
የሰው ልጅ ብዙ አዳጊ እና ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ያሉት ማኅበራዊ ፍጡር ነው ። ፍላጎቶቹ በጊዜ እና በቦታ ልኬት ውስጥ የሚያድሩ፤ ለፍላጎቶቹ ስኬትም በአንድም ይሁን በሌላ ዘመንን በአግባቡ ማወቅ እና በዘመኑ እሳቤ መዋጀትን ከሁሉም በላይ የሚጠይቅ ነው። ለውጥም የዚህ ተለዋዋጭ የሰው ልጅ አዳጊ ፍላጎት መገለጫ ክስተት ነው።
በተለይም በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጠር የለውጥ መሻት እና መሻቱ የሚወልደው ማኅበረሰባዊ መነቃቃት ያልተመለሱ ያደጉ ፍላጎቶች ምላሽ እንዲያገኙ የመፈለግ ውስጣዊ መነሳሳት ነው። ይህ መነሳሳት በተወሰነ የለውጥ ኃይል የዓላማ ቁርጠኝነት ፤ ወደ አደባባይ ይምጣ እንጂ ፤ የለውጡ ማኅበረሰባዊ ስሪት ግን ሕዝባዊ ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ።
የአንድ ማኅበረሰብ የለውጥ ፍላጎት ስኬት እና ውድቀትም የሚለካው በዚሁ ተጨባጭ እውነታ ነው ። ለውጡን የራሴ ነው ብሎ ፤ ዓላማ እና ተልዕኮውን ከራሱ የመለወጥ መሻት ጋር አስተሳስሮ የተቀበለ ፤ ለውጡ ሊያስከፍለው የሚችለውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁነት የፈጠረ ማኅበረሰብ በለውጡ ስኬታማ መሆኑ የማይቀር ነው።
ከዚህ በተጻራሪ በለውጥ ወቅት በሚፈጠሩ ግራ መጋባቶች በውስጡ ላለው የለውጥ መሻት ታማኝ መሆን ያልቻለ ፤ ለውጡን የራሱ መሆኑን ዘንግቶ ለተወሰኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሰጥቶ እራሱን የበይ ተመልካች ያደረገ ማኅበረሰብ ፤ የለውጡ ተጠቃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ የሚታሰብ አይደለም ።
ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ለውጡ እና የለውጡ እሳቤ የራሱ ሆኖ ሳለ በለውጥ ወቅት በሚፈጠሩ ግርግሮች በአንድም ይሁን በሌላ በለውጡ ላይ በተቃርኖ የሚሰለፍ ማኅበረሰብ ፤ ከለውጡ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ፍሬ በሌለው የለውጥ አዙሪት ውስጥ ያልተገባ ዋጋ ከመክፈል ያለፈ እጣ ፈንታ አይኖረውም ። ከመክሸፍ ውጪም መሻቶችን ተጨባጭ ማድረግ ፤ ለትውልድ ተስፋ የሚሆን የለውጥ ተሞክሮ ባለቤት የሚሆንበት ዕድል አይኖርም።
በሀገራችን አሁን ላይ ያለው ትውልድም ሆነ ፤ ከፍ ባለ የለውጥ መሻት ውስጥ ያለው መላው ሕዝባችን ከዚህ ተጨባጭ እውነታ እና ከትናንት የለውጥ ታሪኮቻችን ብዙ ሊማር ይገባል። በተለይም አሁን ያለው ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳት የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ ፤ ከዚህ ትውልድ አልፎ ለመጪ ትውልዶች የሚተርፍ ፍሬ እንዲያፈራ ፤ ይህንን እውነታ በአግባቡ መረዳት እና በተረዳ ማንነት የለውጡ አካል መሆን ይጠበቅበታል።
አሁን ላይ ያለው ሀገራዊ ለውጥ ሕዝባችን ከትናንቶች ጋር አብሮ ላለመቀጠል የደረሰበት ውሳኔ ሁለንተናዊ መገለጫ ነው ። ይህ ውሳኔ በብዙ መልኩ ይህን ትውልድም ሆነ የቀደመውን ከፈተኑት ያረጁ ፤ ያፈጁ ፖለቲካዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አስተሳሰቦች ጋር አብሮ ላለመቀጠል / ለመፋታት የተደረሰ ማኅበረሰባዊ ውሳኔ ነው።
ከዚህ ውሳኔ ላይ እንደ ማኅበረሰብ መድረስ የተቻለው ድንገት ሳይሆን አስተሳሰቦቹ እንደሀገር እና ሕዝብ ካስከፈሉን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተነሳ ነው። ከነዚህ ችግሮች ጋር አብሮ ለመቀጠል የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት እንደሀገር ያለንን መልክ ብቻ ሳይሆን ፤ ማንነት ጭምር ሊያሳጣን የሚችል ነው።
በለውጥ ውስጥ የሚፈጠሩ ግራመጋባቶች ይህንን እውነታ ለአፍታም ቢሆን ሊሸፍኑብን አይገባም ። ለውጡን እና የለውጡን እሳቤ ከዚያም አልፎ ለውጡን እያጋጠሙት ያሉ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የሚኖረን ሀገራዊ መነሳሳት ከዚህ ተጨባጭ እውነታ የሚቀዳ እና ለዚሁ እውነታ የተገዛ ሊሆን ይገባል ።
ከዚህ ውጪ በለውጡ እና በለውጡ ሂደት ላይ ለሚካሄዱ አፍራሽ እና አታካች ፕሮፓጋንዳዎች ራስን አሳልፎ በመስጠት ፤ የለውጥ ተሳትፎን ማቀዛቀዝም ሆነ ፤ የሌላ አካል የጥፋት ተልእኮ ድሪቶ በመደረብ የራስ በሆነው ለውጥ ላይ በተቃርኖ መቆም ውጤቱ አፍራሽ ነው። የለውጡን የጉዞ ፍጥነት በማዘግየትም የታሪክ ተጠያቂነት የሚያስከትልም ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም