ለዘላቂ የቡና ገቢ ዕድገት ከምርት እስከ ብራንድ

ዜና ትንታኔ

በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ቤተሰቦች ኑሯቸውን በቡና ላይ ያደረጉ ናቸው:: ከዚህም ባለፈ እንደ ሀገር ኤክስፖርት ከሚደረጉ ምርቶች ቡና አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል:: ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግ በተሠሩ የለውጥ ሥራዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በየዓመቱ የሚገኘው ገቢ እና የሚላከው የቡና መጠን ከ50 በመቶ በላይ እድገት ማሳየቱን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሪፖርቶች ያሳያሉ:: ከባለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ወጪ የተደረገውን የቡና መጠን እና የተገኘውን ገቢ ማየት ቢቻል፤ በየጊዜው እየመጣ ያለው ለውጥ አበረታች የሚባል እንደሆነ ነው የሚገለጸው:: በባለፈው በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከሦስት መቶ ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ይገለጻል::

በዘንድሮ በጀት ዓመት ደግሞ በስምንት ወራት 257 ሺህ ቶን በመላክ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ተችሏል:: በጀት ዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በማግኘት በቡና የወጭ ንግድ ታሪክ አዲስ ሪከርድ ለመስበርም ታቅዷል::

ከዚህ ጋር ተያይዞ ዘንድሮ የብራዚል እና የቬትናም የቡና ምርት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መጎዳቱን የሚነገር ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ መነቃቃት ከማሳየቱም በተጨማሪ፤ አዳዲስ መዳረሻ ሀገራትን ለማግኘት ችሏል:: የተገኘውን የገበያ ዕድል ዘላቂ ለማድረግ ምን መሠራት አለበት በሚለው የቡና ላኪዎች ማኅበርን እና ምሑራንን አነጋግረናል::

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና እንደሚናገሩት፤ የብራዚል እና የቬትናም ቡና ምርት በድርቅ፣ በውርጭ እና ያለጊዜው ዝናብ በመዝነቡ ምርታቸው በጣም ቀንሷል:: ይህም በዓለም የቡና አቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል::

ይህም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የቡና አቅራቢ ሀገራት የቡና ዋጋ ጭማሪ ተደርጓል:: ነገር ግን ይህ አጋጣሚ ስለሆነ ቀጣይነት አይኖረውም:: ምክንያቱም ሁለቱ ሀገራት ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያገግሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖር ያስረዳሉ::

ፕሬዚዳንቱ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ጥራት ያለውና ተፈላጊ ቡና እንደምታመርት ዓለም ላይ ቡና አቅራቢ ሀገራትን ጨምሮ ሁሉም ያውቀዋል:: እንደ ሀገር የተገኘውን ዕድል በመጠቀም የቡና ምርትን የበለጠ ማስተዋወቅ እና የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ተገቢ ነው::

ከዚህ አንጻር በድርቅ የሌሎች ሀገራት ምርት ሲጎዳ ወይም ምርታቸው ቀንሶ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚለው ጊዜያዊ ነው:: ከዚህ መነሻነትም በራስ አቅም ተወዳዳሪ በመሆን ቀጣይነት ያለው የገበያ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ስትራቴጂ መከተል አስፈላጊ ነው ይላሉ:: ይህን ለማድረግ ወሳኙ ነገር ምርት ማሳደግ፤ የምርት ጥራት መጠበቅ፤ ቡና ምርት ሲደርስ በጊዜ መሰብሰብ፤ እና የምርት ቅብብሎሽ አስተዳደር በማዘመን የግብይት ሠንሠለቱን ማሳጠር አንዱ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ማስተዋወቅ እና አዳዲስ ገበያዎችን ማፈላለግ እንደሆነ ይጠቁማሉ::

አቶ ደሳለኝ እንደሚገልጹት፤ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ተልዕኮ ወደማያውቅባቸው ሀገራት ማለትም ወደ ታይዋን፣ ቻይና ኢንዶኔዥያ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየላክን ነው:: የዓረብ ሀገራት ድሮም ይገዙ የነበር ቢሆንም፤ አሁን የበለጠ የሚገዙት የምርት መጠን ያደገበት ሁኔታ አለ::

የገበያውን ዕድል ዘላቂ ከማድረግ አንጻር መንግሥት አዳዲስ ፖሊሲዎችን መቅረጽ፣ ከተለያዩ የቡና ማኅበራት ጋር በቅርበት በመሥራት፣ የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ ይገባል:: በተጨማሪም ምርታማነት ከማሳደግ አንጻር ምርምሮች ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳሉ::

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፤ ከመንግሥት በኩል ፖሊሲዎችን ማሻሻል፤ ከተለያዩ የቡና ማኅበራት ጋር በቅርበት በመሥራት፣ የቴክኒክ ድጋፎችን ማድረግ እና ምርምሮች እንዲሠሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው::

አርሶ አደሩ በኩል የተሠሩ ምርምሮችን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ቡና ከገበሬው ተቀብለው ለውጭ ሆነ፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡ አካላት የቡና ምርትና የገበያ ተደራሽነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ይጠቁማሉ::

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ምርምር ዳይሬክተር ታደለ ማሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የቡናን ገቢ ለማሳደግ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗን፤ የተለያዩ የግብርና ሥነ-ምሕዳር መኖሩን እና የኢትዮጵያ የቡና ጣዕም የተለየ መሆኑን በማስተዋወቅ ብራንድ ላይ መሥራት ቀዳሚው ጉዳይ ነው::

ብራንድ ላይ ከመሥራት አንጻር ቡና የተመረተበትን የግብርና ሥነ ምሕዳር ማስቀመጥ ተገቢ ነው:: ለምሳሌ የሐረር፣ የይርጋ ጨፌ እና የሲዳማ ሥነ-ምሕዳር አለ:: ይህን ቡናው ከተመረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዝርዝር ጉዳይ ማሸጊያው ላይ መለጠፍ እና “ዘ ኢኮኖሚስትን” ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጋዜጦች ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ::

የተወሰነ ወጪ በመመደብ ዓለም አቀፍ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማስተዋወቅ ጠቃሚ ነው:: ምክንያቱ አንዴ በደንብ ከተዋወቀ ወደ ሰው ልብ ዘልቆ ስለሚገባ፤ በዚህ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ::

ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት፤ ጥሬ ቡና ወደ ውጭ ሀገራት እንደሚላከው ሁሉ፤ ዓለም አቀፍ ቡና ላይ የሚሠሩ ፋብሪካዎች ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ በማድረግ እሴት የተጨመረበት ቡና መላክ ከቡና የሚገኘውን ገቢ ማሳደጊያ አንዱ መንገድ ነው::

በእርግጥ ብራዚል ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ላይ በስፋት የምትሠራ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምሥራቅ ካላት ቅርበት እና የሀገራቱ ኢኮኖሚ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ በእነዚህ ሀገራት ላይ በስፋት መሥራት ይገባታል ይላሉ::

በተለይ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የኢትዮጵያን ቡና አብረው ለማልማት ጥረት እያደረጉ ነው:: እነሱ ላይ በስፋት መሥራት አስፈላጊ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከታዋቂ ዓለም አቀፍ የቡና ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ማጠናከር እና ዓለም አቀፍ የቡና ቀኖች ሲኖሩ ማስተዋወቅ እንደሚገባም ይገልጻሉ::

ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት፤ ለአርሶ አደሮችም ልዩ ትኩረት በመስጠት ሥልጠናዎች መስጠት ተገቢ ነው:: የተገኘውን ዕድል ለማስቀጠል እና የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን ሌላኛው ጉዳይ ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው:: በተለይ ከአምራቹ ጀምሮ አሁን ዓለም የሚፈልገው ምን አይነት የቡና ጣዕም እና ብራንድ ነው የሚለውን በመረዳት፤ የአካባቢ ጥበቃን መሠረት ያደረግ የቡና አመራረት አርሶ አደሩ እንዲከተል ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ነው የተናገሩት::

በዚህ ረገድ ደግሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ተፈጥሯዊ የቡና አመራረት መከተል ጠቃሚ ነው:: እንደ ሀገር ያለው የቡና አመራረት የጥላ ቡና አመራረት ነው:: ይህ ደግሞ የካርቦን ልቀትን የመቀነስ ዕድል ስላለው፤ ይህን ለዓለም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ሲሉ ይጠቁማሉ::

አርሶ አደሮች ግብዓት በቶሎ እንዲያገኙ እና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ መሥራት እና እስከ ወደብ ድረስ ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት የተቀላጠፈ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ::

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You