ኢትዮጵያ ታሪኳም ሆነ ሕልውናዋ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው

አዲስ አበባ፡- ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ስጦታ በመሆኑ ታሪኳም ሆነ ሕልውናዋ በሙሉ ከቀይ ባሕር ጋር እንደሚያያዝ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሳ ሼኮ ገለጹ፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሳ ሼኮ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ስጦታ በመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክና ሕልውና በሙሉ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቀይ ባሕር እንደ ዓይን እና እግር አንድ አካሏ ስለሆነም የኢትዮጵያ ታሪክ ከቀይ ባሕር ተነጥሎ ሊጻፍ አይችልም ብለዋል፡፡

ቀይ ባሕርን ማጣት ማለት ከኢትዮጵያ አካል አንዱን ማጣት ማለት መሆኑን ጠቁመው፤ ቀይ ባሕር ሲባል ባሕርነቱ ወይም መውጫ በር መሆኑ ብቻ አይደለም የተፈለገው፡፡ በቀይ ባሕር ላይ ከ 120 በላይ ሚሊተሪ ቤዞች ይገኛሉ፡፡ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ተርኪዬ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ጃፓን እና ሌሎች ሀገራት ከሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት አቆራርጠው መጥተው ቀይ ባሕር ላይ ሰፍረው ኢትዮጵያ አፍንጫዋ ስር የሚካሄደው ነገር አይመለከታትም ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

አንድ ሰው ቡሬ ተራራ ላይ ቆሞ ቀይ ባሕርን መመልከት እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ሙሳ፤ የባሕር በር ከኢትዮጵያ ድንበር 60 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚርቀው፡፡ ዓለም በደጃችን ሲፋጭ እናንተ ከቀይ ባሕር ምንም የላችሁም እንዴት ይባላል? የቀድሞዎቹ ፖለቲከኞች የሠሩት ስህተት ለምንድን ነው በምሑራን ደረጃ እና በሕግ ባለሙያዎች ዛሬ የማይታየው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሀገር መሆኗን ተረድቶ ቀይ ባሕር ላይ መገኘቷን ስትራቴጂክ ጉዳይ አድርጎ እየተመለከተው ይገኛል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ግብፅና ኤርትራ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የምታነሳውን ጥያቄ ለመቀልበስ የሚያደርጉት ሩጫ የትም አይደርስም ነው የሚሉት፡፡

አቶ ሙሳ፤ በቀጣናው ካለው ተለዋዋጭ ሁኔታና አልሻባብ እየፈጠረ ካለው ችግር ጋር ተዳምሮ ቀይ ባሕር ሌላ መልክ ሊይዝ ይችላል፡፡ አሁን እንኳን የሁቲ አማጺያን በአካባቢው ላይ እየፈጠሩ ያሉት ችግር የሚታወቅ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ሁኔታ ስለተረዳ ኢትዮጵያ የግድ ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ መጠጋት አለባት የሚል አቋም ይዟል ብለዋል፡፡

አያይዘውም፤ ስለ ስለ ቀይ ባሕር ስናነሳ ልንመለከታቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ ጣሊያኖች ከወጡ በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴራል እንድትዋሓድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ስምምነት ላይ በተደረሰበት ወቅት ሰነዱ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር የተጻፈ ነገር አለ፡፡ ኤርትራ ስትገነጠልም እንዲሁ የተደረሰው ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ሐቅ እንዲጠበቅ የሚል ሀሳብ ሰፍሯል፡፡ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በተደረሰው በአልጀርስ የድንበር ስምምነት ላይም ስለ አሰብ ወደብ የተባለ ነገር አለ፡፡ በሦስቱም ሰነዶች ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት የለባትም የሚል አቋም ተንፀባርቋል ብለዋል፡፡

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You