
አዲስ አበባ፡– በ2017 በበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የቱሪስት መስህቦችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉን የሲዳማ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ ቱሪስቶች በክልሉ የተለያዩ የቱሪስት መደረሻዎች ጎብኝተዋል።
ከጎበኙት ቱሪስቶች ሁለት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሲሆኑ፤ አንድ መቶ ሺህ ያህሉ የውጭ ቱሪስቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከዚህም ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ተደርጓል ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ አበበ እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር ሆነ፤ እንደ ሲዳማ ክልልም በደረሰኝ ገንዘብ የምንቀበልበት የቱሪስት መዳረሻ ስለሌለ፤ በዘርፉ ከሚገኘው አጠቃላይ ገቢ 99 በመቶ የሚሆነው ለንግድ ተቋማት ገቢ የሆነ ነው።
የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ በሁለት መንገድ ገቢ ይደረጋል። አንደኛው የንግድ ተቋማት ማለትም ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፤ ትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገኙት ገቢ መሆኑን ገልጸው፤ ሌላኛው የቱሪዝም ገቢ ደግሞ መንግሥት በራሱ በደረሰኝ የሚሰበስበው ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል ሃዋሳ፣ ላንጋኖ ፣ ሶደሬ እና ወንዶገነት የሚባሉ ቦታዎች ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም የሚታወቁ እንደሆኑ አውስተው፤ በእነዚህ ቦታዎች አማካኝነት ክልሉ የቱሪዝም ብራንድ ያለው በመሆኑ፤ የቱሪስት ፍሰቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የስፖርት ቱሪዝም፤ ማይስ ወይም ለስብሰባ፤ ለኤግዚቢሽን፤ ለመዝናኛ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የተለያዩ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ቅዳሜና እሁድ የዕረፍት ጊዜያቸውን በክልሉ አሳልፈው ይመለሳሉ። በቀጣይም የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ እና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም መዳረሻዎችን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምክትል ኃላፊው እንደተናገሩት፤ የኮሪዶር ልማት ባሉት የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ እሴት የመጨመር ሥራ ነው። በክልሉ የኮሪዶር ልማቱ እየተሠራ ያለው በሃዋሳ ከተማ ሲሆን፤ ይህም የከተማውን ውበት ይጨምራል፤ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እንዲስፋፉ ያስችላል።
በከተማው ውበት ላይ እሴት በተጨመረና ከተማው የበለጠ እያማረ ሲሄድ የቱሪስት ፍሰት ይጨምራል። ይህ ደግሞ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እና የሥራ እድል ፈጠራ እንዲጨምር ያስችላል። ከዚህ አኳያም የኮሪደር ልማት እንደ ሀገርም፤ እንደ ክልልም ባሉት መዳረሻዎች የቱሪስት ሳቢነታቸውን እንደሚጨምሩ ተናግረዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም