
“ ከአቅም በላይ ችግር ካልገጠመን በስተቀር በተቀመጠለት ጊዜ ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል”- የድሬዳዋ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፡- የሀረሪ ክልል መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በድሬዳዋ ሪጅን መብራት አገልግሎት እየተሠራ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት በተቀመጠለት ጊዜ የመጠናቀቅ ጉዳይ እንዳሳሰበው ሀረሪ ውሃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ። ከአቅም በላይ ችግር ካልገጠመን በስተቀር በሶስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ እንደሚያጠናቅቅ ድሬዳዋ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል።
የሀረሪ ክልል ውሃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲን ረመዳን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የሀረሪ ክልል በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚከሰተውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በድሬዳዋ ሪጅን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት ከነባራዊ ሁኔታው አንጻር በተባለው ጊዜ የሚጠናቀቅ አይመስልም። በውሉ መሠረት የግንባታ ጊዜው እያለቀ ነው። በመሬት ላይ የሚታዩ ሥራዎች መጓተት ይስተዋልበታል። ባለሥልጣኑ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በተደጋጋሚ ቢጠየቅም በቂ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዲን ገለጻ ፤ሀረሪ ክልል ለአካባቢው ማህበረሰብ በቂ የውሃ አቅርቦት ለማቅረብ የሚያስችል በቂ ጉድጓድ ቢኖራትም ከኤሌክትሪክ ኃይለ መቆራረጥ ጋር በተያያዘ በቂ ውሃ ለህብረተሰቡ ማቅረብ አልተቻለም። በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ከድሬዳዋ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመሆን ለሀረሪ ክልል ውሃ አቅርቦት ብቻ የሚውል መስመር ዝርጋታ (ዲድኬትድ ላይን) ግንባታ እንደመፍትሄ ተወስዶ እየተሠራ ነው።
ባለሥልጣኑ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ክፍያ ቢፈጽምም እስከ አሁን ድረስ በግንባታው ረገድ የተሻለ ለውጥ አለመኖሩን ገልጸው፤ በ2017 ዓ.ም ብቻ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት በውሃ መሠረተ ልማቶች ማለትም በኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎች ላይ በደረሰው ጉዳት ለ24 ሚሊዮን ብር ወጪ መዳረጉን ገልጸዋል።
ተመጣጣኝ አገልግሎት ሳይገኝበት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉ ባለሥልጣኑን እንዳሳሰበው ገልጸው፤ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በተቀመጠለት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል የሚል ግምት የለንም ብለዋል። በተቀመለጠለት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም አቶ ዲኒ ረመዳን ጠይቀዋል።
ድሬዳዋ ሪጅን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፍቅረማርያም አለማየሁ በበኩላቸው ፤ ከአቅማችን በላይ የሆኑ ችግሮች ካልገጠሙን በስተቀር ፕሮጀክቱን ዘንድሮ በሶስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ገልጸዋል።
በሀረሪ ክልል ለመጠጥ ውሃ ችግር የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የውስጥ ችግር እንዳለው ገልጸው፤ ለችግሩን መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ፕሮጀክት ከባለሥልጣኑ ጋር ቀርጸን እየሠራንበት ነው ብለዋል።
ለዚህም እንደመፍትሄ የተቀመጠው ለሀረሪ ክልል መጠጥ ውሃ አቅርቦት ብቻ የሚውል መስመር ዝርጋታ (ዲድኬትድ ላይን) ተለይቶ እየተሠራበት ነው። እስከ አሁን ድረስ ባለው አፈጻጸም 12 ኪሎ ሜትር መሥራት ተችሏል። በአጠቃላይ ከ60 በመቶ በላይ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር አስፈላጊውን ክፍያ በጊዜው አለመፈጸም፣ ለግንባታው ብቁ ኮንትራክተር ማፈላለግ እና በግንባታው ወቅት ያጋጠሙ የባለቤትነት መብት ( right of way) ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከአቅም በላይ ችግር ካልገጠመን በስተቀር በሶስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል።
በባለሥልጣኑ እና በአገልግሎቱ መካከል የነበሩ ችግሮችን ኢፕድ ነሐሴ 25 /2016 ዓ.ም ዘግቧል።
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም