አንድ ዜጎቿን የምታከብር ሀገር አለች ካልንም፤ መመዘኛው ለማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ምን ያህል ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው? የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው፡፡

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ያደረጉት ጥያቄዎችም ዜጎችን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ይሠሩ የሚል ነው፡፡ ይህንን የሚያውቀው መንግሥትም ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የሕዝቦች ሁሉንም ዓይነት ፍላጎቶች ለማድመጥ እና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ፈርጅ በማስያዝ ሥራዎችን ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲሠራ መቆየቱ ይነገራል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኮቪድ 19፤ የሰሜኑ ጦርነት፤ አስቀድሞ የነበረው የቢሮክራሲ አሠራር የሕግ ማሕቀፎች እና ሌሎችም ችግሮች እንደነበሩ ምሑራን ይናገራሉ፡፡

በያዝነው ሳምንት “ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ቃል የከተማ አቀፍ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ለተሳታፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሠረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) እንደገለጹትም፤ የለውጡ መንግሥት ከመጣ ወዲህ የነበሩትን ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮችን ተቋቁሞ የማኅበራዊ ልማቱን ለማሳደግ ተችሏል፡፡

መንግሥት ወደ ሥልጣን እንደመጣም ለልማት ሥራዎች አስፈላጊ የሆነ ሀብት ማሰባሰብ፤ የበጎ ፍቃዶችን ማጠናከር፤ የነበረውን የቢሮክራሲ እና መልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት እና የከተማዋን ደኅንነትና ሰላም የማስጠበቅ ሥራዎችን በትኩረት መሥራቱን አመልክተዋል፡፡

የትምህርት ልማትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ በአንደኛ እና በቅድመ አንደኛ የተማሪዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን 253ሺ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር ተችሏል፡፡ በተማሪ የምገባ አገልግሎት 850 ሺ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ በመቻሉ የተማሪ ቁጥርን መጨመር ተችሏል፡፡

በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን 37ሺ በላይ ተማሪዎችን ዩኒፎርም የማልበስ ሥራ ይሠራል፡፡ በዚህም ትምህርት የሚያቋርጠውን የተማሪ ቁጥር እና የወላጆችን ጭንቀት መቀነስ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በሚለው መርሐ ግብር 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህም መርሐ ግብር በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እና ቁሳቁሶችን ማሟላት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

እንደ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በጤናው ዘርፍ ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች በስፋት ተሠርተዋል፡፡ በሽታን አክሞ የማዳን ሥራ 96 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ ከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግም እየተሞከረ ነው፡፡

የከነማ ፋርማሲ ማዕከላትን የማስፋት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በከፍተኛ ደረጃም የጤና መድኅን ተጠቃሚ ቁጥርም እንዲጨምር ተደርጓል፡፡

የቅድመ ወሊድ ክትትል 102 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ 5200 የጤና ባለሙያዎች በመመደብ እና ቤት ለቤት እንዲሄዱ በማድረግ 360 ሺ ለሚሆኑ ሕጻናት የአዕምሮ እድገታቸውን ለማሻሻል የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

በወጣቶች ተሳትፎ ዙሪያም 114 የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ተገንብቶ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከ1300 በላይ የሚሆኑ የስፖርት ማዝወተሪያዎች ተገንብተዋል፡፡ 76 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶችን አመራር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡

የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግ እና ጫናም ሊያቃልሉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል፡፡ ለአብነትም የእንጦጦ ፕሮጀክት፣ የነገዋ፣ የእንጀራ ፋብሪካዎች እና የሕጻናት ማቆያዎችን ማንሳት እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡

በማዕድ ማጋራት ሥራ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ተደርገዋል፡፡ 24 በሚሆኑ የተስፋ ምገባ ማዕከላት ከ36ሺ በላይ ዜጎች በቀን አንዴ እንዲመገቡ እየተደረገ ነው፡፡ ባለሀብቶችን በማስተባበር ከ37ሺ 5 መቶ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለድሆች ተሰጥተዋል፡፡

በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ 87 የሚሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እንዲከናወኑ ተደርጓል፡፡ የኮሪዶር ልማት ሥራ፤ የወንዝ ዳርቻዎችን የማስዋብ ተግባር እና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን የሚያዘምኑ ሥራዎችም መከናወናቸውን ዓለማየሁ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You