
ፍልስጤማዊው የኦስካር ተሸላሚ ሐምዳን ባላል በይዞታ ሥር ባለው ዌስት ባንክ በእስራኤል ወታደሮች መያዙን ፍልስጤማውያን የመብት ተሟጋቾች ገለጹ። አካባቢውን በይዞታ በተቆጣጠሩ እስራኤላውያንና በፍልስጤማውያን መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ነው በእስራኤል ወታደሮች የተያዘው።
‘ኖ አዘር ላንድ’ የተባለውና በቅርቡ ኦስካር ያሸነፈው ፊልም አዘጋጅ ከሆኑ አራት ፊልም ሠሪዎች አንዱ የሆነው ሐምዳን ቤቱ ሱስያ በተባለው መንደር ጥቃት እየደረሰ ባለበት ወቅት የፊልም ሠሪው ቤት በእስራኤላውያን ሰፋሪዎች መከበቡን አምስት አይሁዳዊ አሜሪካዊ የመብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።
ከፊልሙ ዳይሬክተሮች አንዱ የሆነው ዩቫል አብርሃም እንዳለው ሐምዳን ባላል ድብደባ ተፈጽሞበታል። አምቡላንስ ውስጥ ሳለም በወታደሮች ተወስዷል። እስራኤል ግን ይህንን አስተባብላለች። የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሐምዳንን በስም ባይጠቅስም፣ ሦስት ፍልስጤማውያን እና አንድ እስራኤላዊ የፀጥታ ኃይሎች ላይ “ድንጋይ በመወርወር” ተጠርጥረው ተይዘዋል ብሏል፡፡
አምስቱ አይሁዳዊ አሜሪካውያን የመብት ተሟጋቾች እንዳሉት፣ ማስክ ያጠለቁ ሰፋሪዎች በሱስያ መንደር ጥቃት ከፍተዋል። የመብት ተሟጋቾቹ ክስተቱን ለመሰነድ ወደ መንደሩ ሲሄዱ እነሱም በዱላ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ ጥቃት እንደደረሰባቸውና ሰፋሪዎቹ የመኪናቸውን መስኮት እንደሰበሩ ገልጸዋል።
የሐምዳን ቤት በሰፋሪዎች ተከቦ እንደነበር ፊልሙን ከሠሩት አንዱ የሆነው እስራኤላዊው አዘጋጅ ዩቫል አብርሃም ተናግሯል። ሰዎች እንደተጎዱና ንብረት እንደወደመም ገልጿል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል በቦታው መድረሱን አረጋግጦ በፀጥታ ኃይሎች ላይ “ድንጋይ ተወርውሯል” ብሏል።
“ድንጋይ በመወርወር የተጠረጠሩ ሦስት ፍልስጤማውያንና አንድ ተሳታፊ የነበረ እስራኤላዊ ተይዘዋል። በእስራኤል ፖሊስ ምርመራ ሊደረግባቸው ተወስደዋል። እስራኤላዊው ጉዳት ስለደረሰበት ወደ ሕክምና ተወስዷል” ብሏል።
‘ኖ አዘር ላንድ’ የተባለው ፊልም በ97ኛው አካዳዊ አዋርድ ላይ ምርጥ ዘጋቢ ፊልም ተብሎ ተሸልሟል። ፊልሙ ማሳፍር ያታ በተባለው አካባቢ ያለውን ግጭት ያሳያል። ቦታው 20 መንደሮችን የያዘ ነው። ፊልሙ በፍልስጤማዊውና እስራኤላዊው ፊልም ሠሪ መካከል ያለውን ጓደኝነትም ያሳያል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም