
1.መግቢያ
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሸዋል ዒድ ምንድን ነው? ሸዋል ዒድ ከቅድመ ኢስላም እምነት ጋር የተያያዘ ይሆን? ወይስ ሌላ ምስጢር ይኖረው ይሆን? በዓሉ ለረጅም ጊዜ ሲከበር ኖሯል። ዛሬም በሀገር ውስጥና ሀረሪዎች በሚገኙበት ሀገር ሁሉ ይከበራል። ለመሆኑ ሀረሪ አባቶች ይህን በዓል የተረዱበት መንገድ ምንድን ነው? ሀረር ድርብ በዓል በማክበር ወይም ጥንታዊ በዓልን በፈለገችው መንገድና ዓላማ ለውጣ በማክበር ብቸኛዋ የሙስሊም “ሀገር” ናት? ለምን ከዚህ በዓል ጋር እጅግ ድንቅ የሆነው የበርቲ በርቲ ጨዋታ አይካሄድም? ምን ክልላዊ ፣ ብሔራዊም ጥቅም አለው ? የሚለውን በሚመለከት ብዙ ተጉዣለሁ።
በዚህ ረገድ በዓለም በርካታ ሙስሊም የሚገኝባቸው ሀገሮች፣ ዛሬ እንደኢስላማዊ በዓል ወይም ከኢስላማዊ በዓላት ጋር ደርበው የሚያከብሯቸውን በዓላት እግረ መንገዴን ለማጥናት ሞክሬያለሁ። ለማንኛውሞ ስለሀረሩ ሸዋል ዒድ ከማቅረቤ በፊት የሌሎችን ሀገሮች ተሞክሮ ለማቅረብ እሞክራለሁ። የመጀመሪያዋ ኢንዶኔዥያ ናት።
2.ኢስላማዊ በዓላት በኢንዶኔዥያ
አብዛኛው ሕዝብ ሙስሊም በሆነባት ኢንዶኒዥያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ 6ቱ ከሁሉም በላቀ ደረጃ የሚከበሩ ናቸው ። ከእነሱም ውስጥ አንድ ወር የተጾመው ረመዳን ሲጠናቀቅ ኢድ አልፈጥር የሚከበረው በከፍተኛ ድምቀት ነው። ደማቅነቱም የተገኘው “ብዙ ነገሮች ድል የተደረጉበት ነው” ከሚል ስሜት ነው።
ብዙ ወደ ከተማ ሄደው የሚኖሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው ጋር በዓሉን ለማክበር ወደገጠር ይሄዳሉ። በኢድ አልፈጥር ሁሉም ቤቶች በራቸውን ከፍተው እንግዶቻቸውን ጣፋጭ ነገሮችን ብስኩት፣ ተምር፣ ከረሜላ፣ ለስላሳ መጠጥ እያቀረቡ የሚያስተናግዱበት ደስታ የነገሠበት በዓል ነው። በዓሉ ድሆች የሚረዱበት ፤ ልጆች የበዓል ተሰጥቷቸው የሚፈነድቁበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ በመሆኑ ለኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች ከፍተኛው ፌሽታ ነው።
በኢንዶኔዥያ ብሔራዊ ኢስላማዊ ልምድ መሠረት አዲስ ዓመትም ባህላዊ ከሚባሉት በዓላት አንዱ ነው፤ በደማቅ ሁኔታም ይከበራል። ሠራተኞችም የእረፍት ቀናቸው ነው። በዓሉ የሚከበረውም ወደ መስጊድ ሄዶ ጸሎት በማድረግ ሊሆን ይችላል።
ኢንዶኒዥያውያን በተለይም የጃቫ ሙስሊም ነዋሪዎች እስልምናን በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተቀበሉት ሩዋታን (Ruwatan) የተባለ ጥንታዊ የባህል ጨዋ ታቸውን ይዘው ነው። ሩዋታን በአጭሩ ከእርግማነ መለኮት፣ ከመጥፎ አጋጣሚ፣ ጸርና አጽራር፣ ከመጥፎ ዕድል፣ ከመጥፎ አደጋ፣ በአዋቂዎች ጸሎትና በራሳቸው ላይ ፈሳሽ እየፈሰሰባቸው በመፈወስ ወይም ከእርኩስ መንፈስ በመላቀቅ የሕይወት ዘመናቸውን በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ ስሜት እንዲኖሩ ማድረግ ነው።
በዓሉ ከሂንዱ ቡድሂስቶች የተወሰደ ሥርዓት የቀጠለ ነው። ይህም ባህላዊ በዓል የኢድ አልፈጥር በዓላቸውን ያደምቅላቸዋል። ሩዋታን መከላከያው ብቻ ሳይሆን መርገምት የደረሰበትን፣ ዕድሉ የተመሳቀለበትን፣ ወዘተ ማዳን ጭምር ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሶሎ ነዋሪ ነሆኑ ኢንዶኔዥያውያን ኮቤ ኬቦዋን የተባለ የበፋለው (Buffalo=ጎሽ) ጥቁር ቀንድና ቆዳ በሰው ሠራሽ መንገድ አዘጋጅቸው ያንን ልጆችና ወጣቶች በብዛት ወደ ጎዳና በመውጣት እየተዘዋወሩ በኢድ አልፈጥርና በሙሐረም መግቢያ የሚያሳዩት ትርዕይት ነው።
ሌላውና አስደናቂው ባህላዊ ጨዋታ ትልቅ የጨርቅ ወይም ሌላ አሻንጉሊት ሠርተው እየጨፈሩ እየተደሰቱ መጫወት ነው። ኢንዶኔዥያውያን ባህላዊ በዓሎቻቸውን ደግነትን፣ ከምንም እንከን መላቀቅን፣ መጽዳትንና መዳንን “ደግነት ከራስ ይጀምረውን” የሀገራችን አባባል በተምሳሌትነት የሚጠቀሙበት እንደሆነ ይነገራል።
- የናይጀሪያውያን የሙስሊሞች
ተደራቢ በዓላት
ከናይጀሪያ ሕዝብ ግማሹ ሙስሊም ነው። የናይጀሪያ ሙስሊሞች በዋነኛነት ሁለት ኢስላማዊ በዓላት ሲኖራቸው፣ እነርሱም ኢድ አልፈጥርና ዒደል አድሃ ናቸው። በተለያዩ ሥፍራዎች የሚኖሩ ሙስሊም ናይጀሪያውያን በዓላቱን የሚያከብሯቸው በተመሳሳይ መንገድ ነው።
ኢድ አልፈጥር በናይጀሪያ የሚከበረው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ነው ። ከእነዚህ በዓላት ቀጥሎ ዱራብ (Durab Festival) የተባሉ ለብዙ መቶ ዓመታት የቀጠሉ ባህላዊ በዓላት አሏቸው። እነዚህም በዓላት ከዳውራ ኢሚሬት (Daura Emirate- የዳውራ ሱልጣኔት መሪዎች) ጋር የተያያዙ ናቸው።
ጥንት ፈረሰኞች የጦር ውጊያ ጥበብ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ትርዕይት ያሳዩባቸው ነበር። ይኸውም በሀረር አሁን ቀረ እንጂ “በርቲ በርቲ” እንደሚባለው የዱላ ምክቶሽ ብሎም የጦርና የጎራዴ ምክቶሽ ወይም ፍልሚያ የማሳያ ጥበብ ትርኢት እንደነበረው ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ ዛሬ ናይጀሪያውያን ከዒድ በኋላ ያለውን ቀን የሚያከብሩት የሰልፍ እና የጎዳና ትርኢት በማሳየት ፤ ወደ መሪዎቻቸው በመሄድ ምስጋና በማቅረብ ነው ።
በዚህ ጊዜ ፈረሶች በቀለማት የተሽቆጠቆጠ ኮርቻ፣ ግላስ ልጓም፣ ልባብ ልብስ ይለብሳሉ። ፈረሰኞቹም የባህል ልብስ ይለብሳሉ። ነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያም ይይዛሉ። ሰልፈኞች ከዚህም በተጨማሪ በነጋሪት፣ በድቢ፣ በከበሮ፣ በዜማ ይታጀባሉ። (ሀረሪዎች በሸዋል ዒድ ዕለት ኢማም አሕመድንና ልሎች ጀግና መሪዎቻቸውን በህሊናቸው ያስታውሳሉ እንጂ ይህ ትውልድ እንደሚያውቀው ጦር ሰብቀው ጎራዴ ወድረው ያንን ስሜት እንደማያከብሩ ያስታውሷል። ወደፊት ግን እንደቱሪስት መስህብ ትርኢቱን ያሳዩ ይሆናል።)
ናይጀሪያውያኑ ሙስሊሞች የሰልፍ ትርኢ ታቸውን እያሳዩ አሚሩ (ሡልጠኑ) ፊት ሲደርሱ ጎራዴያቸውን ወደላይ ከፍ በማድረግ የክብር ሰላምታ ያቀርባሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን ይኸው ትርኢት የቱሪስት መስህብ ሆኖ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ላይ ይገኛል።
ናይጀሪያውያን የነብዩ ሙሐመድ (ሰዓወ) የልደት ቀንን በብሔራዊ ደረጃ የሚያከብሩ ሲሆን አከባበሩም እንደየአካባቢው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጉዳይ ወደፊት በሚቻል መንገድ ሁሉ ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
- በዓላት በኢስላማዊቷ ፓኪስታን
ምናልባት ብዙዎቻችሁ አሳምራችሁ እንደም ታውቁት ፓኪስታን በደቡብ ኤስያ የምትገኝ 243 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት፣ በዓለም በሙስሊሞች ቁጥር ከኢንዶኔዥያ ቀጥላ ሁለተኛ ሀገር የሆነች ናት። ስለስፋቷ፣ ስለጎረቤቶቿ ሀገሮች እናንተው ፈልጋችሁ አግኙት። ለማንኛውም ፓኪስታን ከህንድ ተገንጥላ በሕዝቧ ፍላጎት ኢስላማዊ መንግሥት ያቋቋመች ብቸኛዋ ሀገር ናት። ፓኪስታን አሁን እዚህ የማልዘረዝራቸው ነገር ግን በሙስሊሙ ዓለም እጅግ የተደነቁና በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍቶችን የጻፉ፣ በዓለምም ኢስላምን ያስፋፉ ዑለማዎች ነበሯት። አሁንም አሏት። እዚያ ሀገር ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያተረፉ አስር ወይም ሃያ ኪታብ መጻፍ ብርቅ አይደለም። ያን ያህል ጻፍኩ ብሎ መኮፈስም የለም።
ለስማቸው መጥሪያ አንድ መጽሐፍ እንኳን ሳይጽፉ የሚያልፉ ዓሊሞች “አላህ ይርሃማቸው። የሰማይ ቤታቸውን ያሳምርላቸው” ተብሎ ከመሸኘት በስተቀር የአዋቂዎች አዋቂ መስለው አይታዩም። ሳይታወቀኝ ወደ ሌላ አጀንዳ ገባሁ መሰለኝ።
በዚች ሀገር ሙስሊሞች በየዓመቱ የሚያከብሯቸው በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሲኖሩ እነዚህም በዓላት የራሳቸው ጥቅም፣ የአከባበር ሥርዓት፣ ቦታና ጊዜ አላቸው። ከፓኪስታን ጥንታዊና ዘመናዊ ልምድ ጋር የተያያዙ ስለሆኑም በሙዚቃ (በመንዙማ፣ በነሺዳ፣
በዚክር፣ በጭፈራ፣ በርችት፣ ምግብ በማዘጋጀትና አብሮ በመገባበዝ፣ ልዩ ልዩ ትርኢቶችን በማሳየት የሚታሰቡ ናቸው። በፓኪስታን ከሚከበሩት ኢስላ ማዊና ባህላዊ በዓላት መካከልም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሻብ ኢ በራት Shab-e-Barat
ሻብ ኢ በራት Shab-e-Barat በዓል በብሔራዊ ደረጃ የሚከበር ሳይሆን ማክበር አለብን ብለው የሚያምኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች የሚያከብሩት በዓል ነው። በዓሉ ሻዕባን (ኢስላማዊ ወር) በገባ በ15ኛው ቀን ይከበራል። በዚህም ዕለት ሰዎች በሠሩት ስህተት በመጸጸት አላህን በጋራ ምህረት የሚጠየቅበት ነው። ምህረቱም ቁርዓን በመቅራት፣ በመንዙማ በነሺዳ፣ ይከናወናል። ነዋሪዎቹም “ሐላዋ” የሚባለው ጣፋጭ ምግብ በማምጣት ከወዳጆቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ይመገባሉ።
መላ ቺራቓን Mela Chiraghan
ይህ በዓል የብርሃን በዓል እንደማለት ሲሆን ይህም በዓል ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚከበር ነው ። የሚከበረውም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የራሆሩ ዓሊም ሽኽ ሑሴንና ገጣሚ ያለፉበትን ቀን ለማስታወስ የሚከበር ነው። ቁባቸውም ማሕዶ ላል ሑሴን ተብሎ ይታወቃል። በዓሉም የሚደረገው ላሆር በሚገኘው በሻሊማር መስክ ነበር።
በአሁኑ ጊዜ የሚከበረው ግን በ1958 በተሠራው ቁባቸው ወይም ቀብራቸው በሚገኝበት ቦታ ነው። በዓሉ ፑንጃብ ተብሎ በሚጠራው የፓኪስታን ግዛት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ የነበረው ሲሆን አሁን ግን የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል።
ጀሻን ኢ ኖውሩዝ Jashan-e-Nowruz
ይህ በዓል ከማርች 21-23 ቀን ባለው ጊዜ የሚከበር ሲሆን የአከባበር ሥርዓቱም ሆነ ማህበረሰባዊ ጠቀሜታው ከኖውሩዝ (ኢራን)፣ ከአፍጋሃኒስታን፣ ከማዕከላዊ ኤስያ ሀገራት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ይከበራል። በዚህ ዕለት በተለይም ባልቲስታንት በተባለው ሥፍራ በቤት ውስጥ በቀለም የተዋቡ እንቁላሎችን ለወዳጅ ማበርከት የተለመደ ነው።
ከቤት ውጭ ማለትም በአደባባይ ደግሞ በባህላዊ ሙዚቃ፣ ፖሎ የተባለውን ባህላዊ የስፖርት ጨዋታ በመጫወት፣ እሳት በመዝለል ይከበራል። እሳት የመዝለል ባህል ከእስልምና በፊት ማለትም በአቸሜነስና በሳሲናይድ ሥርወ መንግሥት ዘመነ ከነበረው የቀጠለ ነው ። ፓኪስታኖች በዚህ እለት አዲስ ልብስ ለብሰው መታየት የተለመደ ነው። ለሀገሪቱ እድገትና ልማት ዱዓ ይደረጋል። ሑዝና በተባለው ሥፍራ ደግሞ ከግብርና ምርት ጋር በተያያዘ መልኩ ይከበራል።
- ሀረሪዎች ሸዋል ዒድን ለምንና እንዴት ያከብሩታል ?
ለመሆኑ ሸዋል ዒድስ ምንድን ነው? ሀረሪዎችስ ይህን በዓል እንዴትና ለምን ያከብሩታል? ሸዋል ኢድ ከሌሎች ከባቢያዊ ባህሎች ጋር የተያያዘ ይሆን? ወይስ ታሪካዊ ምክንያት አለው?
በሸዋል ወር የሚከበር ልዩ በዓል ነው ። በዓሉ ባህላዊ እንጂ ሃይማኖታዊ (ሸሪዓዊ) እንዳልሆነ ሀረሪዎች ያስረዳሉ። በእርግጥም ይህ በዓል ከባቢያዊ ባይሆን ኖሮ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ እስልምናን ያስፋፉት የሀረር ሊቃውንት በሁሉም ዘንድ እንዲከበር ተጽእኖ ማድረጋቸው አይቀርም ነበር።
ይህ ጉዳይ ከትግራይ፣ ከወሎና ከጎንደር በስተቀር በሌሎች አይታይም። በነዚህ አካባቢዎችም ቢሆን በሸዋል 8ኛ ቀን ዶሮም፣ በግም፣ ፍየልም በማረድና በዱዓ ይከበራል እንጂ ሌላ የለም። በየመስጊዱም ቢሆን ከመታሰብ የላቀ አይደለም። ታዲያ ለምን በሀረር ብቻ ይከበራል ?
ጉዳዩን ከታሪክ ጋር የሚያያይዙት ሊቃውንት ሸዋል ዒድ የሚከበረው ኢማም አህመድ ኢብራሂም በሽምብራ ኩሬ ድል ያደረጉበት ዕለት እንደሆነ ያስረዳሉ። ዳሩ ግን ኢማም አሕመድ በሽምብራ ኩሬ ድል የተቀዳጁት በሸዋል 8 ቀን ነውን? ብለን ስንጠይቅ አይደለም። በመሠረቱ በድሉ ቀን የተለያዩ አስተያየቶች አሉ።
አንዳንዱ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም የሽምብራ ኩሬን ድል የተቀዳጁት እኤአ ማርች 7 ቀን 1529 ማለትም ወርሃ ጁማደል ካልአይ 935 ነው ፤ በእኛ አቆጣጠር መጋቢት 30 ቀን 1521 ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የሽምብራ ኩሬ ጦርነት ድል ማርች 11 ቀን 1529 በኛ አቆጣጠር ሚያዝያ 3 ቀን 1521 ማለትም ረጀብ 1 ቀን 935 ነው ይላሉ።
በሁለቱ አቆጣጠር ያለው ልዩነት 3 ቀን ነው። ስለሆነም ሸዋል ዒድ ከኢማም አሕመድ ጋር የሚያያዝ ከሆነ ሸዋል ወር የ4 ወራት ልዩነትን ስለሚያሳይ ድል አድርገው ወደ ሀረር የተመለሱበትን ቀን ለማስታወስ ሊሆን ይችላል።
ሌላው የሸዋልዒድ መላ ልምታ (hypothesis) ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ ዛሬ እስልምና በምሥራቅ አፍሪካ ከመስፋፋቱ በፊት በሀረርና በአካባቢዋ ባዕድ አምልኮ የሰፈነበት ሁኔታ በሰፊው እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። ዛፎች የሚመለኩበት፣ ወንዞች የሚከበሩበት፣ ጠንቋዮችና ኮከብ ቆጣሪዎች የሚመለኩበት ዘመን ነበር። አንዳንዱም አምልኮም ሰው እስከ መሰዋዕት ሊደርስ ይችላል። ለአማልክቱ መዝፈን መጨፈር፣ መገበር ግዴታ ነበር።
ይሁንና እንደዚህ ያለው ለቀቅ ያለ ባህል በኢስላም ስለማይፈቀድ መከልከል አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነም ሊቃውንቱ “ለረጅም ዘመናት የነበረው ልማድ ከከለከልን በምን እንተካው?” የሚለው ጥያቄ ማስጨነቁ የሚቀር አይመስልም። በሌሎች ሀገሮችም ጥንታዊ ነገር ግን ኢስላማዊ ያልሆኑ ልምዶችን ለማስቀረት በምትካቸው ከእስልምና ጋር የተያያዙ አዲስ ልምዶችን መተካታቸውን ከናይጀሪያ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከፓኪስታን አይተናል።
በዚህ ጽሑፍ ላይ አልቀረቡም እንጂ በግብጽ፣ በኢራን፣ በየመን፣ በቱኒዝያ፣ በሞሮኮ፣ በሴኔጋል በማሌዥያ፣ በአፍጋሃኒስታንና እና በሌሎችም ከኢድ አል አድሃና ከኢድ አልፈጥር በተጨማሪ የሚከበሩ በዓላት አሉ፡፡ ስለዚህ ጥንታዊ የሀረር አባቶች ሸዋል ኢድን አላህን እያመሰገኑ እንዲያሳልፉ ታስቦ የተደረገ ሊሆን ይችላል ፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ ሸዋል ኢድ እንደሌሎች ሀረሪዎች ረቂቅና ተጨባጭ ባህላዊ ቅርሶች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዩኔስኮ እንዲመዘገብም ጥረት እየተደረገ ነው። ለመሆን የሚያስችሉት ባህሪያት እንዳሉም ተለይተው ታውቀዋል። የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል ባህልንም እንደሚያንጸባርቅ ተቀባይነት አግኝቷል።
ማለት የሚቻለው “ሀረር ሸዋል ዒድን የማክበር የራሷ የሆነ ባህል አላት። ባህሉ የረዥም ጊዜ የታሪክ ሒደትንና ምክንያትን ተከትሎ የመጣ እንጂ በአንድ ጊዜ ዱብ ያለ አይደለም። የየዘመኑ በርካታ የሃይማኖት አባቶች አክብረውታልና የእነርሱ ይሁንታን ያገኘ ነው። ሊቃውንቱ በሀገር ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ ሀገሮች ታዋቂነትን ያተረፉ ናቸውና ምስጢሩን እነሱ ያውቁታል”።
የሀረር ሸዋልዒድ እንደቱሪስት መስህብ
በኢትዮጵያ ካሉት ከተሞች ሁሉ ረጅም ዕድሜ ማለትም 1000 ዓመት ያህል ዕድሜ ያስቆጠረችና አሁንም በእንቅስቃሴ የምትገኝ ሀረር ብቻ ናት።
* በሀረር ውስጥ 100 ያህል ሱልጣኖች፣ ኢማሞችና ዐሚሮች በጊዜ ሂደት በቅደም ተከተል መርተዋል፣
*የብዙዎቹ መሪዎች ቀብርና መታሰቢያ ተለይቶ ይታወቃል፣
*300 ያህል ቅዱሳን መቃብሮችና መታሰቢያዎች ይገኛሉ
*መቶ ያህል መስጊዶች አሉ፣
*ለዘይላዕና ለበርበራ ወደቦች ቅርብ ከመሆኗም በላይ ከነዚህ ወደቦች ጋር ያላት ትስስር ከፍተኛ ነው፣ መንገዶቹም ለቱሪዝም እጅግ በጣም ማራኪ ናቸው፣
* በርካታ አውሮፓውያን፣ ዓረቦችና የሩቅ ምስራቅ ወደ ሀረር በእግራቸውና በአጋሰሶች መጥተው ጎብኝተዋታል፣
*በዓለም ካሉት ጥንታዊ ኢስላማዊ ከተሞች አንዷና ብርቋ ናት። ብርቅነቷም እንደ ቲንባክቱና ላሙ ነው፣
*ለዓፋር ሱልጣኖችና ኢማሞች፣ ለሱማሌ ዑጋዞች፣ ለባሌና ለአርሲ ሸኾችና መሻኢኾች ዓይን ናት
*ሀረሪኮ ከአፍራን ቃሉዎች፣ አላዎች፣ ኖሌዎች፣ ጃርሶዎች ከጋራ ሙለታ ኦሮሞዎች ጋር ድርና ማግ ናት፣
*በሀረሪ ክልል ያሉ ቀበሌዎች ሁሉ ታሪካዊ ናቸው፣
*ጅጎል የተሰኘው 3 ኪሎ ሜትር ያህል ያለው ግንቧ አስደናቂ ነው።
* ታሪካዊዎቹ አምስቱ በሮቿና ወደበሮቹ የሚያደርሱ የመንገድ መስመሮቿ አስደማሚ ናቸው።
*በአጭሩ ሀረር ዙሪያዋን ማለትም ከሀረር እስከ ዘይላዕና በርበራ፣ ከሀረር እስከ ጅግጅጋ፣ ከሀረር እስከ ባሌ፣ ከሀረር እስከ አውሳ፣ ከሀረር እስ አዋሽ እየተባለ ሲገለጽ ለቱሪዝም በእጅጉ የምትመች ናት፣
*ከአክሱም ቀጥሎ የራሷ ገንዘብ የነበራትና ለአጼ ምኒልክ ሳንቲም ቀረጻ መጀመር አስተዋጽኦ ያደረገች እርሷ ናት፣
*ለኤርትራ፣ ለትግራይ ለጎንደርና ለወሎ፣ የአው አባድርና ሸኽ ሐሺም የልጅ ልጆች ሁለተኛዋ ክልላቸው ናት፣
*ከጅማ ሱልጣኔት ጋር እጅና ጓንት ናት፣
ይህች ጥንታዊ ከተማ በሀረሪዎች ልጆቿ ተጠብቆ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ሌሎች የተረሱ ባህሎቻችን ለማስታወስ፣ ለማሳደግና ለቱሪስት መስህብ ለማድረግም እጅግ ከፍተኛ ጠቃሚነት አለው፡፡
5.ማጠቃለያ
አንዳንድ ሰዎች ከዒድ አልፈጥርና ከዒድ አልአድሃ ሌላ በዓል መከበር የለበትም ይላሉ፡፡ ማስረጃቸውንም ያቀርባሉ፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ እንዲህ ባዮች ተጨማሪ በዓሎችን አለማክበር መብታቸው ነው፡፡ ሆኖም የአክባሪዎችን መብት መጋፋት የለባቸውም፡፡ በተለይም ጥንታዊ በዓላት ለኢኮኖሚውና ለማህበራዊ ኑሮው ጠቃሚ ሆነው ከተገኙ ተጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም ነው፡፡
ከተሾመ ብርሃኑ ከማል
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም