
በፊቼ ጫምባላላ የሚከወኑ ጭፈራዎች፣ ባህላዊ ምግቦች፣ የአባቶች ምርቃቶች የበዓሉ ልዩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሃዋሳ ከተማ ሶሬሳ ጉዱማሌ በተለያዩ ትዕይንቶች ተከብሯል፡፡ በዓሉ በተለይም በሃዋሳ ሶሬሳ ጉዱማሌ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተገኝበት በድምቀት ነው የተከበረው፡፡
አንድ ማህበረሰብ የሚጠራበት እና የሚታወቅበት የራሱ ባህልና እሴት አለው። እነዚህን እሴቶቹን እለት ተእለት በሚያከናውናቸው ማህበራዊ መስተጋብሩ አማካኝነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፋቸዋል። አብዛኛዎቹ ባህሎቹ፣ ወጎቹና ልማዶቹ አብሮነትን ፣ አንድነትንና ፍቅርን የሚሰብኩ ናቸው ።
የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ ሥርዓትም ከእነዚህ ባህላዊ እሴቶች አንዱ ነው፡፡ ማህበረሰቡ አሮጌውን ዘመን ጨርሶ ወደ አዲሱ ዘመን ሲሸጋገር አምላኩ የፈጸመውን ጥፋቱን ይቅር እንዲለው የሚማጸንበትና መጪው ዘመን የሰላምና የፍቅር እንዲሆንለት የሚጠይቅበት ነው፡፡ በዚህ ባህላዊ ሥርዓት የሲዳማ ሕዝብ ከቂምና ከበቀል ጸድቶ፤ ሰላምና ፍቅርን አውጆ ወደ አዲሱ ዓመት ይሸጋገራል፡፡
የፊቼ ጫምባላላ ዘመን መለወጫ በዓል የሲዳማ አያንቱዎች (ትልልቅ አባቶች ) በቀደመ የክዋክብት እውቀት በመረዳት በቀን አቆጣጠራቸውና በጨረቃ ዑደቶች በመመሥረት የዘመን መለወጫ ዕለትን ይተነብያሉ። በዚህ በዓል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የመረዳዳት ባህል ጎልቶ የሚታይበት እና በረከቱ ለሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ማህበረሰቦችም የሚተርፍበት ነው፡፡
ይህ ዕለት በሁሉም የሲዳማ ዞኖችና ወረዳዎች ሲከበር በዋናነት በዋና ከተማዋ ሃዋሳ ሶሬሲ ጉዱማሌ በሕብረት በቄጣላ ( ጭፈራ ) ሥነ ሥርዓት ከንጋት አንስቶ በተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች በድምቀት ይከበራል ።
የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የባህል ታሪክና ቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞ የታሪኩን መነሻ እንዲህ ያብራራሉ ። ቀን አቆጣጠር ሥርዓቱ አባቶች የጨረቃን ዑደት በማጥናት እና ከዋክብትን በመመልከት የፍቼ ጨምባላላ ቀንን ይቆጥራሉ። ይህም በባለሙያዎች እና በምሁራን ተጠንቶ ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ እሴት ነው ይላሉ፤ የዓለም የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች እንደመዘገበውም ያስታውሳሉ፡፡
የሲዳማ ሕዝብ ይህንን ቅርስ ለዓለም ካበረከተም 10 ዓመታትን አስቆጥሯል። የጨምባላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ በየቤቱ የሚያከብረው ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ ሃዋሳ ሶሬሲ ጉዱማሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ደግሞ ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ አባቶች እና ወጣቶች ቄጣላ (ጭፈራ ) እያሰሙ ወደዚህ ስፍራ መጥተው በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡
በጫምባላላ ክብረ በዓል አስቀድሞ በርካታ የአብሮነት እሴትን የሚያንፀባርቁ ሰላምን የሚሰብኩ ሕዝቡ አንድነትን ፈላጊ መሆኑን የሚመሰክሩ ሥርዓቶች እስከ ዋዜማው እለት ይከናወናሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አዲስ ዘመን ከመግባቱ አስቀድሞ ጪሜሳዎች (የበቁ አረጋውያን) ለ15 ቀናት ያህል በመጾምና በመጸለይ አዲሱን ዓመት በሰላም ይሻገሩ ዘንድ ስለሀገራቸው፣ ስለቤተሰቦቻቸው፣ ስለ ከብቶቻቸው ይፀልያሉ። በዓሉ አንድ ሳምንት ሲቀረውም የተቸገሩ ሰዎች በዓልን ደስ ብሏቸው እንዲውሉ በማድረግ፣ የተጣሉ ሰዎች አፊኒ (ሰማችሁ ወይ) ብለው ጉዳዩን በመዳኘት እና ሀላሌ ( ሀቅን ) በማውጣት የታጣላ እንዲታረቅ ያደርጋሉ ።
የሲዳማ አባቶች ሰፎተ ቄጣላ (የጭፈራ ሥነ-ሥርዓት) ብለው አዲሱን ዓመት ሲያስረክቡ ወጣቶች ደግሞ ‹‹አዲቻ ቄጣላ›› ብለው ይረከባሉ ፣ ታዲያ በዚህ ወቅት አባቶች ወጣቶች ምን አሉ የሚለውን ይሰማሉ።
አቶ ተፈራ ሲገልጹ፤ የሲዳማ ዘመን መለወጫ የዋዜማ ዕለት ፊጣራ እና ዋናው ቀን ጫምባላላ የየራሳቸው ኩነቶች አሏቸው። በዋዜማው እለት ከስድስት ሰዓት በኋላ አዲስ ዓመት ነው ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ በፊጣራ እለት አባቶች በእርጥብ እንጨት ሁሉቃ ( መሽሎኪያ) ሠርተው ቤተሰቦቻቸውን እና ከብቶቻቸውን በዚያ በማሳለፍ አዲሱን ዓመት በሰላም መሻገራቸውን ያበስራሉ።
ሌላኛው በዋዜማ የሻፌታ ሥነ-ሥርዓት የሚባል ሲሆን ይህም ሁሉም በአንድነት ማዕድ ቀርበው የሚቆርሱበት ሲሆን በቆጮ እና በቂቤ የሚዘጋጅ ባህላዊ ምግብ ነው ። ሻፌታ ከመቆረሱ በፊት ግን አንድ ተግባር እንደሚቀድም ዳይሬክተሩ ያነሳሉ ።
በሲዳማ ባህል ኀዘን ጥልቅ ነገር ሲሆን ኀዘን መሆኑን የደረሰባት ሴት ለረጅም ጊዜ ራሷን ልትጥል ትችላለች። በፍቼ ጫምባላላ ወቅት ግን የሀገር ሽማግሌዎች ወደዚህች ሴት ቤት በመሄድ አዲሱን ዓመት በኀዘን እንዳትሻገር በቤቷ ሄደው ቅቤ እንደሚቀቧትም አቶ ተፈራ ያብራራሉ። የሻፌታ ቆረሳ ሥነ-ሥርዓቱም ወደ ጪሜሳዎች ( ወደ በቁ አባቶች ) ቤት አመሻሹን በማምራት ይከናወናል።
በሌላው ጊዜ የአመጋገብ ሥርዓት በታላላቅ አባቶች የሚጀመር አልያም በእድሜ ቅደም ተከተል የሚሄድ ሲሆን በሻፌታ ግን ሁሉም በእኩልነትና በጋራ ሆነው የሚቆርሱት ይሆናል። ይህም የፍቅር ገበታ በመባል ይታወቃል።
ቀጣዩ የጫምባላላ ቀን የደስታ እና የፌሽታ የአዲስ ዓመት ብስራት በመሆኑ ሕፃናት ከብቶች ጥበቃ ወደ ሜዳ አይሰማሩም፣ እንስቶችም የሚያጌጡበት ፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት ቀን ይሆናል።
በጫምባላላ እለት ስጋ አይበላም፡፡ ይህም የራሱ ምክንያት እንዳለው አቶ ተፈራ ያስረዳሉ፡፡ እንኳን ሰው ከብቶችም እረፍት የሚያገኙበት ዕለት በመሆኑ እርድ አይከናወንም፤ ይልቁንም ከብቶች በቂ ግጦሽ ቀርቦላቸው ጠግበው እንዲውሉ ይደረጋል። ለተፈጥሮም ተመሳሳይ እንክብካቤ ይደረጋል፤ በዚህ ቀን እንሰት አይቆረጥም፣ መሬትን በጦር መውጋት ጭምር የተከለከለ ነው።
የሲዳማ ዘመን መለወጫ በተከበረበት ዕለት የተለያዩ የኢትዮጵያውያን ብሄር ብሄረሰቦችን ባህል በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የብሄር ብሄረሰብ ሙዚቃዎችን በማጥናት ባህላዊ ሙዚቃዎች ይሠራሉ። ድምፃዊ ተስፋዬ ታዬ የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምባላላን አስመልክቶ በሠራው ሙዚቃ ተወዳጅነትን ያገኘ ነው። የሲዳማ ሕዝብ የራሱ ባህል እሴትና መገለጫዎች ያሉት መሆኑን ድምጻዊው በዘፈኑ ይገልጻል። የሲዳማ አባቶች በፊቼ ጫምባላላ ዕለት የሚያደርጉት የቄጣላ ሥነ- ሥርዓት ይበልጡኑ እንደሚማርከው ገልጸዋል። ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ ቀደምት አባቶች ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉት ሲሆን ኪነ-ጥበብ ይህንን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ሚና ያለው ነው ሲሉ ተናግረዋል ። በመሆኑም ባህሉን ከትውልድ ወደትውልድ ለማስተላለፍ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሚያደርጉት ሂደት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የሚሠሩ ዜማዎችም ትክክለኛ የባህሉን ገጽታና ትውፊቱን እንዲያስተላልፉ ሙያዊ እገዛ ማድረግ እንደሚያስፈልግና ባለሀብቶች በዚህ ውስጥ ሊሳተፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በዓለማችን የራሳቸው አቆጣጠር ያላቸው ሕዝቦች ጥቂት ሲሆኑ፤ ከጥቂቶቹም አንዱ የሲዳማ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡
የሲዳማ አያንቱዎች ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ዕውቀት በመረዳት የፊቼ ጫምባላላን ቀን የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የፊቼ ጫምባላላ በዓል የመከባበር፣ የአንድነትና የአብሮነት መሠረት ያላቸው እሴቶችን የያዘ በመሆኑ በዓሉን ለማህበረሰቦች ትስስር መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም