ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኅብረተሰቡን ሊጎዱ የሚችሉ ምርቶችን አስወገደ

አዲስ አበባ፡- ከ655 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ኅብረተሰቡን ሊጎዱ የሚችሉ ምርቶች ማስወገዱን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሸበላው ተገኝ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ምርቶቹ በሽያጭ ላይ ሆነው የተገኙት በክፍለ ከተማው ወረዳ 7 ሸማቾች ማኅበር ውስጥ በተለያየ ቀጣና ባሉ 5 የሸማቾች ሱቆች ነው፡፡ ምርቶቹም ወደ 26 የሚደርሱ ሲሆን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው፣ ምንም ዓይነት የመጠቀሚያ ጊዜ ያልተጻፈባቸው፣ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ደረጃ ያልተሰጣቸው እንዲሁም በአያያዝ ጥንቃቄ ጉድለት በአይጥና በሌሎች ተባዮች የተበሉ ናቸው ብለዋል፡፡ የተወገዱት ምርቶች በጥቆማ የተገኙ ሲሆን መረጃውን የሰጡትም የክፍለ ከተማው ንግድ ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች መሆናቸውን አመልክተው፤ በተጨማሪ ‹‹እኔም ለጤናዬ ባለሥልጣን ነኝ›› በሚል መሪ ቃል በክፍለ ከተማው የተቋቋመው የቁጥጥር ፎረምም ምርቶቹ ላይ የማጣራት ሥራ እንዲሠራባቸው ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት በጽሕፈት ቤቱ በኩል መረጃዎችን በማሰባሰብ የምግብ ተቋማት የባለሙያዎች ቁጥጥር ቡድን በማዋቀር በቦታው እንዲገኝ በማድረግ በወረዳ 7 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ከሚመራ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን ክትትል ተደርጓል፡፡ የክትትል ግብረ ኃይሉ ባለድርሻ አካላት ደግሞ የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት፣ ንግድ ጽሕፈት ቤት፣ አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት፣ ኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት፣ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት እና ፖሊስ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በክትትሉም ሸማቹን ኅብረተሰብ ሊጎዱ የሚችሉ ግምታዊ ዋጋቸው 655 ሺህ 225 ብር የሆኑ 26 ያህል ምርቶች ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግምታዊ ዋጋቸው 76ሺህ 500 ብር የሆነ 17 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት፣ 48 ሺህ ብር የሚወጣ 4 ኩንታል የስንዴ ዱቄት እና 252ሺህ 703 ብር የሚያወጣ አራት የተለያየ መጠን እና ስም ያላቸው ደረቅ ሳሙናዎች በክትትሉ ተገኝተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 386 ሊትር 3 ዓይነት መጠን ያላቸው ፈሳሽ ሳሙናዎች እና 534 ኪሎ ግራም የሻይ ቅጠል እንዲሁም ሌሎች 26 የሚደርሱ ምርቶች መገኘታቸውን ሥራ አስኪያጁ በዝርዝር ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም እነዚህ ምርቶች ግብረ ኃይሉ በተገኘበት እንዲታሸጉ ከተደረገ በኋላ ወረዳው በአዘጋጀው መጋዘን በማከማቸት መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የወረዳው የአካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ባሰናዳው ሥፍራ እንዲወገዱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

አቶ ሸበላው ተገኝ ሸማቾች አንድ ምርት ሲገዙ የአገልግሎት ጊዜው ያላለፈበት መሆኑን እንዲሁም የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ደረጃ የተሰጠው መሆኑን አስተውለው በማረጋገጥ በመግዛት የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ጤንነት መጠበቅ አንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም የክፍለ ከተማውም ሆኑ የከተማው ነዋሪዎች በሰው ጤና ላይ ችግር ይፈጥራል ብለው የሚጠራጠሩት ምርት ሲያጋጥማቸው በአካልም ሆነ በ8864 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል የተለመደውን የጥቆማ ትብብር በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You