
በአገሪቷ ከከተማዎች መስፋፋት እና እድገት፣ ከሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ለውጥ ማሳየት ጋር ተያይዞ በአካባቢው ላይ የሚፈጠሩ ጫናዎች እየበዙ መጥተዋል። በተለይ ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ እና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እያስከተለ ያለው ተፅእኖ እየበዛ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ ደረቅ ቆሻሻ የጋረጠውን ችግር በመረዳት መንግሥት ላለፉት 18 ዓመታት ሲሰራበት የቆየውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ 513/1999 አዋጅ ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል::
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ሥራ ላይ የቆየው አዋጅ የወጣው በከተሞች የሚታየውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት ለማስያዝ ነበር። በወቅቱ የከተማ ሕዝብ ብዛት 12 ነጥብ አምስት ሚሊየን ያህል ነበር። ይህ አሀዝ አሁን ወደ 25 ነጥብ ስምንት ሚሊየን አሻቅቧል:: በ106 በመቶ እድገት ማሳየቱን ነው መረጃዎቹ ያመላከቱት።
ከሰሞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የከተማ፣ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ ሆነው ከባለድርሻ አካላት ጋር በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ላይ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ የረቂቅ አዋጁን በንባብ ያሰሙት በፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሕግ ዴስክ ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ታደሰ፤ ነባሩን አዋጅ ቁጥር 513/1999 መቀየር ካስፈለገባቸው ገፊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የሚመነጨው የቆሻሻ ማመንጨት መጠን መጨመር መሆኑን አመላክተዋል:: ነባሩ አዋጅ ይህን ችግር ለመፍታት ጉድለቶች እንዳሉበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ቆሻሻዎች በአንድ ቦታ ሲከማቹ በሚኖረው መታመቅ እና በሚፈጠረው ሙቀትና መርዛማ ጋዝ አማካኝነት የአየር ንብረት ብክለት እንዲከሰት እንደሚያደርጉ አቶ ወንድወሰን ጠቅሰው፣ ቆሻሻውን ከምንጩ መቀነስና የአያያዝና የአወጋገድ ሥርዓቱን ማሻሻል ማስፈለጉ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ እና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እያስከተለ ያለው ተፅእኖ እና ጉዳት እየተባባሰ መሆኑን አመልክተው፣ አዋጁ ይህን ችግር ለመፍታት በአዲስ መልክ ተሻሽሎ መቅረቡን ጠቁመዋል። በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ደረቅ ቆሻሻ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ውጤታማ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ አጓጓዝ፣ አከመቻቸት፣ መልሶ መጠቀም፣ እና አወጋገድ ሥርዓት መዘርጋት አስፈልጓል። የተቀናጀ እና ዘላቂነት ያለው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓት ለመዘርጋት የኅብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ማሳደግ ይገባል።
በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አገልግሎት የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች፣ ማሕበራት፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ኃላፊነት እንዲሁም ዘርፉ የሚመራበትን ሥርዓት በሕግ መወሰን ተገቢ ሆኗል::
አቶ ወንደሰን እንዳብራሩት፤ በረቂቅ አዋጁ መሰረት የልዩ ልዩ ደረቅ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ የመኖሪያ፣ የአገልግሎት መስጫ ወይም የማምረቻ ተቋማት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ተመላክቷል። ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤት ይዞታው ወሰን አንስቶ ቢያንስ እስከ 20 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት አለበት።
ማንኛውም የአገልግሎት መስጫ ወይም የንግድ ተቋም ከይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ 50 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት አለበት። ማንኛውም የአገልግሎት መስጫ ወይም የንግድ ተቋም በየፈርጁ የተለዩ ምልክት የተደረገባቸው የጉድፍ ማጠራቀሚያዎች አመቺ በሆነ ቦታ ማስቀመጥ አለበት።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከባለድርሻ አካላት የተለያዩ ግብረመልሶች እና ሀሳቦች ተነስተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ በኢትዮጵያ በርካታ የፕላስቲክ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ኢንዱስትሪዎቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም አመልክተዋል:: ዘርፉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ሊመራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
ያሚድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ወክለው አስተያየት የሰጡት አቶ መስፍን፤ ካለው ሀገራዊ ለውጥ፣ የከተሞች እድገት፣ የሕብረተሰብ አኗኗር መቀየርና ጥግግት አኳያ ሲታይ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው ብለዋል:: እያደገ የመጣው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያመነጨው ቆሻሻ እንዳለም ጠቅሰው፣ ደረቅ ቆሻሻን እንዴት ማስወገድ እና መያዝ እንደሚገባ ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማሕቀፍ መዘጋጀቱ ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል::
ከባለድርሻ አካላት የተነሱ ግብአቶች በሕጉ ተካተው ችግሩን መፍታት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመላክተዋል። ፕላስቲክን በካይ ነው በሚል እሳቤ ከመያዝ ይልቅ በአግባቡ መጠቀም ላይ እንዲተኮርም አስገንዝበዋል:: ፕላስቲክ ኢኮኖሚው ላይ ወሳኝ አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል መረዳት እንደሚገባም ገልጸዋል። በምን መልኩ በአግባቡ መጠቀም ይገባል በሚለው ላይ መሰመር እንዳለበት ተናግረዋል::
በየአካባቢያችን ከምናየቸው የቆሻሻ ምንጮች አንዱ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ረቂቅ አዋጁም ትኩረት አድርጎ የተነሳው የፕላስቲክ ብክለት መከላከልን እንደሆነም አመልከተዋል::
ከፍትህ ሚኒስቴር በመድረኩ የተገኙት አቶ በአምላኩ አንዳርጌ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ሲዘጋጅ በማርቀቁ እና አስተያየት በመስጠት ሂደት መሳተፋቸውን አስታውሰዋል። በዚህ አዋጅ አምራቾች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ፕላስቲክ አምራቾች ሲያመርቱ መልሶ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልና ሲሰበሰብ አካባቢን ሊበክል የማይችል መሆኑን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው። ያንን ባላገናዘበ መልኩ ካመረቱ ኃላፊነት አለባቸው:: ለተፈጠረው ክፍተት መክፈል እንዳለባቸው በሕጉ ተቀምጧል፤ ይህም አዲስ ጭብጥ ነው። ሕጎች ሲወጡም ነገን ማየት ያለባቸው በመሆኑ ይህም ሕግ ይህን ታሳቢ አድርጓል።
አዋጁ አጠቃላይ የደረቅ ቆሻሻን የሚመለከት ቢሆንም፣ በብዛት ያተኮረው ግን በፕላስቲክ ቆሻሻ ላይ ነው። ደረቅ ቆሻሻን ከምንጩ ዲዛይን ሲደረግ አንስቶ ምርቱ እስከሚወገድበት ድረስ ያለውን ተመልክቷል። ዝርዝር ገብቶም የፕላስቲክ ጠርሙስ፣ የውሃ ማሸጊያዎችንና የመሳሰሉትን ይይዛል። ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችንም እንዲሁም የፕላስቲክ ከረጢቶችን የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
በአንቀፅ 12 ላይ የተመለከቱት የፕላስቲክ ጠርሙስ፣ ጣሳ፣ የፕላስቲክ ውሃ ማሸጊያዎች፣ ወዘተ. የሚባሉት ይሰብሰቡ፤ መልሶ ጥቅም ላይ ይዋሉ ተባለ እንጂ እልተከለከሉም ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአንቀፅ 13 ላይ ደግሞ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ፕላስቲኮችና እነዚህም የትኛዎቹ እንደሆኑ ተመልከቷል። ይህንንም መልሶ ጥቅም ላይ የማይውል፣ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውሎ ቀጥታ የሚወገድ ፕላስቲክ መሆኑ ተብራርቷል። በዚህ መሰረት ረቂቅ አዋጁ ላይ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል የፕላስቲክ ውጤት ማምረት እንዲሁም መጠቀም መከልከሉን ማስፈሩን ተናግረዋል።
በልዩ ሁኔታ አስፈላጊ የሆኑትን ለማምረትም ባለሥልጣኑ መመሪያ የሚሰጥባቸው መሆናቸውን በሕጉ መቀመጡንም ገልጸዋል። የፕላስቲክ ከረጢት ከሆነ ግን ጥቅም ላይ ማዋል፣ ማምረት፣ ከውጭ ማስገባት አይቻልም ብለዋል።
በነባሩ አዋጅ ውፍረቱ ተልክቶ ይወሰን የነበረ ቢሆንም፣ ያ ለቁጥጥር ያልተቻለ በመሆኑ እና በተግባር መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉ አለመሆናቸው በጥናት ተለይቷል። በመሆኑም መከልከሉ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል ሲሉ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሙሉቀን ዮናስ፤ አካባቢ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ዓለም-አቀፋዊና አህጉር አቀፋዊ ችግር መሆኑንም አስታውቀዋል። ፕላስቲክ የሚያስከትለው ብክለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚነሳውን ሀሳብ ማንም ሰው ማጣጣል እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባም የሚታየውን ይህን ችግር ለመቅረፍ እና በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር ታሳቢ ያደረገው ሕግ ሲወጣ “ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ” በሚል ዋና ዋና የብክለት ርዕሶችን በመለየት ሕዝቡን የማነቃነቅ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በከተማዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ሕዝብ በአካል በማግኘት ማወያየት ተችሏል፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎቻቸውን አቅርበዋል።
