እስራኤል እና ሃማስ አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ለማድረግ ተስማሙ

ሃማስ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ከሁለት ቀናት በፊት በግብፅ እና በኳታር የቀረበለትን ምክረ ሃሳብ መቀበሉን የቡድኑ ከፍተኛ መሪ አስታወቁ። የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ፣ አደራዳሪዎች ባቀረቡት ሃሳብ መሠረት በጋዛ የተኩስ አቁሙ እንዲቀጥል አምስት እሥራኤላውያን ታጋቾችን ለመልቀቅ እና ለ50 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚል የቀረበውን ሃሳብ እንደሚደግፍ ገልጿል።

ከጋዛ ውጭ የሚገኙት ከፍተኛ የሃማስ መሪ፣ ካሊል አል-ሀያም ቡድኑ በግብፅ እና በኳታር አደራዳሪዎች የቀረበውን ረቂቅ ምክረ ሃሳብ ማፅደቁን ተናግረዋል። ሮይተርስ የደኅንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ግብፅ አዲሱን የተኩስ አቁም ስምምነት በተመለከተ ከእሥራኤል ወገን በጎ ምላሽ አግኝታለች።

የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት እቅዱን እንደተቀበለው ገልፆ “ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበር ለአደራዳሪዎቹ ሌላ ምትክ ምክረ ሃሳብ” ማቅረቡን ገልጿል። ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች ከተስማሙ አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ እሁድ ከሚጀመረው የሙስሊሞች የዒድ አልፈጥር በዓል ጋር ሊገጣጠም ይችላል።

ቅዳሜ ዕለት የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ከአደራዳሪዎቹ ጋር የተኩስ አቁም ሃሳብ ላይ ምክክር መደረጉን አስታውቋል። እስራኤል ያቀረበችው ምትክ ምክረ ሃሳብ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት እንደተደረሰበት ቢገለጽም፣ ምን ምን ሃሳቦች እንደተካተቱበት የተባለ ነገር የለም።

አሜሪካ በጉዳዩ ላይ በይፋ አስተያየት አልሰጠችም። እአአ ጥር 19 በሥራ ላይ የዋለው የተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ወር መጀመሪያ ካበቃ በኋላ የእሥራኤል ኃይሎች በራፋ በእግረኛ ጦር ዘመቻ ሲጀምሩ፣ በጋዛ ሰርጥ ደግሞ የአየር ድብደባ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ሁለቱም ወገኖች የመጀመሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ ሁለተኛው ዙር ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል። ሃማስ በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ምዕራፍ 33 ታጋቾችን ለቋል። በኢራን የሚደገፈው ቡድኑ አሁንም 59 እስራኤላውያን በቁጥጥሩ ስር ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሁሉም በሕይወት ይኖራሉ ተብሎ አይታመንም።

ሃማስ ቀደም ሲል መጀመሪያ ላይ ቀርቦ በነበረው መደራደሪያ ሃሳብ መሠረት ሁለተኛው የድርድር ምዕራፍም እንዲቀጥል በመጠየቅ፣ የተቀሩት ታጋቾች ሙሉ በሙሉ እንዲለቀቁ የእሥራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቅቆ እንዲወጣ እና ጦርነቱን እንዲቆም ጠይቆ ነበር። ነገር ግን እነዚያ ድርድሮች ሊካሄዱ አልቻሉም።

እሥራኤል እና አሜሪካ በምትኩ ከአንድ ወር በፊት ያበቃው የተኩስ አቁም የመጀመሪያው ምዕራፍ እንዲራዘም ሃሳብ ቢያቀርቡም ጦርነቱ እንደሚያከትም ግን ግልጽ ዋስትና አልተሰጠም። እሥራኤል ሃማስን የተኩስ አቁሙ እንዲራዘም የቀረበውን ሃሳብ አልቀበልም ብሏል ብላ በመወንጀል እአአ ከመጋቢት 18 ጀምሮ በጋዛ ላይ የአየር ድብደባዋን ቀጥላለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእሥራኤል በደረሰ የአየር ጥቃት ከ900 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀሩት ታጋቾች ቤተሰቦች ኔታንያሁ የተኩስ አቁምን በመጣስ የታጋቾችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ሲሉ ከሰዋል። ከእነዚህ ታጋቾች መካከል አንዱ የሆነው ኤልካና ቦህቦት እንዲፈታ ሲማፀን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ሃማስ ይፋ አድርጓል።

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ይህ ጦርነት የተቀሰቀሰው፣ እአአ ኦክቶበር 7 ቀን 2023 እአአ ሃማስ ደቡብ እሥራኤልን ካጠቃ በኋላ ሲሆን፣ በዚህ ጥቃት አንድ ሺህ 200 ያህል ሰዎች ሲገድሉ እና 251ዱን አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል። እሥራኤል በበኩሏ በወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ከ50,000 በላይ ፍልስጤማውያንን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስታወቁን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You