የትራምፕ ውሳኔና የንግድ ጦርነት ስጋት

ዜና ትንታኔ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለያዩ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል። ይህ የፕሬዚዳንቱ ርምጃ ወደ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ጦርነትና የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንዳያመራ ተሰግቷል።

ማዕቀብ ለመጣል፣ ታሪፍ ለመጨመር፣ ርዳታዎችን ለማቋረጥ እና ስምምነቶችን ለመሰረዝ ፈጣን ርምጃዎችን የሚወስዱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ ከአንዳንድ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጨምሩ ሲዝቱ ቆይተዋል።

እንደዛቱትም የነጩን ቤት መንበር እንደተረከቡ ከካናዳና ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ እንዲሁም አሜሪካ ከቻይና በምታስገባቸው ምርቶች ላይ ደግሞ የ10 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ይህን ውሳኔያቸውን አንድ ጊዜ ሲያራዝሙት፣ ሌላ ጊዜ እንደገና ሲመልሱት ቆይተዋል። የታሪፍ ጭማሪ የተደረገባቸው ሀገራትም ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ አሳውቀው ተመጣጣኝ ያሉትን ርምጃ ይፋ አድርገው ነበር።

ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ በዋናነት በካናዳና ሜክሲኮ ላይ ያነጣጠረ መስሎ ቢቆይም አዲሱ የፕሬዚዳንቱ የታሪፍ ጭማሪ እቅድ በርካታ ሀገራትን የሚመለከት ውሳኔ ሆኗል። 60 ሀገራት ከፍተኛ የሚባል ታሪፍ ተጥሎባቸዋል። ለአብነት ያህል ቻይና 34 በመቶ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት 20 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል። ትራምፕ በሀገራቱ ላይ የጣሉት የታሪፍ መነሻ ምጣኔ 10 በመቶ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጣል አስታውቀዋል።

በውሳኔያቸው ‹‹በጣም ቸር›› ለመሆን መሞከራቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ሌሎቹ በሚጥሉብን ታሪፍ ልክ መጣል እንችላለን። እንዲያ ማድረግ ብችልም ያን ያህል ግን ልጎዳቸው አልፈልግም›› ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለአሜሪካ ንግድ ‹‹ነፃነት››ን እንደሚያጎናጽፍ የተናገሩለት አዲሱ እቅዳቸው አሜሪካን ተጠቃሚና በድጋሚ ባለፀጋ እንደሚያደርጋት ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ታሪፉ ሌሎች ሀገራት በአሜሪካ ምርቶች ላይ ከሚጥሉት ታሪፍ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህ የትራምፕ የታሪፍ ውሳኔ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚን በመገንባት ላይ የሚገኙት የደቡብ አሜሪካ እና የደቡባዊና ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚደርስባቸው ተገልጿል።

የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ የሀገራትና የተቋማት መሪዎች አቋማቸውን አሳውቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት ለትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል። የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊየን በሰጡት ማብራሪያ፣ አዲሱ ውሳኔ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች አስፈሪ መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ ገልፀዋል። ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ አዲስ ታሪፍ ለመጣል መወሰናቸው ለዓለም ኢኮኖሚ ትልቅ ጉዳት እንደሆነም ተናግረዋል። አውሮፓ የተቀናጀ አካሄድ እንደሚከተል ቃል ገብተው፣ ኅብረቱ በድርድር ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ምርጫው እንደሆነና እያደረገ ያለው ድርድር ካልተሳካ የአጸፋ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስጠንቅቀዋል። ‹‹ከመካከላችን አንዳችን ላይ ርምጃ ከተወሰደ ሁላችንም ላይ እንደተወሰደ እንቆጥረዋለን›› ብለዋል።

ቻይና የዶናልድ ትራምፕን እርምጃ በመቃወም ‹‹ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ቆራጥ›› መሆኗን ገልጻለች። የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር አሜሪካ ታሪፉን በፍጥነት እንድትሰርዝ የጠየቀ ሲሆን፣ ቻይና ‹‹የራሷን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት የአፀፋ እርምጃዎችን ትወስዳለች›› ብሏል።

የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ‹‹ውሳኔው ስህተት ነው›› ካሉ በኋላ፣ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ጦርነትን ላለመጀመር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል። የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው፣ ሀገራቸው ‹‹ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም ለመፍጠር ቁርጠኝነቷን ትቀጥላለች›› ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሃን ዳክ-ሶ እንዲሁ ‹‹የዓለም ንግድ ጦርነት እውን ሆኗል›› ካሉ በኋላ፣ መንግሥታቸው የንግድ ቀውሱን ለማሸነፍ የተለያዩ አማራጮችን እንደሚመለከት ተናግረዋል። ጃፓን የተጣለባትን የ24 በመቶ ታሪፍ ‹‹እጅግ በጣም ያሳዝናል›› ብላዋለች። የዓለም ንግድ ድርጅት እና የአሜሪካ-ጃፓን ስምምነቶችን የሚጥስ እንደሆነም ገልጻለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለታሪፍ ጭማሪው የሚያነሷቸው ምክንያቶች ከአደንዛዥ መድኃኒቶችና ከሕገ ወጥ ስደተኞች እንዲሁም ከንግድ ሚዛን ኢ-ፍትሐዊነት ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ሲገልፁ ቆይተዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ጎረቤቶች ካናዳና ሜክሲኮ ሕገወጥ ስደተኞችና እንደፌንታኒል (Fentanyl) ያሉ አደገኛ መድኃኒቶች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ቁጥጥር አያደርጉም የሚለውን የመረረ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ‹‹አሜሪካ በጎረቤቶቿና በሌሎች የሩቅ ሀገራት ለበርካታ ዓመታት ስትበዘበዝ ኖራለች፤ በሀገራቱና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ኢ-ፍትሐዊና አሜሪካን የጎዳ ነው›› የሚል አመላካከትም አላቸው።

ከሌሎች ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ አሜሪካውያን ሸማቾች የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ እንደሚያበረታታ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ እንዲሁም የሚሰበሰበው የታክስ መጠን እንዲጨምር እንደሚያደርግ ይከራከራሉ።

በእርግጥ አሜሪካ በዓለማችን ትልቁ የንግድ ጉድለት ያለባት ሀገር ናት። የ2023 መረጃዎች እንደሚሳዩት፣ የሀገሪቱ የንግድ ጉድለት ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው። አሜሪካ በ2024 ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በነበራት የንግድ ልውውጥ ደግሞ የ213 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አጋጥሟታል። ትራምፕ ይህንን የንግድ ጉድለት ‹‹ግፍ›› ሲሉ ጠርተውታል። በአጠቃላይ ይህ የንግድ ጉድለት የመጣው ከአሜሪካ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚላኩ ምርቶች ከፍተኛ ታሪፍ ስለሚጣልባቸው እንደሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያምናሉ። መላውን ዓለም ያስገረመውን የታሪፍ ውሳኔ ይፋ ያደረጉትም ይህን የንግድ ጉድለት ለማስተካከል አስበው ነው።

‹‹መዝገበ ቃላት ውስጥ ካሉ ቃላት መካከል በጣም የምወደውና ደስ የሚያሰኘኝ ‹ታሪፍ (Tariff)› የሚለው ቃል ነው›› ብለው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ የታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካን አምራች ኢንዱስትሪ ለመጠበቅና ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል ብለው ያምናሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው ይፋ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ለዋጋ ንረት፣ ለምጣኔ ሀብት መዳከምና ለዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት ያስከትላሉ። የታሪፍ ጭማሪው ለአሜሪካውያን ሸማቾች የምርቶች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል፤ በሌሎች ሀገራትም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይፈጥራል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You