በተለይ ከፕላስቲክና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በአገሪቱ እየደረሰ ያለውን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በተመለከተ ብዙ ትንታኔዎች ቀርበዋል። ይህና ከሕዝብ ውይይት ጎልቶ የወጣው ሀሳብ በዘርፉ ጠንካራ ሕግ ያስፈልጋል የሚል ስለመሆኑም ከሕዝቡ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አመላከተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀደም ሲል ተኪ ምርት ላይ የሚሰሩትን ፈልጎ ማግኘት አዳጋች እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ከፕላሰቲክ ቦርሳ ጋር ተያይዞ አዲስ ፈቃድ አግኝተው ወደዚህ ዘርፍ የገቡ 32 አምራች ድርጅቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ ባለሥልጣኑ የግል ዘርፉ በኢኮኖሚውም በአካባቢውም ያለው ሚና ከፍተኛ ሚና መሆኑን ጠቅሰዋል:: የግል ዘርፉ የበለፀገች እና ፅዱ ኢትዮጵያን ለመመስረት የላቀ ሚና ያለው መሆኑ ታሳቢ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የግሉ ዘርፍ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ እድገት እንዲያስመዘግብ፣ ከአካባቢው ሕጎች ጋር የተጣጣመ የመዋዕለንዋይ ፍሰት እንዲሁም በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ላይ የመዋዕለንዋይ ፍሰት እንዲኖር ይጠብቃል ሲሉ አብራርተዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተለያዩ ኢንሼቲቮች እንደ አገር ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የኮሪደር ልማት፣ የአረንጋዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚሉት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ሁሉ ዘላቂ የሆነ አረንጓዴ አካባቢ፣ የለማ ኢኮኖሚ እንዲኖረን ያስችላሉ:: እነዚሀ ኢኒሽየቲቮች ተግባራዊ ሲደረጉም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መነሻ ተደርጓል።
በዚህ መነሻ አንዱ እንደ አገር የገጠመው ትልቅ ተግዳሮት የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ አያያዝና አወጋገድ መሆኑን ኢንጂነር ሌሊሴ አስገንዝበዋል። የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ዋነኛ ችግሮች ናቸው በሚልም ጥናት መደረጉን ገልጸዋል:: ሥራ ላይ የቆየው አዋጅ 18 ዓመት እንደሞላው ጠቅሰው፣ በየጊዜው እየተፈጠሩ ካሉ አዳዲስ ልማቶች፣ ለውጦችና ኢንሼቲይቮች ጋር አብሮ የሚሄድ አዋጅ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የኮሪደር ልማት፣ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን፣ ባሕል በማድረግ ለትውልድ ለማሻገር፣ የግል ዘርፉም አሁን ካለበት ጫማ ወጣ ብሎ ማሰብ እንዳለበት አስታውቀው፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ማየት እንዳለበት ጠቁመዋል::
አዋጁ አካባቢን እየበከሉ ያሉት ምን አይነት ቆሻሻዎች ናቸው? ምን አይነት ችግሮች ገጥመውናል? የሚሉትን መነሻ በማድረግ እንዲሻሻል እና ነባራዊውን ሁኔታና አገራዊውን ለውጥ ያማከለ እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ፕላስቲክ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ብክለት ያስከትላል፤ በዚህም ውሃን፣ አየርን፣ አፈርን እየበከለ ነው:: በሰው ልጅ ጤና ላይ ስጋት ይፈጥራል። በተለይ የምግብና ውሃ ብክለት እንዲሁም በግብርና ምርታማነት ላይ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው። በጤና አጠባበቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ጫናን አስከትሏል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሁሉንም የፕላስቲክ ውጤቶች መከልከል እንደማይቻል አመልክተው፣ 11 በመቶ የነበረው የፕላስቲክ አጠቃቀማችን 412 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ሲሉ አብራርተዋል። በመሆኑም ሙሉ ለሙሉ ፕላስቲክን ማስቀረት አይቻልም ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በሁሉም ፕላስቲክ አምራቾች የኢአርፒ ሞዳሊቲ (Enterprise resource Planning) የፕላስቲክ አስተዳደር ሥራዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉም አመላክተዋል።
የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገር ያለችበትን የኢኮኖሚ ግስጋሴ እና የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የማኅበረሰብ ዕድገት ማዕከል ያደረገ የቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ረቂቅ አዋጅ ሆኖ ሲወጣ በከተሞች ብሎም በሀገር የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ በሚያስችል ዓውድ መቃኘት እንዳለበት አስገንዝበዋል:: መድረኩም በረቂቅ አዋጁ ላይ አስፈላጊ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ጠንካራ አዋጅ ለማዘጋጀት ታልሞ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም