የሴቷ የመሬትና የንብረት መብት ተጠቃሚነት በተግባር ሲተረጎም

ዜና ትንታኔ

የሴቶች የቤት፣ የመሬትና የንብረት ባለቤትነት መብቶች መከበር ለማህበረ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው። የእነዚህ መብቶች መከበርም የሴቶችን የመወሰን አቅም፣ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዲሁም ፆታ ተኮር ለሆኑ ጥቃቶች እና ለጤና ችግር ካላቸው ተጋላጭነት የመጠበቅ ሁኔታቸውን ያጎለብታል። እነዚህ መብቶች ማረጋገጥ መቻል ለሴቶች የተረጋጋ ሁኔታን፣ ራስን መምራትን እና ነፃነትን ያጎናፅፋሉ።

የኢትዮጵያ የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2024 መሠረት፤ በሕጉ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ከዓለም አቀፋዊ የሠብዓዊ መብቶች ሕጎች ጋር የተናበቡ መሆናቸውንና በመሬትና በንብረት እንዲሁም ቤትን ከማግኘት፣ ከመጠቀም፣ ከመቆጣጠርና ከመግዛት እና ከማስተላለፍ ረገድ እኩልነትን ለማስፈን ወሳኝ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ አበበ ፤ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፤ በተለይ በመሬት እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ አዲስ አስተሳሰብ ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አንድ ባለሀብት መሬት ባይኖረውም አቅም፣ ልምድ እና ካፒታል ካለው መሬት ካላቸው ባለሀብቶች ጋር ውል ገብቶ ወደ ኢንቨስትመንት መግባት ይችላል ይላሉ።

በመሆኑም ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በሰባቱም ክልሎች በአፋር፣ አማራ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች ሴቶችን ጨምሮ 150 ሺህ ባለሀብቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ ይሁን እንጂ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ለመሆን ከባለሙያ እጥረት፣ ከመሠረተ ልማት እና ከፋይናንስ ጉዳይ የሚነሱ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው ይላሉ።

468 ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሴት ኢንቨስተሮችና ባለሀብቶች በ48 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ በአራቱም የግብርና ኢንቨስትመንት ዓይነቶች በአዝርእት፣ የአበባ እና ፍራፍሬ፣ እንስሳት ሀብት እና ኮንትራክት እርሻ (መሬት ተከራይቶ መሥራት) ሴት ባለሀብቶች ግብርና ሚኒስቴር በቅርቡ ባደረገው መርሃ ግብር ላይ አርአያነታቸውን አስመስክረዋል ይላሉ።

356 ሴት ባለሀብቶች በእንስሳት ሀብት ኢንቨስትመንት ተሠማርተዋል፤ በመሆኑም የግብርና ኢንቨስትመንት በተለይ በአበባ ምርት ለበርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር እንዲሁም በማክሮ እና ማይክሮ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ተፅእኖ ይፈጥራል፤ በመሆኑም ዘርፉን ለማጠናከር በመንግሥት በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

የሃቢታት ፎር ሂማኒቲ ኢትዮጵያ የአድቮኬሲ ስፔሻሊስት የሆኑት ኤደን አስራት በበኩላቸው፤ የሕግ ማዕቀፉ ለሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ግልፅ የሆነ አዋጅ ቢኖረውም፤ ሆኖም በተለያዩ የሕግ አስፈፃሚ አካላት ሕጉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተሠራ አይደለም ይላሉ።

ሴቶችን የመብት ተጠቃሚ ማድረግ ከጥቃት ከመጠበቅ ጀምሮ የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ያለው ተፅእኖ ላቅ ያለ ነው፤ ይህን ክፍተት ለመድፈን ሃቢታት ፎር ሂማኒቲ ቁልፍ ዓላማዎች እንዳሉት ጠቁመ የመጀመሪያው ዓላማው ዘላቂ እና ቀጣይነት ያለው የሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማመቻቸት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህን ለማሳካትም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ፤ በፋይናንስ በማብቃት ታች ድረስ በመሄድ ሴቶችን እና ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራ ይሠራል ይላሉ።

የሴቶችን የመሬት መብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠሩ ጠቁመው፤ የሴቶች ተጠቃሚነትን እንዲረጋገጥ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ተግባራዊ ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መለሰ ዳምጤ (ዶ/ር) ፤ የተሻሻለው የመሬት ሕግ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ሴቶች ከወንዶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ እና የፋይናንስ እና ሌሎች ግብዓቶች ተደራሽነት እንዲኖራቸው መብት ይሰጣል ይላሉ። ይሁን እንጂ የቤተሰብ ሕግ ላይ ሊቀረፍ የሚገባው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ወንዱ ቀድሞ የመሬት ባለቤት በመሆን ሴቷን ሲያገባ በትዳር መካከል ችግሮች ሲፈጠሩ በተለይ በገጠሩ አካባቢ እናቶችን ለጉዳት ሲዳርግ ይስተዋላል ይላሉ።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕገ መንግሥት እስከ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ድረስ ሴቶችን ወደ ኋላ የሚጎትት የሕግ አሠራር የለም፤ ሆኖም ልማዳዊ አሠራሮችን ጠንካራ ከመሆናቸው የተነሳ የሴቶችን መብት በመገደብ ይታወቃሉ፤ ለዚህም የሴቶችን መብት የሚያስጠብቀው የሕገ መንግሥቱ አካል የሆነው ሲቪል ኮድ ማናቸውም የሴቷን መብት የሚጎዱ ልማዳዊ አሠራሮች ሥራ ላይ እንዳይውሉ ቢከለክልም ተግባር ላይ ግን ይቀረዋል ይላሉ።

በሴቶች የመሬት መብት ተጠቃሚነት ላይ ሁሉም እንዳመላከቱት፤ እኩል ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሕግ ተግባር ላይ በማውረድ፤ የሀገር ዘላቂ የልማት ግብ ከሆኑት መካከል ድህነት ማጥፋት፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ማረጋገጥ እና ሴቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ የመቋቋም አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You