
የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የአሠራር ክፍተቶችን መርምሮ እንዲያቀርብ ማሳሰቢያ ተሰጠ
አዲስ አበባ፡- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመንግሥት በጀት በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ላይ 699 ሚሊዮን ብር አላግባብ ወጪ መደረጉን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ። የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶችን መርምሮ እንዲያቀርብ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክት ውል እና የሰው ሀብት አስተዳደር አፈጻጸም ውጤታማነት የ2015/16 የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ትናንት ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ እንዳሉት፤ ኦዲቱ ሲሠራ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት መጠናቀቃቸውና ዓላማቸውንም ማሳካታቸው ላይ ትኩረት ተደርጎ ተከናውኗል። በዚህም የተለያዩ ክፍተቶች እና የአሠራር ጥሰቶች ተገኝተዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማእከል ግንባታ እቅድ በ2009 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በ2013 ዓ.ም ይጠናቀቃል እንደሚል አስታውሰው፤ ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም ተቋርጧል። ይሁን እንጂ በ2012 በጀት ዓመት 46 ሚሊዮን ብር፣ በ2015 በጀት ዓመት 57 ሚሊዮን በድምሩ 104 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ተናግረዋል።
ሞዴል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ በ2009 ተጀምሮ በ2013 ለማጠናቀቅ ቢታቀድም የኦዲቱ ሥራ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ አለመጠናቀቁን ገልጸው፤ በወቅቱ ለሥራው 47 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ነበር። ሥራው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ 90 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ወጥቷል ብለዋል።
ለብሔራዊ ዳታ ማእከል ግንባታ በ2011 ተጀምሮ በ2013 ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቀሱት ዋና ኦዲተሯ፤ ለፕሮጀክቱ 255 ሚሊዮን ብር ወጪ ቢደረግበትም እስካሁን ሥራው እንዳልተጀመረ አስረድተዋል።
ነባሩን ዳታ ማዕከልን ለማሻሻል በ2011 ተጀምሮ በ2013 ለማጠናቀቅ 20 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እንደነበር አስታውቀው፤ ለሥራው 297 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ። በዚህም ከተያዘው በጀት በላይ 277 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን አፈጻጸሙ 70 በመቶ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ከላይ ለተጠቀሱት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 699 ሚሊዮን ብር አላግባብ ወጪ መሆኑን ዋና ኦዲተሯ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አልተጠናቀቁም፤ ተጀምሮ ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክት ገንዘብ ወጪ ተደርጓል፤ ላልተጀመሩ ፕሮጀክቶችም አላግባብ ወጪ እንዲወጣ ተደርጓል ያሉት ወይዘሮ መሠረት፤ በተጨማሪም በአጋር አካላት ድጋፍ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች፣ በሠራተኞች ቅጥርና መረጃ አያያዝ እንዲሁም የተቋሙን ንብረቶች ከማስመለስ ጋር የተያያዙ ከፍተቶች ተስተውለዋል ነው ያሉት።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰው ሀብትና የንብረት አስተዳደር ሂደቱ ደካማ ነው ያሉት ወይዘሮ መሠረት፤ ከሕግ አግባብ ውጭ የተከፈሉ ክፍያዎች እና ለተስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶች ላይ ላይ በፍጥነት የርምት ርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
ባለድርሻ አካላት የቀረበውን ኦዲት መነሻ አድርገው ተጠያቂነትን ለማስፈን መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ ተቋሙ ሠፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ በመሆኑ በሥራ ሂደት ክፍተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። የቀረበውን የኦዲት ግኝት መነሻ በማድረግ የተለያዩ የማስተካከያ ርምጃዎች ተወስደዋል። በቀጣይነትም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንሠራለን፤ የድርጊት መርሐ ግብር በማዘጋጀት እና የተወሰዱ ርምጃዎችን በማካተት ለቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ እናቀርባለን ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም ባንክና ከአጋር አካላት ጋር የሚሠሩ ሥራዎች በአይነትና በቁጥር በርካታ መሆናቸውን አመላክተው፤ በዚህ መነሻ የተስተዋሉ የኦዲት ክፍተቶችን ለማረም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
በጀት ተይዞላቸው የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን የአፈፃፀም ክፍተት ለመፍታትና የሳይንስ ማዕከላት ያለባቸውን ውስንነት ለመቅረፍ ይሠራል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህን መነሻ በማድረግ ያሉ ክፍተቶችን በመገምገምም ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በሰጡት ማጠቃለያ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ከመግባታቸው በፊት የቅድመ አዋጭነት ጥናት እንዲሁም ግምገማ ተደርጎላቸው እንዲከናወኑ አልተደረገም ብለዋል።
በመንግሥት በጀት፣ በዓለም አቀፍ ድጋፍና ብድር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከበጀት አኳያ የትግበራ ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸው ለምክረ ሃሳብ ለሚመለከታቸው አካላት አለማቅረቡ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልፀዋል።
ለትራንስፖርት ኪራይ፣ ለዳታ ማዕከል ግንባታ፣ ለሳይንስ ካፌ፣ ለሠራተኛ ደሞዝና ለመሳሰሉ ወጪዎች ከሕግ አግባብ ውጪ የወጣውን ወጪ ኦዲት በማድረግ በአፋጣኝ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ለተገኘበት የበጀት ጉድለት መንስኤ የሆኑ የአሠራር ሂደቶችን በማረምና ለጉድለቱ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ አሳስበው፤ የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶችን መርምሮ እንዲያቀርብ፤ በዚህ ሂደትም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም