የአፍሪካውያን የመደጋገፍና ችግሮችን የመፍታት ጉዞ ማሳያ

ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ የመረዳዳትና ለጉርብትና ቅድሚያ መስጠት ከጥንት ጀምሮ ያጎለበተችው መልካም እሴት ነው፡፡ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት በተለያዩ ሀገራት የሚከፍሉት የሕይወት መስዋዕትነት ቀዳሚ ቢሆንም በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም ችግሮች በተከሰቱ ጊዜ እጆቿን ለርዳታ እንደማታጥፍ ከታሪክ ድርሳናት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ ለተለያዩ ሀገራት ያደረገችው የሰብዓዊ ድጋፍና ጦሯ በኮንጎ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮሪያ እንዲሁም በላይቤሪያ በመዝመት ሰላም ለማስከበር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ዲፕሎማቶች ይገልጻሉ ፡፡

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወቅት የኮቪድ ስርጭትን መግታት የሚያስችላት 17 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን የሕክምና ቁሳቁሶችን ለደቡብ ሱዳን ርዳታ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል የመንገድ መሠረተ ልማት ማሳደግ የሚስችል ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የ738 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ብድር መስጠቷም የሚታወስ ነው፡፡

ጎን ለጎንም ለጎረቤቶቿ ነፃ የትምህርት ዕድል ትሰጣለች፡፡ ይህም በቀጣናው በአካዳሚክስ ዘርፉ ያሉ ውስንነቶች ለመቅረፍ ቀላል የማይባል ሚና እንደሚጫወት ለመገመት አያዳግትም፡፡ በመሠረተ ልማት ረገድም ለጅቡቲ፣ ለኬንያ፣ ለደቡብ ሱዳንና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኃይል ማዕከል ለመሆን መንገድ ጠራጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ከመንገድና ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በተጨማሪ ከ20 እስከ 30 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በየቀኑ ለጅቡቲ እያቀረበች እንደምትገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጥር 2016 ዓ.ም ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡የተጀመሩ የውሃ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በየቀኑ 100 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ለጅቡቲ የንፁሕ መጠጥ ውሃ ማቅረብ የሚያስችሉ መሆኑ ተመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገች ሲሆን በቅርቡም በጦርነት ለምትታመሰዋ ሱዳን የ15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡ በተለይ አሁን ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) መቋረጥ በአፍሪካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ባለበት ጊዜ መሆኑ ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያግዝ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሑራን ያስረዳሉ፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሑር ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ‹‹ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚለው መፈክር የቆየ ቢሆንም አሁን በኢትዮጵያና በሌሎች ሀገራት የተጀመረው ውጥን ተስፋ የሚሰጥ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ እንዲሁም አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ለሱዳን ሕዝብ መረጋጋትና ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚውል የተደረገው ድጋፍ የሚበረታታና ወደፊትም ሁሉም አፍሪካዊ ባለው አቅም ሊተገብረው የሚገባው በጎ ተግባር እንደሆነም ያነሳሉ፡፡

በሀገራት መካከል ግንኙነትን ለማጠናከር ብሎም ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት ለማምጣት ራቅ ካሉ ሀገራት ከሚደረጉ የእርስ በርስ ግንኙነት ይልቅ በቅርብ ካሉ የጎረቤት ሀገራት ግንኙነት የተሻለ ፍሬማ ነውም ባይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው ጥረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚፈጥረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዘለለ ለሌሎች የአሕጉሪቱ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥና ለሱዳንም መፍትሔ የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን ሀገራት መሉ በሙሉ እራሳቸውን መቻል ባይችሉም ያልባሰበት ለባሰበት መርዳት ተፈጥሯዊ ነው የሚሉት ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በምግብ እራሷን ለመቻል እንዲሁም የነበረባት ዕዳን በማገባደድ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ጎረቤቷን ማገዟ ተገቢ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለአፍሪካውያን እየተደረገ ያለው ድጋፍ በተለይ ዘላቂ መፍትሔ ከማምጣት አኳያ የላቀ ሚና እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡ ያደጉ ሀገራት ድጋፍ ሲያደርጉ ውስጣዊ ዓላማቸውን አንግበው ነው የሚሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፤ ድጋፉ በተለይ ከአፍሪካ ውጪ የሚመጡ ውጫዊ ጫናዎችን እንዲቀንሱ የሚያደርግ ስለመሆኑ ነው የሚገልጹት፡፡

የቀድሞ ዲፕሎማት ዲያሞ በበኩላቸው ሱዳን በችግር ውስጥ ካሉ ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤቷ ያደረገችው የሰብዓዊ ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው ይላሉ፡፡ ይህንን በጎ ተግባር ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ በተጨማሪም ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ወገኖች ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ ማድረግና የአፍሪካ ሀገራትም በአስቸጋሪ ጊዜያት እርስ በራስ መተጋገዝ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

በአሜሪካ የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞ አምባሳደር ቺሆምቦሪ-ኩዎ በአልጀዚራ “The Bottom Line” ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) በአፍሪካ ውስጥ “የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ” ነበር ይላሉ፡፡

የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው የሚሉት አምባሳደሯ፣ ወስነው ከሠሩ በውጭ ርዳታ የሚሸፈነውን በጀት ራሳቸው መሸፈን ይችላሉ በማለት ይከራከራሉ፡፡ በተጨማሪም አፍሪካ ሰጪ እንጂ ለማኝ ልትሆን እንደማትችል ይጠቁማሉ፡፡

የርዳታው መቋረጥ ለአፍሪካ የማንቂያ ደወል መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” እንደሚሉት ሁሉ የአፍሪካ መሪዎችም “ቅድሚያ ለአፍሪካ” ማለት መጀመር አለባቸው ባይ ናቸው፡፡

አፍሪካውያን ከለማኝነት ለመውጣት የተራድዖ ድርጅቱ ሥራ ማቆም እንደ ዕድል ተጠቅመው የተፈጥሮ ሀብታቸውን በማልማት ከልመና መውጣት አለባቸው ይላሉ፡፡

አፍሪካውያን የእርስ በርስ መደጋገፋቸውን በማጠናከርና በምግብ ራሳቸውን በመቻል የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ራዕይና ግብ አስቀምጠው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ማሳካት ሲችሉም በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለውጭ ገበያ በማቅረብ ወደ ብልፅግና የሚያደርጉትን ጉዞ እንደሚያሳልጥላቸው ነው ባለሙያዎቹ የገለጹት፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You