
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ዞር ዞር ብሎ የተለያዩ አካባቢዎችን የቃኘ ሰው የት ሰፈር እንዳለ ለማወቅ ትንሽ ይቸገራል። በደረሰበት ቦታ ቆም ብሎ እዚህ ጋር የነበረው ምን ነበር ? ብሎ ለመጠየቅም ይገደዳል፤ የሚያየው እንደ ሕልምም ሊመስለው ይችላል። ጥያቄ ቢያነሳ ከራሱ ጋርም ቢወዛገብ አይፈረድበትም።
ትክክለኛውን መልስ የሚያገኘው በጣም አስተዋይ ከሆነ ተጨማሪ ምልክት ያላቸውን ጠቋሚ ነገሮች ካለው ሰው ካልሆነ በስተቀር ምናልባትም ያንን ቦታ በትክክል ሊገልጸው አይችልም። እርግጠኛ ሆኖ ለመናገርም በደረሰበት ግራና ቀኝ እያየ «አሁን የት ነን ? » ብሎ ደጋግሞ ሊጠይቅና ግራ ሊጋባም ይችላል። የኖረበት አካባቢ፣ የተመላለሰበት ሰፈር እና መንደር ሁሉ ግር ይለዋል።
በተለይም አሁን በከተማው ውስጥ በስፋት የተሰሩትን የኮሪዶር ልማት እና የወንዝ ዳር ፕሮጀክት ሥራዎችን በቅርበት ያላየና ያልተከታተለ ወይም ቆይታው ሌላ አካባቢ ሆኖ ወደ መዲናዋ ብቅ ያለ ሰው ምንም አትጠራጠሩ የሰፈሮቹን ስም እንጂ ሰፈሮቹን በትክክል ለማወቅ ይቸገራል። ይሄ መደነጋገር ታዲያ በራሴም ላይ የደረሰ ነውና ማንንም አልታዘብም።
ለካስ ከተሰራ ሀገር እንዲህ ይቀየራል እንድል ተገድጃለሁ – ያየሁትን አይቼ። ሀገሬ ሌላ ሀገር ሌላ ከተማ እስኪመስለኝ ድረስ በራሴ ጭምር ተደንቄያለሁ። በአየሁት ልማት ተገርሜያለሁ። እናም ይሄንን ማድነቅ ግድ ይላል። እንዲህ በዐይን የሚታይ፤ በእጅ የሚዳሰስ ነገር እያዩ ማየት አለመቻል ንፉግነት ይሆናል። መርፌ ሲለግም ቅቤ አይወጋም እንዲሉት አይነት ተረት። የሆነውን ሆነ የጎደለው ጎደለ ወይም ተበላሸ ይሟላ ይስተካከል ማለት ደግሞ ከሰለጠነ ማሕበረሰብ የሚጠበቅ ነው።
የማውቀው ሰፈር ያውም በቅርብ የተመላለስኩበት አካባቢ አንድ ሰሞን መስመር ቀይሬ ብቅ ስል የማላውቀው ሌላ ሰፈር ልለው በምችለው ደረጃ ሆኖ አገኝቼዋለሁ። እንደ ነገሩ እንዴት ነው ዐይን ጨፍኖ ሲገለጥ ሌላ ብዬ መደነቄን ቀጠልኩ። ወደ አያት መንገድ፣ የተባበሩት ነዳጅ ማዳያ አካባቢ፣ ወደ አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር፣ ወደ ሰሚት አቅጣጫ፤ መገናኛ በቃ እነዚህ ሰፈሮች በፊልም የማያቸው የሌላ ሀገር ከተማ እንጂ የተመላለስኩባቸው የኖርኩበት ከተማ ጭራሽ ሊመስለኝ አልቻለም። ይሄ እውነት ነው ለተጠራጠረ ሰው ደግሞ ብቅ በሉና እዩት በማለት በነጻ እጋብዛለሁ።
እርግጠኛ ሆኜ በኮሪዶር ልማቱ የተገነቡ ፓርኮቹ፣ አረንጓዴ ቦታዎቹን፣ ዎክ ማድረጊያ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር አረንጋዴ ቦታዎች፣ የሳይክል መንገዶች፣ የመንገዶቹ ውበት ስፋት፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የመብራቶቹን ድምቀት ያልገለጽኩትን ጨምሮ አይቶ ካለማድነቅ ሌላ ሊባል የሚችል ነገር የለም። የምናውቀው መንደር ሌላ ሀገር ያለን ያህል እንዲሰማን አድርጎናልና፤ የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ከማድነቅ፣ አሰሪዎቹም ከማመስገን ውጪ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም።
አብዛኛው ሰፈር ቀደም ሲል ከሚታወቅበት መልኩ ተለውጧል። ሰፋፊዎቹ መንገዶች እንደልብ ያስተላልፋሉ፤ የመኪናና የሰዎች ግፊያ በዛው ልክ ተራርቋል። እግረኛው እንደልቡ ሊተላለፍ ግድ ሆኗል። ከመኪና አደጋ ጋር ሊራራቅ ዳር ደርሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንዲሁም መኪናዬን የት ላቁም? ስፖኪዮ እበላለሁ ከሚሉ ስጋቶች የሚያላቅቅ ባለ መኪና እፎይ የሚያሰኙ በርካታ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።
ይሄ እፎይ የሚያደርገው ባለመኪኖችን ብቻ አይደለም፤ ሥራ አጥ ወጣቶችንም ባለ ሥራ ማድረግ ጀምሯል። የሚቀሩ በአሰራር የሚስተካከሉ የዋጋ ጉዳይ፣ የሕጋዊነት ጉዳይ፣ ሕጋዊ ደረሰኞችን ለተገልጋዩ የማቅረብ ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ይሆናል የሚለውን ሀሳብ እንደሚኖር አምነን አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከነችግሩም ቢሆን ይበል ያሰኛል።
ሌላው ከዚህ ቀደም ብዙም ትኩረት አግኝቶ የማያውቀው የሕጻናት መዝናኛ ሥፍራ አለመኖር ነው። የኢኮኖሚ አቅሙ ከፍ ያለው ማሕበረሰብ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ሀገር ድረስ ልጆቹን ወስዶ ያዝናናል። አቅሙ ዝቅተኛ የሆነው ማሕበረሰብ ግን ልጆች የሚጫወቱበት ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ሥፍራ አልነበራቸውም። ይህም በመሆኑ የጨዋታ ቦታቸውን የሚመርጡት በሰፈር ውስጥ አቧራ ላይ ነበር፤ አሁን ግን ይሄን ታሪክ የሚያደርጉ ሥራዎች በከተማው በተለያየ ደረጃ ተሰርተዋል።
ሕጻናትን ማዝናኛ የደከመ ሰውነትን ማሳረፊያ ከቤት ወጣ የሚባልበት የመዝናኛ ሥፍራዎች የማረፊያ ቦታዎች በአበባና ሳር አምረውና በመቀመጫና በልጆች መጫወቻ ተሟልተው ተዘጋጅተዋል። ገና አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም እንጂ የቡና መጠጫ እና የመጸዳጃ አገልግሎት መስጫ ቤቶችም እንዲሁ የኮሪዶር ልማቱ አካላት ናቸው።
ሰዎች ሞባይል ዘጋብኝ ብለው ከሞባይሎቻቸው ጋር እንዳይፋቱ በመንገድ ዳርቻ የተሰሩት የማረፊያ ቦታዎች ላይ ሞባይል ቻርጅ ማድረጊያ ሶኬቶች ጭምር ተገጥመው ማየት ችለናል። ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ትልቅ ዋጋ ያላቸው ሰዎች እንዳይጠፋፉ፤ጉዳያቸው እንዳይስተጓጎል ሞባይሎቻቸውን ለደቂቃዎች መንገድ ዳር ማረፊያ ቦታ ተቀምጠው ቻርጅ ማድረግ ይችላሉ፤ በዚህም ጊዜያዊ ችግራቸውን ይፈታሉ።
የአፍሪካ መዲና የአፍሪካ ሕብረትና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በምትባለው ከተማችን በተለያዩ ቦታዎች ይታይ የነበረው የቆሻሻ ክምር፤ በየቦታው የነበረው መጥፎ ጠረን እንኳን በእግሩ ለሚንቀሳቀስ ቀርቶ በመኪና ለሚያልፈው ጭምር አፀያፊ እንደነበር የምናስታውሰው ሀቅ ነው።
ዛሬ ከተማችን ምን ያህል ንጹህ እንደሆነች ቦታዎቹ ራሳቸው አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ፤ የተመልካችን ዐይንና ቀልብ የሳቡት እነዛ በመጥፎ ሽታ የሚታወቁት በኪሎ ሜትር ልንርቃቸው የምንፈልጋቸው የዛሬዎቹ ወንዞቻችን ናቸው። ዛሬ ወንዞቻችን አፍንጫችንን በመሀረብ ይዘን የምንሮጥባቸው አካባቢዎች አይደሉም፤ ፊታችንን አኮማትረን መጥፎ ጠረን መኖሩን ለስሜቶቻችን በምናደርስበት፤ ጉንፋን ከወዲያ ወዲህ የምንሸምትበት አካበቢዎች ከመሆን ተርፈዋል።
በተቃራኒው የመዝናኛ ሥፍራ፣ በዐይን ታይተው የማይጠገቡ ሆነዋል። አትለፉን የሚሉ የሚያስጎመጁ የሳር የአበባ የልዩ ልዩ እጸዋት መብቀያ ሥፍራ ሆነዋል። ለራሱ ጸጥታን ለሚሻ፣ ከራሱ ጋር ንግግር ማድረግ እና ማሰላሰያ ቦታን ለሚመርጥ ሰው፣ ጸሀፊ አእምሮውን የሚያሳርፍበት፣ ሀሳብ የሚያሰላስልበት ምቹ ሁኔታና ቦታ ሆነዋል።
በእነዚህ ሥፍራዎች በሥራ የደከመ ሰውነቱን ለማፍታታት በእግሩ የሚንቀሳቀስ ንጹህ አየር እየሳበ በአመሻሽ የተፈጥሮ ጸጋ ይደሰታል፤ ይደመማል፤ ይደነቃል። ተፈጥሮን የሚያይበት ስለተፈጥሮም ሆነ ሌላው የሚያጠናበት የሚመራመርበት ዕድልም ይገኛል። ለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ ምላሾችን ሰጪ ሥፍራዎች ሆነዋል -የወንዝ ዳር ቦታዎቻችን።
በአንዳንድ በተለዩና ቅድሚያ በተሰጣቸው የኮሪዶር ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች አሮጌ የሚባሉ ቤቶች ተነስተዋል። አንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎቹ እንኳን ሊኖሩበት ቀርቶ ሊመኙት በማይችሉት መልኩ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች መኖር ጀምረዋል። አዳዲስ የመኖሪያ ሕንጻዎች በፈራረሱ አሮጌና ጭቃ ቤቶች ምትክ ብቅ ብቅ ብለዋል። በአንድ በኩል ማሕበራዊ ችግሮች ፈቺ በሌላ መልኩ የከተማው ድምቀት መሆን ችለዋል። ያነሳሳናቸው ጥቂቶቹ የኮሪዶር ልማት ትሩፋቶች ናቸው።
ይህንን ሁሉ አይተን፤ ባየነው ተደንቀን እንዲሁም ታዝበን ማን ሰራው? መቼ ተሰራ? እንዴት ተሰራ ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ሁሉም ሥራ የተሰራው በየትኛውም የውጪ መንግሥት አይደለም። በእኛው ለእኛው የተሰራ መሆኑን ማወቅ ይገባል፤ ጠቀሜታውም ለእኛው ነው። መጀመሪያ በተሰራው ሥራ የሚጠቀመው ዜጋው ሲሆን ጠቀሜታውም ብዙ ነው።
ከማሕበራዊ ጠቀሜታው ጎን ለጎንም ከተማችን የተዋበች ለስብሰባም ሆነ ለጉብኝት ምቹ የሆነች ስትሆን በርከታ ቱሪስቶች ወደ ከተማችን ይመጣሉ። ከቱሪስቱ የሚገኘው ገቢ አንድም የሀገር ሀብት ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ በገቢው በሚሰራ ማንኛውም የልማት ሥራ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ራሱ የከተማው ነዋሪ ነው።
እንደ ሀገር ሲታይም የኮሪዶር ልማት ዋና እሳቤው መጪውን ሀገር ተረካቢ ትውልድን ማዕከል ያደረገ ነው። ለመጪው ትውልድ እዳን እና መጥፎ ታሪክን ሳይሆን መልካም ሀገር፣ መልካም ከተማን፣ መልካም ታሪክን ጥሎ መሄድ ነው። ትውልዱ ባሕር ማዶ ናፋቂ ሳይሆን ሀገሩን የሚወድ፤ በሀገሩ ላይ መስራትን፣ በሀገሩ ምርት መኩራትን ገንዘቡ ያደረ፤ በሀገሩ ተደስቶ በሀገሩ ኮርቶ እንዲኖሩ ምቹ መደላድል መፍጠር ነው።
ይሄ እሳቤ ደግሞ በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ የኮሪዶር ልማት በከተማም በገጠርም እንዲኖር ተደርጎ ተቀርጿል። በዚህም በርካታ ቦታዎች ከአዲስ አባባ ውጪ የኮሪዶር ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል። ሀዋሳ፣ ጎንደር፣ ባሕርዳር፣ ጅማ … ተጠቃሾች ናቸው። በዚህ ዙሪያ ያሉት ጅማሮዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው። ለዚህ ነው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አሁን ላይ ልምድ ስጡን እያሉን ያሉት።
አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ200 በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ ተሰርቷል። ሰፋፊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች ተሰርተዋል። የውሀ ፍሳሽ፣ የመብራት መስመሮች ተገንብተዋል። ቀደም በነበረው ዝናብ ዘነበ ማለት ማለት አካባቢዎቹ ሁሉ በጎርፍ ተጥለቀለቁ ማለት ነው። የእግረኛም ሆነ የመኪና መንገድ ማግኘት ከባድ ነው።
አሁን ዝናብ ሲዘንብ እንዳየነው በንጽጽር በጎርፍ ያልተጥለቀለቀው የፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎችን በመሻሻሉ ምክንያት ነው። ከዚያ ባሻገር የኮሪዶር ሥራ ፈጥሯል፤ ዜጎች ያላቸው የሀብት (አሴት) ከፍ አድርጓል። ለዐይን የሚማርክ ከተማ ፈጥሯል፤ የትራፊክ ፍሰት አሻሽሏል።
ከተማዋን ከማሳመርና ከማስዋብ ጎን ለጎንም የመኖሪያ ቤቶች ችግር በመፍታት ሂደት ትልቅ ሥራ መሰራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ብለዋል። የቤቶች ግንባታ ላይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም፤ 160 ሺህ ገደማ ቤቶች ተገንብተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት 167 ሺህ ቤት ገንብተን ለጥቅም አውለናል። የአምስት ዓመት ሥራችን ከ15 ዓመት ሥራ ሊነጻጸር ይችላል። አሁንም በመንግሥት፤ በመንግሥት እና የግል አጋርነት እንዲሁም በግሉ ሴክተር እየተገነቡ ይገኛሉ። የቤት ፍላጎታችን ሰፊ ስለሆነ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም የተገኘው ውጤት በጣም ተስፋ የሚሰጥ ነው።
ፓርኪንግ ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ፓርኪንግ በውስጥና በውጭ ተገንብቷል። ፓርኪንግ ነበረ እንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርኪንግ ማለት አስፋልት መንገዱ ማለት ነበር ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ችግር አስታውሰዋል። አሁንም በቂ አለመሆኑን አምነው ተጨማሪ ሥራ እንደሚኖር አረጋግጠዋል።
በኮሪዶር ልማት የተጀማመሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች በጎንደር፣ በባሕርዳር፣ በደሴ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋ፣ በጅማ፣ በአምቦ፣ በነቀምት፣ በአርባምንጭ፣ በሀዋሳ፣ በሶዶ፣ ከቦታ ቦታ ቢለያይም ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች አሉ። በሐረር የተሰራው የኮሪዶር ልማት ሥራ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን በትንሽ ገንዘብ ብዙ ሥራ የተሰራበት ነው።
ይሄን መልካም ተሞክሮ ወስዶ የተሻለና የበለጠ ለመስራት መነሳሳት ግን ያስፈልጋል። አሁን የተሰሩት የልማት ሥራዎችን አንድ ሁለት ብለን ብንቆጥራቸው ጅምሩ አስደሳች መሆኑን ያሳየናል። እንደ ሀገር ሲታይ ግን ተግዳሮቶቻችን ሰፊ፣ ሀብታችን አነስተኛ፣ የሚያስፈልገን ልማት ደግሞ ብዙ ነውና ያለንን አጠንክረን በልበ ሙሉነትና በቅንነት ተነስተን መስራት ይጠበቅብናል። በዚህ መልኩ መንቀሳቀስ ከተቻለ እንደ ሀገር ተመራጭ ለምሳሌነት የምትበቃ ሀገርና ታሪክ የሰራ ትውልድ መሆን እንችላለን። ይህ ደግሞ ከለውጡ የሚጨበጥ ትሩፋት የሚጠቀስ ነው።
አዶኒስ ( ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም