
ከለንደን ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ ኒውዮርክ ከተማ ለመድረስ ያስችላል የተባለ የባቡር ዋሻ በ15 ትሪሊዮን ፓውንድ ለመገንባት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ንድፈ ሃሳቡ ይፋ የሆነው።
ጉዳዩ ሕልም ቢመስልም እነዚህን ከ4 ሺህ 820 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ያላቸውን ሁለቱን ከተሞች የሚያገናኝ ‘ትራንስ አትላንቲክ’ የተባለ የባቡር ዋሻ ለመገንባት የቀረበው ንድፈ ሃሳብ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ነው የተገለጸው። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት እውን የሚሆን ከሆነ የለንደን ከተማ ነዋሪዎች በቀላሉ ባቡር በመሳፈር በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ ኒው ዮርክ ከተማ ሊደርሱ ይችላሉ ተብሏል።
ንድፉ አዲስ ባይሆንም ሊሳካ አይችልም በሚል ተቀምጦ ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ የዋሻው ርዝመት እና እሱን ለመገንባት የሚጠይቀው ወጪ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር የሆነው ኤለን መስክም ስለዚህ ጉዳይ በኤክስ (ትዊተር) ገጹ እንዳሰፈረው ከሆነ “The Boring Company” የተባለው ድርጅቱ አሁን ዋሻውን ለመገንባት ከሚጠይቀው ዋጋ አንድ ሺህ እጥፍ ባነሰ ዋጋ ሊሠራው እና ማጠናቀቅ እንደሚችል ገልጿል። ምንም እንኳ የሚጠይቀው ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም ንድፈ ሃሳቡ በስተመጨረሻ እውን ሊሆን እንደሚችል የቅርብ ጊዜ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች አመላካች መሆናቸውን ገልጿል።
ለዚህ ፕሮጀክት የታቀዱት ባቡሮች ፍጥነት በሰዓት ከ4 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ የሚችሉ ሊሆኑ እንደሚችሉም ነው የሚጠበቀው። ይህም ፍጥነቱን የሚገድብ ምንም የአየር ግፊት ከሌለ ማለት ነው ሲል ሜትሮ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም