ኅብረቱ በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለፀ

የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በሶማሊያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሐመድ ዓሊ ዩሱፍ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ውይይቱን አስመልክተው የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በኤክስ ገፃቸው እንዳስታወቁት÷ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል፡፡

ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በሞቃዲሾ ያደረጉት ሊቀመንበሩ፤ የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል። ሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መሥራች እና አባል ሀገር እንደመሆኗ፣ ለአህጉራዊ አንድነት፣ አብሮነት እና የባለብዙ ወገን ትብብሮች ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በሞቃዲሾ ጉብኝት በማድረጋቸው አድናቆታቸውን ገልጸው፤ በሶማሊያ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና ማቅረባቸውን ኬቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ ሞሐመድ ዓሊ ዩሱፍ ወደ በሶማሊያ የተሰማራውን የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የጎበኙ ሲሆን፤ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ የሶማሊያን ሰላም ለመመለስ በርካታ መስዋዕትነት መክፈሉን አንስተዋል፡፡

ኅብረቱ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ተልዕኮውን ለመፈፀም በሚንቀሳቀስበት ወቅት የሚያጋጥሙትን ችሮች ለመፍታት እና የሠራዊቱን አቅም ለማጎልበት ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You