በሰመር ካምፕ 184 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተገኝተዋል

አዲስ አበባ፡– ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰመር ካምፕ 184 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማግኘት መቻሉ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰመር ካምፕ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰመር ካምፕ 184 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

‹‹እስኪል ኢትዮጵያ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የሰመር ካምፕ በክህሎት ውድድር ያሸነፉ ጀማሪ የፈጠራ ቢዝነሶች/ስታርትአፖች/ ወደ አንድ ማዕከል ወደ ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት እንዲመጡ የሚደረግ መሆኑን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማዕከሉ የመኝታ አገልግሎትና ሌሎች አገልግሎቶችን ጭምር እያገኙ ክህሎታቸውን የሚያዳብር ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የፋብሪካ ጉብኝት ያደርጋሉ፣ የፈጠራዎቻቸውን የማሻሻል ሥራዎችንም ይሠራሉ። ተቀራራቢ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች የማቀራራብ ሥራ ተሠርቶ እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።

መጀመሪያው ዓመት በ2016 በጀት ዓመት ወደ ማዕከሉ የመጡ 85 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸው ጠቅሰው፤ በሁለተኛ ዓመት በ2017 በጀት ዓመት እንዲሁም 99 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማግኘት የተቻለ መሆኑን አመልክተዋል።

እነዚህ 184 የፈጠራ ሥራዎች ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በጥብቅ መስፈርት ልየታ አልፈው ወደ ማዕከሉ የገቡ ናቸው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተቀመጠላቸው የተለያዩ ደረጃዎች መሠረት ደረጃዎችን ጠብቀው የሚሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የመጀመሪያውን የሥልጠና፣ የኢንዱስትሪ ጉብኝት፣ የልምድ ልውውጥ፣ ቢዝነስ እቅድ ማዘጋጀት፣ ዲዛይኖችን የማሻሻልና የመሳሳሉት ደረጃዎች ማለፍ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ካለፉ በኋላ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ወደ ማምረት ይሸጋገራሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የሚሠሩትም ቴክኖሎጂዎች በአምስቱ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ምሰሶዎች በሚባሉ ዘርፎች ከግብርና፣ ከቱሪዝም፣ ከማዕድን፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ የሚሄዱ መሆናቸውን ብሩክ(ዶ/ር) አመልክተዋል።

ግብርናው እና ሌሎችንም ዘርፎች የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂ መሥራታቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ብዙ አይነት ፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎቹ በአሁኑ ጊዜ የፋይናንስ ድጋፍ ፍለጋ ያሉ እንዳሉ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የፋይንናንስ ድጋፍ ያገኙት ደግሞ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ክልሎች ትዕዛዝ ተሰጥቶቸው በብዛት እያመረቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከልም አንዱ መስኖን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ከመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንዲባዙ የተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዳንድ ቴክኖሎጂዎች ለማባዛት ፍላጎት ያላቸው ክልሎች ትዕዛዝ የሰጡ መሆኑን አመላክተዋል።

ሁሉንም ቴክኖሎጂ በብዛት ወደ ሥራ ለማስገባት የፋይናንስ አቅርቦት ማነቆ መሆኑንም ጠቁመው፤ እነዚህ አዲዲስ ቴክኖሎጂዎች የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው ወደ ማምረት ሥራ ከገቡ በኋላ በግላቸው አቅም እየፈጠሩ ወደ ኩባንያ ደረጃ የሚያድጉበት መሆኑን አስታውቀዋል።

ቴክኖሎጂዎቹ በማዕከሉ ለአጭር ጊዜ፣ ለአንድ ዓመትና እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊቆዩ እንደሚችል ጠቅሰው፤ የሚቆዩ የጊዜ ገደብ በሚያገኙት የድጋፍ ማዕቀፍ የሚወሰን መሆኑን አመልክተዋል።

የፈጠራ ሥራዎች ለመደገፍ ከሚያገጥማቸው ማነቆዎች መካከል ዋነኛው የፋይናንስ አቅርቦት ነው ያሉት ዋና ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ረገድ የሀገራችን ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ጀማሪ የፈጠራ ቢዝነሶች /ስታርትአፕ/ ለመደገፍ የሚያደርጉት ጥረቶች ቢኖሩም በቂ አይደሉም ብለዋል።

የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን እያሰፋን ካልሄድን አንደኛ በቴክኖሎጂ ራሳችንን መቻል አንችልም። ሁለተኛ ደግሞ በሀገር ውስጥ በቀላሉ መሥራት የሚቻሉ ምርቶች ከውጭ እያስመጣን የምንዘልቀበት ይሆናል። የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መፍታት እስካልተቻለ ደረስ ውጤት ማምጣት አንችልም የሚል እምነት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

‹‹እስኪል ኢትዮጵያ›› የተሰኘው እንቅስቃሴ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን ወደ ክልሎች እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You