አሜሪካ የኤችአይ ቪ ርዳታ ማቋረጧ የሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ ተገለጸ

የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ በመቋረጡ በየቀኑ ተጨማሪ ሁለት ሺህ አዳዲስ ሰዎች በኤችአይቪ እንደሚያዙና በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ሰዎች በላይ በበሽታው እንዲሞቱ እንደሚያደርግ የዩኤንኤድስ ኃላፊ ተናገሩ፡፡

እ.አ.አ በ2004 በኤች አይቪ ኤድስ ይሞቱ የነበሩ ከሁለት ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች ቁጥር በ2023 ወደ 600 ሺህ መቀነስ ተችሎ የነበረ ቢሆንም የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ግን ኤች አይቪን በመከላከል ረገድ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል ተብሏል፡፡

የዩኤንኤድስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊኒ ቢያኒማ የአሜሪካ መንግሥት ለኤችአይቪ ፕሮግራሞች ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ ጨምሮ የውጭ ርዳታን ለማቆም መወሰኑ ከወዲሁ አስከፊ መዘዝ እያስከተለ ነው ማለታቸው ተሰምቷል። በተለይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ በመግለጽ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የማቋረጥ ውሳኔውን በአስቸኳይ እንዲያጤነው አሳስበዋል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው የኤችአይቪ ህክምና እና መከላከል መርሀ-ግብሮች በመቋረጣቸው የተነሳ በአፍሪካ ውስጥ የእናቶች እና የጨቅላ ህጻናት ክሊኒኮች እንዲዘጉ ሲደረግ ሕይወት አድን የሆኑ የጸረ ኤች አይቪ መድሃኒቶች ላይም ከፍተኛ እጥረት መከሰቱ ታውቋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢያኒማ የጸረ ኤችአይቪ መድሃኒቶች በድሃ ሀገራት እምብዛም ወደማይገኙበት፣ ኢንፌክሽኖች እና ሞት እየጨመሩ ወደነበረበት 1990ዎቹ ዘመናት እንዳይመለስ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል። አሜሪካ ለዓመታት የኤችአይቪ ህክምና እና መከላከል ላይ ብቸኛዋ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ ሀገር የነበረች መሆኗን አንስተው፤ ለዚህ በጎ ተግባሯም ቢያኒማ አመስግነዋል። አሜሪካ ‹በጊዜ ሂደት የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀነስ መፈለጓ ምክንያታዊ ነው ነገር ግን የሕይወት አድን ድጋፍ በድንገት ማቋረጧ ከባድ ተጽእኖ ያሳድራል› ብለዋል፡፡

እስከ አሁን ድረስ ዋሽንግተን ውሳኔዋን እንድትቀይር የሚቀርቡላትን ተማጽኖዎች እየሰማች እንደሆነ የሚያሳይ ምንም ምልክት ካለመኖሩ በላይ በአውሮፓ የሚገኙ ለጋሽ ሀገራትም የገንዘብ ድጋፍን ለመቀነስ ያቀዱ ሲሆን እንደዚሁም ኤችአይቪን መከላከል ላይ የሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት የጋራ ኤጀንሲ ሌሎች ሀገሮች በአሜሪካ ውሳኔ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ምንም እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ጠቅሷል፡፡

ቢያኒማ ሰኞ እለት በጄኔቫ ንግግር ሲያደርጉ በኬንያ ኤችአይቪ በደሟ የሚገኘውን የጁሊያናን ታሪክ ጠቅሰው፤ ከአሜሪካ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ እናቶች ልጆቻቸው በበሽታ እንዳይያዙ ለመከላከል የምትሠራውን ሥራ ማቅረባቸው ታውቋል። አያይዘውም አሜሪካ የምታደርገው ድጋፍ ከተቋረጠ ጁሊያና ሥራዋን ማጣት ብቻ ሳይሆን ጡት የሚጠባው ልጇ ህክምና በማጣት ለአደጋ እንደሚጋለጥ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ናይጀሪያ፣ ኬንያ፣ ሌሴቶ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ፣ ሄይቲ እና ዩክሬን የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ካቆመ በቅርብ የኤችአይቪ መድሃኒት ሊጨርሱ እንደሚችሉ ስጋቱን መግለጹ ይታወሳል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኤችአይቪ ፕሮግራሞች መስተጓጎል የሃያ ዓመታት እድገትን ሊቀለብስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ዩኤንኤድስ የገንዘብ ቅነሳ ከሚደረግባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች አንዱ ነው። የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ 6ሺህ ያህሉ ሥራ ሊያጣ እንደሚችል ሲገልጽ ዩኒሴፍ በበኩሉ የህጻናትን ሞት መቀነስ ላይ የታየው መሻሻል ስጋት ሊገጥመው ይችላል ብሏል። አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደሥልጣን በመጡበት የመጀመሪያ ሳምንት ወቅት የመንግሥት ወጪ ለመከለስ በሚል ለዘጠና ቀናት ያህል ሀገራቸው የምትሰጠውን ዓለም አቀፍ ርዳታ ማቋረጣቸው አይዘነጋም። መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You