
የኢኮኖሚ ስብራት ዛሬ ላይ የተፈጠረ ሳይሆን ዓመታትን ያስቆጠረ፤ ከመጣንባቸው አስቸጋሪ ውጦ ውረዶች ጋር የተቆራኘ ነው። ከአንድ የመንግሥት ስርዓት ጋር የተሳሳረ ሳይሆን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ ድንገትም ከዚያም በፊት ጀምሮ የተስተዋለ፤ በደርግ ስርአት ሆነ በኢሕአዴግ ስርአት የቀጠለ እና ለብልጽግና መንግሥት ያደረ የቤት ሥራ ሆኖ የኖረነው ።
የለውጡ መንግሥት ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት፤ በሕዝቡ ውስጥ ከነበረው የለውጥ መንፈስ አኳያ ብዙ ደስታ የነበረ ቢሆንም፣ እንደ ሀገር የነበርንበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች የላቀ የለውጥ አመራር አቅሞችን፣ አርቆ አሳቢነትን፣ ሆደ ሰፊነትን እና ስክንተን የጠየቀ እንደነበር ለዜጎች የተሰወረ አይደለም።
በአንድ በኩል ለውጡን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚሞክሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች፤ በሌላ በኩል በለውጥ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የገቡ፤ ከዛም በላይ ለውጡን ሙሉ በሙሉ በመቀልበስ በኃይል እና በሴራ ከጃችን ወጥቷል ያሉትን ስልጣን ለማስመለስ የተንቀሳቀሱ ኃይሎች የፈጠሯቸው ግር ግሮች እና ግራ ማጋባቶች የለውጡን መንፈስ በብዙ ተፈታትነውታል።
ለውጡ ቀናትን እየተሻገረ በመጣ ቁጥርም ከለውጥ ዋዜማ ጀምሮ የተፈጠሩ ግርግሮች እና ግራ ማጋባቶች ወደ ተጨባጭ የለውጥ ስጋት ተለውጠው፤ ሀገር እና ሕዝብን በብዙ የፈተኑበት እውነታ ተፈጥሯል። ይህም መንግሥት የቀደሙ የቤት ሥራዎችን በአግባቡ ለመስራት ቀርቶ፤ አሁናዊ የሀገር የሕልውና ስጋቶችን የመቀልበስ እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች ውስጥ እንዲገባ አስገድዶታል።
በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ በአንድ በኩል አደጋ ውስጥ የወደቀውን ሀገረመንግሥት ለመታደግ፤ በሌላ በኩል ለውጡ ይዞት የተነሳውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ለማከም እና እንደ ሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አዲስ የለውጥ ጉዞ ተጨባጭ ወደሆነ የታሪክ ትርክት እንዲለወጥ መንግሥት በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል።
በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ እና በፖሊሲው ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ላለፉት ስድስት ዓመታት ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችሏል። እድገቱ ሀገር እንደ ሀገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና የተመዘገበ መሆኑ፤ ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ዘንድ እንደ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።
ተጠባቂ የውጪ ምንዛሬ ክምችት ባልነበረበት፤ ለመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል አንኳን ስጋት በሆነበት፤ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከስብራት ወደ ውድቀት በፍጥነት እየተጓዘ ባለበት ሁኔታ ኢኮኖሚውን ከውድቀት ታድጎ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ሀገርን ከተጠበቀ ጥፋት የመታደግ ያህል ነበር።
አሁን ላይ እንደሀገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን የገነባነው ኢኮኖሚ ሆነ እያስቀጠልን ያለነው የኢኮኖሚ እድገት እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ አዲስ ጉዞ ተስፋ ሰጭ ጅማሮ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በዚህ ሂደት እያካበትናቸው ያሉ ተሞክሮዎችም፤ በቀጣይ በፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ሀገራዊ መነሳሳት መፍጠር የሚያስችሉ ናቸው።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በይቻላል መንፈስ ተነቃቅተን እና ጉድልትን አርመን ብዙዎች አይሞከርም ያሉትን የዓባይ ግድብ ለፍጻሜ አድርሰናል፤ ከስንዴ ልመና እና ሽመታ ወጥተን ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ስንዴ አምራች ሀገር ሆነናል፤ በምግብ እህል ራሳቸንን ለመቻል እያደረግነው ያለው ጥረት ከተስፋ ወደ ተጨባጭ እውነታ እየተለወጠ ነው፤ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ወደ ልማት አቅም ለመለወጥ እያደረግነው ያለው ጉዞ፤ ባለ ብዙ ሪዞርቶች እና የቱሪስት መዳረሻዎች ባለቤት ከማድረግ ባለፈ የውጪ ምንዛሬ ክምችታችንን እያሳደገው ይገኛል፤ የኮሪዶር ልማት ሥራዎቻችንም አዳዲስ በጎ ባሕል እየፈጠሩና ሀገርን አዲስ ገጽታ እያላበሱ ነው።
ይህ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደሀገር እያስመዘገብነው ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እና ዕድገቱ የፈጠረው ሀብት ያስገኘልን ትሩፋት ነው። ዕድገቱ የስኬት ጅማሬ እንደሆነ ሁሉ፤ የልማቱ ትሩፋቶቹም የልማቱ የበኩር ፍሬዎች ናቸው። በብዙ የሚሰፉ፣ የእያንዳንዱን ዜጋ የለት ተዕለት ሕይወት መለወጥ የሚያስችል ዘርንም በውስጣቸው ያቀፉ ናቸው። እነዚህን የዘር ፍሬዎች ወስዶ የማባዛትና መኸሩን መሰብሰብም የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነትም ግዴታም ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም