
አዲስ አበባ፡– መላው የትግራይ ሕዝብ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ገጻቸው ላይ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በደንብ ቁጥር 533/2015 አንቀፅ 3(2) መሠረት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትን መሾም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት እንደሆነም ተገልጿል። ጥቆማውንም በኢሜል info@pmo.gov.et መስጠት እንደሚችሉም ተመልክቷል።
በፌዴራል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 62(9) እና አዋጅ ቁጥር 359/1995 የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ መግባት፣ በፕሪቶሪያ ስምምነትና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 533/2015 መሠረት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሁለት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15(3) መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቆየው ለሁለት ዓመታት ብቻ ነው። ነገር ግን ትክክለኛ ምክንያት ካለ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል አመልክተዋል።
ከላይ በተጠቀሱት ሕጎችና በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራውን በሁለት ዓመት ውስጥ አጠናቅቆ ኃላፊነቱን ለሕዝብ ለተመረጠው መንግሥት ማስረከብ እንደነበረበት አንስተው፤ ይሁን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁልፍ ተግባራቶቹን በወቅቱ ማከናወን አልቻለም ብለዋል
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁልፍ ተግባራቶቹ መካከል አንዱ ቁልፍ ተግባር ለምርጫ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ተግባር ካልተጠናቀቁ ተግባራት ውስጥ አንዱ ሲሆን የሕግ ማሻሻያ በማድረግ የጊዜያዊ መንግሥት የሥልጣን ጊዜን ለአንድ ዓመት ማራዘም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የጊዜያዊ መንግሥቱን የሥልጣን ዘመን በማራዘም ላይ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት መሾም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸው፤ በደንብ ቁጥር 533/2015 አንቀፅ 3(2) መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትን መሾም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ሕዝቡ በተሟላ መንገድ በምርጫ መሪዎቹን እስኪመርጥ ድረስ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ተሳትፎ እንዲኖረው አስፈላጊ በመሆኑ የጊዜያዊ አስተዳደር ተግባራት በብቃት የሚወጡና የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ይችላሉ ብላችሁ የምታምኑዋቸውን እጩዎች ከመጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እጩዎቻቸውን ከዚህ በታች ባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኢሜል መላክ ትችላላችሁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም