
ኢትዮጵያን ስናነሳ በብዙ መልኩ ልዩ እንደሆነች እገነዘባለን። በተለይም በዓለም ዙሪያ የምትገኝበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ለሃይማኖቶቻችን የምንሰጠው ትኩረት፣ ለታሪካችን የምንሰጠው ክብደት፤ በሥልጣኔም ቢሆን ቀደምትነታችን እንዲሁም ነፃ የሆንን ሀገር መሆናችን የታሪክ ባለቤቶች ከሚባሉት ሀገሮች ተርታ ያሰልፈናል።
በሰላም አብሮ የመኖር ተምሳሌትነታችን፤ ብዙ የተለያዩ ቋንቋዎች ያለን መሆናችንና ሌሎች ዘርዝረን ልንጨርሰው የማንችላቸው የተፈጥሮ፤ የባሕልና ሰው ሠራሽ ሀብቶች ባለቤት መሆናችንም ለብዙዎች መሳቢያና መደነቂያ እንዲሁም መድመቂያ እንድንሆን ያስችለናል። ነገር ግን ይህን ሆነናል ወይ ከተባለ መልሱ ተቃራኒ ነው። በተለይም ዛሬ ዛሬ እየሆነ ያለውን ነገር ስናይ የት እየሄድን ነው፤ ምን ነክቶን ነው፤ ምን ይሻለናል ?እንድንል ያስገድደናል።
አሁናዊ እውነታችን በትውልድ ግንባታው ውስጥ ችግሮች እንዳሉብንም ያመላክታል። ችግራችንን ለይተን ለመፍትሔው መሥራት እንዳልቻልንም የሚያሳዩ ነገሮች አሉ። እንደሚታወቀው እኛ ባለታሪኮች ነን። እርስ በእርሳችን በታሪካችን የተሻለውን ሁሉ መገንባት የምንችል፤ ነፃ በመሆናችን የተሻለ ነገን መፍጠር የሚሆንልን ነን። በብዙ ባሕላችን የከረረ ጸባችንን ማብረድ፤ ትስስርን ማጠንከር የምንችልም ነን። ለሌሎች አርአያ መሆን የምንችላቸው ሀብት ባለቤቶችም ነን።
ነገር ግን አንዱንም እየተጠቀምንበት ነው ለማለት የሚያስቸግሩ ተግባራትን ስንከውን እንታያለን። እኛ አይደለም ለሰው ለእንስሳት ጭምር የምንሳሳ ሕዝቦች ነበርን። ዛሬ ግን ግለሰቦች በሚፈጥሩት ውዥንብር መነሻነት የምናደርገው ጠፍቶብን እንታያለን። አሰቃቂ ድርጊቶችን ምንም ሳይመስለን እንፈጽማለን። ባለመረዳታችን ራሳችንን በራሳችን እየገደልን እንገኛለን። ቆም ብለን ባለማሰባችን የማይታሰቡ ማንነታችን ያልተገነባባቸውን ተግባራት ስንፈጽም እንታያለን። ለዚህም አብነት የሚሆነን ምንም የማይመለከታቸውን እንስሳት ጭምር በጋጣቸው ማቃጠል መጀመራችን ነው። እዳው ለእኛም ለልጆቻችንም ሆነ ለሀገራችን እንደሚተርፍ ሳይገባን በምን አለብኝነት የደረሱ ሰብሎችን በእሳት እያቃጠልን ነው።
እኛ ስለ አንድ ሰው ነፍስ የሚጨንቀን ሃይማኖተኛ ሕዝቦች ነበርን። ዛሬ ላይ ግን አሰቃቂ ድርጊቶች ባሕል እስኪመስሉ ድረስ ከአንድም ሁለትና ሦስት በላይ ሲደረጉ እንመለከታለን። አባት በልጁ፤ ልጅ በእናቱ ሲጨክን እናያለን። አባት ልጁን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደፍር፤ ሲገድል ማየትም የተለመደ ተግባር ሆኖ እየቀጠለ ነው። ወጣቱም ማን ሹክ እንዳለው በማይታወቅ ሁኔታ ፍቅሬን ለምን አልተቀበልሽም ሲል አሲድ ሲደፋ፤ አንቆ ሲገል፤ በጥይት ጭምር በጠራራ ፀሐይ ያናገራትን ሕይወት ሲቀጥፍም ማየት እየለመድን ነው።
እኛ በነበረን ልምድ ከተጋቡ በኋላ መፋታትን አናውቅም። ችግሮች ቢኖሩ ቤተሰብ ጭምር ጣልቃ ገብቶ ያስታርቅና ዓመታት በትዳር የምንቆይ ሕዝቦች ነበርን። ዛሬ ግን ተዋዶ ተጋብቶ ሳይቀር በሰላም መፋታት አይቻልም። በአሰቃቂ ሁኔታ ሚስትን መግደል ጀብዱ እየሆነ መጥቷል። ታዲያ እነዚህንና መሰል አሰቃቂ ሥራዎቻችንን ስንመለከት ሁላችንም ውስጥ አንድ ነገር ማቃጨሉ አይቀርም።
ይህም ምን ነክቶን ነው? የሚለው ነው። አዎ ምን ነክቶን ይሆን? ምክንያቱም እኛ ባሕል አላነሰንም፤ ያውም መልካሞችና ትውልድን በሚገባ የሚቀርጹ። እኛ ሃይማኖት አለን። ያውም መልካም ሥነ ምግባርን የሚያላብሱ። አዎ እኛ ሕግ አለን በማህበራዊ ሕይወታችን የሚያስተሳስሩ። ታዲያ ምን ነክቶን ነው እንዲህ ሰውነታችን የወሰደው? ሰብዓዊነታችንን የሰለበው?
እኔ ይህንን ነገር በሦስት መልኩ ከፍዬ ማየት እፈልጋለሁ። የመጀመሪያው ማህበራዊ መስተጋብራችን በተለያዩ መንገዶች ላልቷል የሚል ነው። ትናንት ጎረቤት ብቻውን ምንም አያደርግም። ጥሬ እንኳን ብትኖረው አብሮ መቆርጠምንና ችግሩን አብሮ ማሳለፍን ይመርጣል። በትንሿ ቤት ቡና ጠጡ ተብሎ ችግር መፍትሔ ይሻትለታል። ሀዘን ወደ ደስታ ይቀየራል። ደስታም ብቻን ሳይሆን በሌሎች ሕብረት ልብን አረስርሶ ቀጣይ ሕይወትን ያሰምራል። ዛሬ ግን ማንም የማንንም ሃሳብ መስማት አይፈልግም። ሁሉም በራሱ ልክ ነኝ ብሎ ማሰብንና ወደፊት መጓዝን ይመርጣል።
ዛሬ ቡና ጠጡ ጠፍቷል። በዚህም በቤት ውስጥ ችግሩን አምቆ የሚቆዝመው ብዙ እንዲሆን አድርጓል። ቡና ጠጡ ለነገ ባለዳነትን ያወርሳል። ምክንያቱም መልስ ሳይሰጡ እየሄዱ መጠጣት ነገ የማይኖሩት ሕይወት ነው። ትናንት የቸገረው ሰው፤ ሀዘን የደረሰበት ሰው፤ የታመመ ሰው ልክ እንደ ቤተሰብ በጎረቤቶቹ እንክብካቤ ያገኛል። ተሽሎትም በደስታ ሕይወቱን ይመራል። ዛሬ ግን ቤተሰብ ጭምር ይሰላቻል። ረዘም ላለ ጊዜ ከታመመ ደግሞ በቃኝ እስከ ማለትም ይደርስና ለሞት ጭምር ይዳረጋል።
በማህበራዊ ግንኙነት ሰው እንደ ሰው ይታያል። ቤተሰብ፤ ጓደኛ፤ የሀገሬ ልጅ ይሉት ነገር አይባልበትም። ይህ ትናንት ላይ በስፋት ነበረ። ለዚህም ምስክራችን እንደ ጉዲፈቻ ዓይነት ልዩ ባሕሎቻችን ናቸው። የሌላ ልጅ ልጄ ይባልበታል። የፈለገው ነገር ተሟልቶም ለወግ ማዕረግ ይበቃበታል። ዛሬ ግን አይደለም የሌላውን ማሳደግ በራስ ልጅ ላይ መጨካከን ተጀምሯል። እናት ልጇን ሳይቀር በአደባባይ ጥላ መሄድ አለያም አፍና ስትገል ይታያል። ስለሆነም ችግሮቻችንን አብረን መፍታታችን እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ተግባራትን እንድናይ፤ እንድንሰማ አድርጎናል።
ሌላውና ሁለተኛው ለባሕላችን እየሰጠነው ያለነው ትኩረት እያነሰ መምጣቱ ነው። ሁሌ ባሕላችንን ስናስብ ኋላ ቀር ነው እንለዋለን። ኋላ የቀረው ማነው ሲባል ከሌላ ዓለም የወሰድነው እንደሆነ እንረዳለን። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያዊያን በሕግ መመራትንና ዲሞክራሲን ሳይቀር በገዳ ሥርዓታችን ለዓለም ያስተማርን ሕዝቦች ነን። በዚህ ደግሞ ዛሬያችንን ብቻ ሳይሆን ነጋችንን አሳምረናል፤ ሰርተንበት ቆይተናልም። ለማንነታችን መገንባትም ወሳኝነት ኖሮት አልፏልም።
በባሕላችን ትናንት ስናድግ ታዛዥነትን ተምረናል፤ አክባሪነትን አውቀናል። ሰውን መውደድን ኖረንበታል። ምክንያቱም ትናንት ልጅን እንደ ልብ ጎረቤት ጋር ጥሎ ሥራን አከናውኖ መመለስ ይቻላል። የሰፈሩ እናትና አባቶች በሙሉ የሁሉም ልጆች ናቸውና በእነርሱ ተቆንጥጠዋል፤ ተገስጸው መልካም ሥነ ምግባርን ተላብሰዋል።
ትናንት በኖርነው ባሕል ሁሉም አንድ ዓይነት አኗኗር ስለሚኖር እናትንና አባትን ከተወቃሽነት ታድጓል። ተተኪውን ትውልድም በፍጹም እምነትና ታዛዥነት ስላሳደገው የተደረገለትን ለመክፈል እንዲፋጠንና ነገውን እንዲሠራ ሆኗል። በምላሹ ምንም ሳይጠብቅ አዛውንት አይሉት ታላቅ መታዘዝ ግዱ እንደሆነ በባሕሉ አውቋል። ከዚያም ባሻገር ምርቃቱ ነገውን እንደሚሠራለት ተረድቶ ዛሬውን አድሷል።
ዛሬስ ከተባለ ነገሩ ሌላ ነው። የሚቆጣ፤ ሊያስተካከል የሚፈልግ ሰው ባይጠፋም ምን አገባህ ባዩ በርካታ ነውና ማንም የማንንም ልጅ አይቀጣም። ለማስተካከልም አይሞክርም። ጎረቤት በሰፈሩ ልጅ ጉዳይ መብት የለውም። እንደ ትናንት ጎረቤት ልጅን አደራ ሰጥቶ መሄድም የሚቻልበት ጊዜ አይደለም።
ምክንያቱም ልጅን የሚያስነውር ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ተበራክተዋል። በባሕል አይቻልም የሚባለው ነገር ተገፎ ሁሉንም ማድረግ መብቴ ነው ወደሚል ሃሳብ ተቀይሯል። ስለዚህም የአካባቢው ሰው ለተተኪ ትውልዱ እምብዛም አይጨነቅም፤ ልጁንም ከቤት እንዲወጣ አይፈቅድም።
ትውልዱ ነባርና መልካም ባሕሎቹን እየተወ በመምጣቱና ሀይ ባይ በማጣቱ ዛሬ እኛነትን እየጠፋ ግለኝነትን አንግሷል። ለእኔ ብቻ ማለቱን ተያይዞታል። ይህ ደግሞ በምንም መልኩ ርካታ ላይ ስለማያደርሰው የማይገባውን ነገር እንዲሆን አድርጎታል። በተለይም ወጣቱ ላይ የምንመለከተው በሱስ የመጠመድ ባሕል የሚያማክረው፤ ችግሩን የሚጋራለትና መልካም መንገዶችን የሚመራው ሰው በማጣቱ የተነሳ የመጣ መሆኑን ማንም የሚረዳው ነው።
ሁኔታው ሲከብደው ራሱን እስከ ማጥፋትም የሚደርሰው በምንም ምክንያት አይደለም። ባሕል ሲተው ሌላ ባሕል ፍለጋ መባዘን አይቀርምና ብዙዎቹ ወጣቶች ገብተው የምናያቸው ምዕራባውያኑ ጎራ ነው። ግለኝነት የነገሰበት የምዕራቡ ዓለም ባሕል ከራስ አልፎ ሌሎች ላይ ጨካኝ እስከ መሆን ያደርሳል። የሌለንን ያገኘነውም ከዚህ አንጻር ይመስለኛል።
ሶስተኛው ሃይማኖተኛ አለመሆን ነው። እንደሚታወቀው ሀገራችን 98 በመቶ የሚሆነው አማኝ ሕዝብ ያለባት ነች። ሆኖም እምነት ከምግባር ጋር የተካከለባት መሆን እንደተሳናት በተለያዩ ተግባራት እንመለከተዋለን። እምነቱ የማይፈቅዳቸው በርካታ ተግባራት ሲከወኑም እናያለን። አንዱ የሰውን ልጅ ሕይወት በረባ ባረባው ማጥፋቱ ነው።
በማንኛውም እምነት ሰው መግደል ተገቢነት የለውም። ነገር ግን አሁን ላይ አንድና ሁለት ሦስትና አራት ከዚያም በላይ ሲሞቱ የቁጥሩ ብዛት እንጂ የሰውዬው ማንነት አያሳስበንም። ‹‹ትንሽ ነው›› ማለትም ጀምረናል። ለመሆኑ የሰው ትንሽ አለው? ስንት ሲደርስ ነው ብዙ የምንለው? መልሱን ለእናንተ ልተወው።
አንድ ነገር ግን እኔ አምናለሁ። አይደለም ሰውን መግደል ራስን ማጥፋት እንኳን በፈጣሪ ዘንድ ከባድ ቅጣትን ያመጣል። ሰውን መግደል ብቻውን ስናይ እንኳን ሰው ፈጣሪ ክቡር አድርጎ ከሁሉም አስበልጦ በራሱ አምሳያ የፈጠረው ነው። ፈጣሪን ማስከፋት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ቅጣቱም ከሌሎች እኩል እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። ስለዚህም እኛ አማኞች ነን የምንል እምነታችን ተግባራችንን እንዲገልጸው ካላደረግን በስተቀር መቼም ከዚህ የባሰ እንጂ ያነሰ ነገር እንደማያገኝን መገንዘብ ይገባናል።
እንደምታውቁት ኢትዮጵያዊነት በአንድ ግለሰብ ፍላጎት፣ በአንድ የታሪክ ወቅት ወይንም በአንድ የታሪክ ቦታ የሚተረጎም አይደለም። የኢትዮጵያዊነት ትርጉም በአንድ ግለሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይም አይመሠረትም። ኢትዮጵያዊነት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የሀገር እውነት ነው። ዛሬም፤ ነገም፤ ከነገ ወዲያም ዘላለማዊ የሚሆን ባለ ሀገርነት፤ ባለቤትነት፤ ማንነትን ማላበስ ነው። ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያዊነት ከኢትዮጵያ መገኘትን ይጠይቃል።
በትውልድ ሽግግር ውስጥ ማንነትን ይገነባል። የተሻለውን መንገድም ማሳየት ነው። ኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ ያለንን ፍቅር ያቅፋል። ሀገሬ የእኔ ናትና እቆምላታለሁ የሚል ሃሳብን በውስጣችን ያሰርጻል። በአንድነት መቆምን፤ ነፃነትን፤ መከባበርን መሠረት የሚያደርግ ኃይልም ነው። በመሆኑም ተሳስረን፣ አንድነታችን አጠንክረን፣ አንድ ሀገር ሆነን ወደፊት መጓዝ ይገባናል።
ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለ ነው ሁሉ ከግጭት ይልቅ ፍቅሩ እንደሚገነባን ልንረዳ ያስፈልጋል። አንድ የሆነ እምነትና መግባባትም ልምዳችን፤ ባሕላችን መሆን ይገባዋል። ይህ ካልሆነ ግን አሁን እየሆንን ካለነው በላይ የችግሮች ሰለባ መሆናችን አይቀርም። ዛሬን ተመስገን ማለታችንም እንዲሁ የሚቀር አይደለም። ሰላምና መረጋጋት፤ ልማትና ዕድገት፤ የሕልም እንጀራ ይሆኑብናል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርብን ሕብረታችን ሲገነባን፤ ባሕላችን ሲያስተሳስረንና ነጋችንን ብሩህ ሲያደርግልን ነው። ግለሰብ ሀገርን ሲያተራምስ እሺ ብሎ መከተሉ አያዋጣንም። ተባብረን ማረፍ ያለባቸውን አካላት እረፉ ልንላቸው ይገባል። ያለንን ሕግና መመሪያም በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሕግ በላይ ማህበራዊ ትስስራችን ያፋቅረናል። ባሕላዊ ዳኝነታችን ችግሮቻችንን ይፈታልናል። እርቃችን ከልብ፤ ደስታችን ከውስጣችን የሆንን ሕዝቦች ነንና ጠንካራ ሀገራችንን ለመመስረት አሁንም አረፈደም። ጎባጣውን በመልካሙ የባሕል እሴታችን ልናቀናው ያስፈልጋል።
እያየን ያለውን መሠረታዊ ሀቁን ከመካድ ይልቅ ተቀብለነው በመልካሙ የባሕልም፤ የሕግም ዳኝነታችን ልናስተካከለው ግድ ይላል። እኛ ስንተባበር፤ እኛ እኛነታችንን ስንቀበል ነው ወደፊት የምንራመደው። ሀገራችንን የሚያስጠራ ለውጥና ብልፅግናን የምናመጣው። ስለዚህም የሆነውን በመለየት ልንሆን የምንፈለገውን እናድርግ በማለት ለዛሬ የያዝኩትን ሃሳብ ቋጨሁ። ሰላም!!
ክብረ መንግስት
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም