አሜሪካ ፑቲን በተኩስ አቁሙ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ ይገባል አለች

ፕሬዚዳንት ፑቲን ስለ ሰላም እንዲሁም የተኩስ አቁም ላይ ያላቸው አቋም “በሳምንታት ውስጥ” እንደሚታወቅ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ተናገሩ። ፑቲን ለዩክሬን ጦርነት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት “በወራት ውስጥ ሳይሆን በሳምንታት” ውሳኔ ላይ ሊደርሱ እንደሚገባ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተናግረዋል።

ማርኮ ሩቢዮ “ጦርነቱን ለማስቆም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው” ሲሉ በብራስልስ ከነበረው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በኋላ ገልጸዋል። የብሪታንያ እና የፈረንሳይ አቻዎቻቸው ፑቲን ስምምነቱን በማዘግየት በዩክሬን ላይ ጥቃታቸውን ቀጥለዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሶስት ዓመታት በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በሚሞክሩበት በዚህ ወቅት ሩሲያ እና ዩክሬን የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች አጠናክረዋል። ባለፈው ወር በሳዑዲ አረቢያ የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ አሜሪካ ያቀረበችውን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ዩክሬን ስትቀበል ሩሲያ በበኩሏ እስካሁን ውሳኔዋን አላሳወቀችም።

ሩሲያ እና ዩክሬን ጥቁር ባሕር ላይ የሚያደርጉትን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረማቸውን ዋይት ሃውስ አረጋግጧል። ነገር ግን ሩሲያ የጥቁር ባሕር የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው ምዕራባውያን የጣሉት ማዕቀብ ሲነሳ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ቅድመ ሁኔታዎቿን አስቀምጣለች።

ሩሲያ ይህንን ድርድር ጦርነቱን ለመቀጠል የምትጠቀምበት ስልት ሊሆን ይችላል? ተብለው ማርኮ ሩቢዮ የተጠየቁ ሲሆን እሳቸውም የትራምፕን ጦርነቱን በአስቸኳይ የማስቆም አቋምን በድጋሚ ተናግረዋል። “ሩሲያውያን ጦርነቱን ለማስቆም ያለንን አቋም ያውቃሉ። በቅርቡ ከሚሰጡት መልስ ወደ እውነተኛ ሰላም ለመምጣት ወይም የማዘግየት ዘዴ እንደሆነ ግልጽ ይሆናል” ብለዋል።

ትራምፕ “ስለ ድርድሮች ማለቂያ በሌላቸው ድርድሮች ወጥመድ ውስጥ አይገቡም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። የኔቶ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ፑቲን የተኩስ አቁም ለማድረግ እየተዘጋጁ ስለመሆናቸው ምንም አይነት ፍንጭ እንደሌለ ተናግረዋል።

ሩቢዮ ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንደሚደረግ ተስፋን እንደሰነቁ ነው። ሩሲያ የምትሰጠውን ምላሽ ተከትሎ አሜሪካ አካሄዷን እንደገና እንደምትገመግም አስረድተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You