
በቻይና ናንጂንግ ከተማ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ከታዩ ድንቅ አጨራረሶች መካከል የወንዶች 3ሺ ሜትር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው። በፓሪስ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ብር ሜዳሊያ አሸናፊ ከ5ሺ ሜትር አሸናፊው ባገናኘው ውድድር የመጨረሻ ሜትሮች የታየው ትንቅንቅ በስፖርት ቤተሰቡ አድናቆት ተችሮታል።
በአስደናቂው ፉክክር በማይክሮ ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ የብር ሜዳሊያ ለሀገሩ ያሳካው ኢትዮጵያዊው አትሌት በሪሁ አረጋዊ፤ ለዚህ ቻምፒዮና ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቀረበለትን ጥሪ የተቀበለው በግሉ ሊሳተፍበት የነበረውን የግማሽ ማራቶን ውድድር ሰርዞ ነበር።
ይህ ለብዙዎች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ተግባርም ቡድኑ ወደ ሀገሩ መመለሱን ተከትሎ ያስመሰገነው ሆኗል። በቻምፒዮናው ከዓለም 3ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ በመሆን ያጠናቀቀው የአትሌቲክስ ቡድን ትናንት ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስ በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎለታል። ይህ የቡድኑ አበረታች ውጤትም በቀጣይ ለሚካሄዱ እንደ ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላሉ ውድድሮች መነሳሳትን እንደሚፈጥር አትሌቶቹ ተናግረዋል።
የመካከለኛና ረጅም ርቀት ጀግናው አትሌት በሪሁ አረጋዊ የግሉን ውድድር በመሰረዝ ለሀገሩ የብር ሜዳሊያ በማስገኘቱ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ገልጿል። ወጣቱ ኮከብ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና የመካፈል ዕቅድ ባይኖረውም በቀረበለት ጥሪ መሠረት በሁለት ሳምንት የዝግጅት ጊዜ በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤታማ ሆኗል። ከወራት በኋላ የሚካሄደውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አልሞ እየሠራ በመሆኑ ውድድሩ ልምድ ያገኘበት እንደነበርም ተናግሯል። ከኖርዌያዊው ተፎካካሪው እጅግ ጠንካራ ውድድር እንደገጠመው ያስታወሰው በሪሁ፣ በቀጣይ ሌሎች ውድድሮች ላይ የመገናኘት እድሉ ሰፊ እንደመሆኑ ባለው ጊዜ ሊያሸንፈው የሚያስችል ጠንካራ ዝግጅት እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡
በቻምፒዮናው አሳማኝ ብቃት በማሳየት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያሳካችው አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉም ትኩረቷ የዓለም ቻምፒዮና መሆኑን ተናግራለች። በፓሪስ ኦሊምፒክ በተፈጠረው ውዝግብ እንዳትሳተፍ ብትደረግም በተያዘው የውድድር ዓመት ግን በድንቅ ብቃት ተመልሳለች። በቻምፒዮናው አስቀድሞ በቱር ውድድሮች ብልጫ በማስመዝገብ በቀጥታ ተሳታፊነቷን ያረጋገጠችው ፍሬወይኒ፣ ለዓለም ቻምፒዮናው በተሻለ ዝግጅት ውጤታማ ለመሆን ዝግጅቷን ከወዲሁ ጀምራለች። በመካከል በሚኖሩ እንደ ዳይመንድ ሊግ ባሉ ውድድሮችም ፈጣን ሰዓት የማስመዝገብ ዕቅድ እንዳላትም ገልጻለች።
በ800 ሜትር ሴቶች የኦሊምፒክ ጀግናዋ አትሌት ጽጌ ድጉማ በፍጻሜው እንደተጠበቀው ሜዳሊያ ባታስመዘግብም ሌላኛዋ አትሌት ንግስት ጌታቸው የብር ሜዳሊያውን ወስዳለች። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፍሬ የሆነችው ወጣቷ አትሌት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት ቻምፒዮና ከባድ ቢሆንም በውጤታማነት በመፈጸሟ ደስተኛ ናት። ልምድ ካላቸው አትሌቶች ጋር ብትሮጥም በራሷ ታክቲክ መሮጧ የሜዳሊያ ባለቤት አድርጓታል። በቀጣይም በ800 እና 1ሺ500 ሜትር ሀገሯን እንደ ዓለም ቻምፒዮና ባሉ መድረኮች ለመወከል ጠንክራ እንደምትሠራ አስተያየት ሰጥታለች።
በ12 አትሌቶች በጥቂት ርቀቶች በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የተሳተፈችው ኢትዮጵያ 2 የወርቅ እና 3 የብር በጥቅሉ 5 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ አሜሪካና ኖርዌይን በመከተል አጠናቃለች። ለዚህም ምክንያት የሆነው በአሰልጣኞችና አትሌቶች መካከል የነበረው መናበብ መሆኑን ቡድኑን የመሩት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አበባ የሱፍ ጠቁመዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አንጋፋው አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ፣ ቡድኑ ያስገኘው ውጤት ለወደፊት ጥሩ ምልክት መሆኑን ነው የገለጸው። በቀጣይም ቻምፒዮናውን መነሻ በማድረግ መሠራት የሚገባቸውን ዝግጅቶች ለሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከወዲሁ የሚደረግ ይሆናል ብሏል። ለውጤታማው ቡድንም በቀጣይ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትለት አመላክቷል።
ለአትሌቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ድል የለመደ እንደመሆኑ ‹‹ኢትዮጵያ ኮርታባችኋለች›› ብለዋል። ስፖርት የሀገርን ውስብስብ ችግር የመፍታት አቅም ያለው እንደመሆኑ በዚሁ መንገድ በመሥራት በቀጣይ ለሚኖሩ ውድድሮች መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም የስፖርቱ ዋነኛ ችግር የሆነውን የማዘውተሪያ ስፍራዎችና የመም ዕጥረት በቅርቡ መፍትሔ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል። ለመጪው የዓለም ቻምፒዮናም አትሌቶች ዝግጅታቸውን በትራክ ላይ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም