የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች ፍቅርና አጋርነትን ማሳየት ይገባል

አዲስ አበባ፡- ሁሉም ዜጋ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች አስፈላጊውን ድጋፍና አጋርነት ማድረግ እንዳለበት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አስገነዘቡ።

የዓለም የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ቀን “መጋቢትን ከዲቦራ ጋር” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በዲቦራ ፋውንዴሽን አስተባባሪነት በመስቀል አደባባይ ተከብሯል። ቀኑ “የድጋፍ ሥርዓቶቻችንን እናሻሽል” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ልጆች ፍቅርና አጋርነትን ማሳየት ይገባል።

የዲቦራ ፋውንዴሽን እነዚህ ዜጎች የትምህርት ማዕድ፣ የጤና ክብካቤ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል።

መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ለነዚህ ዜጎች የሚገባቸውን በማድረግ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች ያማከሉ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዚሁ መሠረት ከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን ለሁሉም ዜጎች የተመቸች ከተማ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።

እነዚህ ዜጎች በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሥራ እድል እንደሚፈጠርላቸው እና በጤና ተቋማት ነፃ ህክምናን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

የዲቦራ ፋውንዴሽን መሥራች አቶ አባዱላ ገመዳ እንዳሉት የቀኑ ታስቦ መዋል ዋና ዓላማ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች እንደማንኛውም ዜጋ መማርና መሥራት እንዲሁም ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ለማሳወቅ ነው።

ፋውንዴሽኑ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በፋውንዴሽኑ የሠለጠኑ ዜጎች በተለያዩ ሥራዎች መሠማራታቸውን ጠቅሰዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር የተወለዱ ዜጎችን መደገፍና አቅማቸውን እንዲያሳዩ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ እነሱን ያማከለ ሥርዓት መዘርጋት መጀመሩንም ተናግረዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You