የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖችና የውጪ ተጫዋቾች ተፅዕኖ

በ2023 አፍሪካ ዋንጫ ከ24 ሀገራት 630 ያህል ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ወክለው ተሳትፈዋል። ከነዚህ ተጫዋቾች መካከል 200 ያህሉ ተጫዋቾች የተወለዱት ከአፍሪካ ውጪ ነው። ይህም በአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ናሚቢያ ብቻ ተጫዋቾቻቸው ሙሉ በሙሉ በአፍሪካ የተወለዱ ናቸው።

በዚያ አፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ ተጫዋቾች መካከል 104ቱ በፈረንሳይ የተወለዱ ናቸው። 24 ተጫዋቾች በስፔን፣ 15ቱ በእንግሊዝ፣ 13ቱ በኔዘርላንድስ፣ 10ሩ በፖርቹጋል የተወለዱ ናቸው። በዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድና በሌሎችም ከአፍሪካ ውጪ የተወለዱ ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫው ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች ተሰልፈዋል።

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ በመሆን አዲስ ታሪክ የፃፈችው ሞሮኮ ከሀገሪቱ ውጪ የተወለዱ በርካታ ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድኗ በማካተት በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ቀዳሚ ነበረች። የአትላስ አናብስት ባለፈው 2022 የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ የሆነች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ስትሆን መሠረታቸው አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ያደረጉ 18 ያህል ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኑ መካተታቸው ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው።

የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅታ ያነሳችው ኮትዲቯርን በሦስተኛው የምድብ ጨዋታ 4ለ0 በማሸነፍ አስደናቂ አቋም ያሳየችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ከሞሮኮ በመቀጠል 17 ተጫዋቾቿ የተወለዱት ከሀገሪቱ ውጪ ነው። ዲሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ በ16 ተጫዋቾች ተከታዩን ደረጃ ትይዛለች። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላቸው እንደ አልጄሪያ፣ የ2021 ሻምፒዮኗ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ኮትዲቯርና ሌሎችም በርካታ ሀገራት ወሳኝ የሆኑ በርካታ ተጫዋቾቻቸው መሠረታቸው ከአፍሪካ ውጪ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ ብሔራዊ ገንብተው እየታዩ የሚገኙ እንደ ኬፕቨርዴ አይነት ሀገራትም በውጪ ሀገራት የተወለዱ ተጫዋቾቻቸውን በመጠቀም ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ።

እነዚህ ሀገራት በውጪ የተወለዱ ተጫዋቾቻቸውን በብሔራዊ ቡድናቸው መጠቀማቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ብቅ ለማለታቸው ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው በስፖርቱ ባለሙያዎች ተደጋግሞ የተነገረና የሚያስማማ ጉዳይ ነው። ዋናው ቁም ነገር ተጫዋቾቹ በውጪ ሀገራት መወለዳቸው አይደለም። ተጫዋቾቹ የዳበረ የእግር ኳስ ባህል፣ በዘመናዊ ሥልጠናና ሳይንሳዊ መንገድ መገራታቸው ለየቡድኖቻቸው የተሻለ ነገር እንዲያበረክቱ እንዳስቻላቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ ሀገራት አንዷ ነች። በ2021 አፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ 24 ሀገራት መካከል አንድም ከአፍሪካ ውጪ የተወለደ ተጫዋች ያላካተተችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች። ለዚህም ሕገ መንግሥቷ ጥምር ዜግነት አለመፍቀዱ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ይቀመጣል።

ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባልተናነሰ በአውሮፓና ሌሎች የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ ያላቸው ሀገራት ውስጥ ተወልደው በትልቅ ደረጃ የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው። እነዚህ ተጫዋቾች በርካቶቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት ፍላጎታቸውን እንዳላቸው በተደጋጋሚ ታይቷል። ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ውጪ ያላቸውን ፓስፖርት ቀደው ለመምጣት ፍላጎት የላቸውም።

እነዚህ ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ የመጫወት ፍላጎት የሚያሳዩት ሀገሪቱ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ያሉ ታላላቅ መድረኮች ላይ ስትሳተፍ እንጂ በማጣሪያ ውድድሮች ላይ ፍላጎት የላቸውም ተብለው ይወቀሳሉ። በዚህ ሃሳብ የማይስማሙ አሠልጣኞች ተጫዋቾቹን ወደብሔራዊ ቡድኑ የመጥራትና የመመልከት ፍላጎት እንደሌላቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ።

የኢትዮጵያ ሕግና የተጫዋቾቹ ፍላጎት ለየቅል መሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ ይህን ዕድል መጠቀም እንዳልቻለ ፌዴሬሽኑ በተለያየ ጊዜ ሲገልፅ ይደመጣል። በውጪ የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከያሉበት በመመልመል ለዋልያዎቹ እንዲጫወቱ ትልቅ ጥረት በማድረግ የሚታወቀውና ለኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው ትውልደ ጀርመናዊው ዴቪድ በሻህ ግን ይህ ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ ደጋግሞ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ዕድል መጠቀም እንዲችል በሚዲያና በሌሎች የስፖርቱ ባለሙያዎች አማካኝነት ከብዙ ውትወታ በኋላ በቅርቡ በውጪ የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን መጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ጥረት እንደጀመረ ይታወቃል። ሰሞኑን በሰጠው መግለጫም ይህን ጥረቱን አጠናክሮ እንደቀጠለ ጠቁሟል።

እነዚህ ተጫዋቾች የውጪ ፓስፖርታቸውን ሳይቀዱ የኢትዮጵያን ጥምር ዜግነትም ሳያገኙ ለብሔራዊ ቡድኑ መጫወት የሚችሉበት አንድ ተስፋ ከወደ ፊፋ ተሰምቶ ነበር። ይህም ተጫዋቾች መጀመሪያ የያዙትን ፓስፖርት ሳይቀዱ በስፖርት ፓስፖርት (ስፖርት ቪዛ) የሚጫወቱበት መንገድ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በራሱ ውስብስብና አሳሪ ሂደቶች ያሉት በመሆኑ ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ተደፋፍኖ ቀርቷል።

ፊፋ 2014 ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት አንድ ተጫዋች በእናቱና በአባቱ አሊያም በአያቶቹ ኢትዮጵያዊ ከሆነና ላደገበት ሀገር ዋና ብሔራዊ ቡድን ካልተጫወተ ለኢትዮጵያ የመጫወት መብት እንዳለው ያስቀምጣል። ይህም ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ጥምር ዜግነት ለማይፈቅዱ ሀገራትና የውጭ ፓስፖርታቸውን ለመቅደድ ፍቃደኛ ላልሆኑ ተጫዋቾች ጉዳይ አሁንም መፍትሔ ሆኖ በተግባር አልታየም።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You