
እሁድ አመሻሽ እሥራኤል ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ባደረሰችው ጥቃት ነባር የሃማስ አመራር እና ረዳታቸው መገደላቸውን ሀማስ ለቢቢሲ ገለጸ። በኻን ዩኒስ ግዛት ናስር ሆስፒታል ላይ በደረሰው ጥቃት የሀማስ የፋይናንስ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ኢስማኢል ባርሁም መገደላቸው ተሰምቷል።
ግለሰቡ ከአራት ቀናት በፊት በእሥራኤል ጥቃት በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት በሆስፒታሉ ሕክምና እያገኙ እንደነበር የሀማስ ባለሥልጣናት የገለጹ ሲሆን የእሥራኤል ጦር ኃይል በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቁልፍ የሀማስ ሰው ላይ የተሳካ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።
ጦር ኃይሉ ከባድ የመረጃ ማጠናከር ካደረገ በኋላ በፈጸመው ጥቃት ነጥሎ የሚመታ መሣሪያ እንደተጠቀመ አሳውቋል። በሀማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳለው በጥቃቱ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳውቋል። ሚኒስቴሩ አክሎም በጥቃቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የሆስፒታሉን ክፍል ሠራተኞች ለቀው ከአካባቢው እንዲርቁ መደረጉን ገልጿል።
ቢቢሲ ማጣራት የቻለው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው ከሆነ ከጥቃቱ በኋላ በስፍራው የነበሩ ሰዎች እሳቱን ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ታውቋል። እሥራኤል በተደጋጋሚ ሀማስ ሆስፒታሎችን በመሸሸጊያነት ይጠቀማል እንዲሁም ለጦር መሣሪያ ክምችት እና ለዕዝ ማዕከልነት ይጠቀምባቸዋል ስትል ብትወቅስም ሀማስ በበኩሉ ይሄን የእሥራኤልን ወቀሳ እንደማይቀበለው ነው የገለጸው።
እስራኤል በኻን ዩኒስ እሁድ አመሻሽ በፈጸመችው ጥቃት ሌላኛው የሀማስ አመራር ሳላህ አል ባርዳዊል መገደላቸውን የሀማስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የጤና ሚኒስትሩ እንዳለው በኻን ዩኒስ እና ራፋህ እሁድ ጥዋት በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰላሳ የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ አመሻሹን ደግሞ በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
እሥራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ባለፈው ማክሰኞ ድጋሚ ጀምራለች። ይህም ለሁለት ወራት ያክል የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በጋዛ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።
እስራኤል በዩናይትድ ስቴትስ የቀረበውን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት አልቀበልም ብሏል ስትል ሀማስን የወቀሰች ሲሆን ሀማስ በበኩሉ እሥራኤል ዋናውን የተኩስ አቁም ስምምነት አፍርሳለች ሲል ይወቅሳል። በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው የወቀሳ እንካ ሰላምታ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሽሮ ለዳግም ጦርነት መንገድ መክፈቱ አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል። ማባሪያ ያጣው የንጹሓን ሞት በተኩስ አቁም ስምምነቱ እልባት ያገኛል የተባለ ቢሆንም አንዱ አንዱን ተጠያቂ በማድረግ ቅቡልነት ማጣቱ እየተገለጸ ይገኛል። ለዓመታት በሁለቱ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ጦርነት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በርካቶችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በእስከ አሁኑ ፍልሚያ ሀማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሁለት መቶ ሀምሳ ሦስት ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወቃል። እሥራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከአርባ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከዚያው ጤና ሚኒስትር የተገኘ መረጃ ሲያሳይ ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸው በሀማስ አስተዳደር ስር ካለው ጤና ሚኒስትር የወጣው መረጃ አመላክቷል።
እሥራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንፃ መውደሙን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁ አይዘነጋም። መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም