
አንተ ማነህ? ብለው ይጠይቁታል። እርሱም ሌላ ምላሽ የለውም፤ ሁልጊዜም መልሱ “እኔ የሥነ ጽሑፍ ወዛደር ነኝ” የሚል ነው። ከስሞች ሁሉ መርጦ ይህን ስም ለራሱ ሰየመ። የከፋው ሆድ የባሰው ዕለት ስሜቱን መቋጠሪያ፣ ለእንባው ማጀቢያ፣ እህ! ብሎ መተንፈሻውን ብዕሩን አደረገ። ያኔ ግን ከልጅነቱ በቃላት የተሰናኙ ስንኞች መድኃኒቶቹ ነበሩ። ከስሜቱ ግርጌ፣ በኀዘንና በመከፋት መሐከል ተቸንክሮ፣ የውስጡን ሕመም ለማስታገስ በሚያደርጋት መታገል ውስጥ ጥበብን ወለዳት። ከጣር በላይ ሆና ነብሱን ልታክመው ከውስጡ ፈልቃለታለች። “ወንድዬ ዓይናፋር ነው” ይሉታል፤ ከዚህች ጥበብ ጋር ግን ዓይኖቹን ለአፍታ አይነቅልም። ጥበብ ስሜቶቹን ሁሉ ወደ ብርሃን ትቀይርለታለች። ዕንባውን አብሳ በተስፋ ትሞላዋለች። ጥበብን የያዘ፤ በየትኛውም መገፋትና መናጥ ውስጥ ሁሌም ልክ እንደ ረጋ ወተት ነው። ስያሜዎቹ ሁሉ ከግብሮቹ ውስጥ የሚፈልቁለት ነውና “አባት ወንድዬ” የሚሉትም በማንነቱ ውስጥ የተመለከቱለት መልኩ ነው። በብዕር ተወልዶ፣ በሥነ ጽሑፍ አድጎ፣ በግጥም አንቱታን ያተረፈውን ወንድዬ ዓሊን፤ የሚያውቁት ያላሉለት ነገር የለም። ከዚሁ ላይ ጥቂት ለመዝገን ያህል እንጂ፤ ታሪኩን ለመተረክ ማለት አያስደፍረንም፡፡
በሀገራችን በሥነ ግጥም አድማስ ላይ ከሰፈሩ ታላላቅ የጥበብ ልጆቿ መካከል አንደኛው የሆነው ወንድዬ ዓሊ፤ “አምስተኛ ክፍል ሲደርስ እንጉርጉሮዎቼ አንድ ደብተር ሞሉ” እንዳለውም ዕድሜውን ሙሉ ደብተሩን እንደሞላ ኖረ። 25 የግጥም መድብሎችን ለማስነበብ ያበቁት ገና በልጅነቱ ያስነቡት ቀናት መነሻዎቹ ነበሩ። ግጥሞቹ ደግሞ ለግጥም አፍቃሪያን ሁሉ የፈውስ ክኒን፣ የውስጥ መድኃኒት ናቸው። በምናባዊ የምጥ ስሜት ውስጥ ሆኖ የሚያመጣቸው በመሆናቸው በቃላትና ስንኞቹ ውስጥ በዓይን ወደ ልብ የሚገባ ነገር አላቸው።
ወሎ የጥበብ ጡቶቿን ያጠባችው መክኖ እንዳይቀር፣ በማን መጀን እንዳለች፤ ከማህፀኗ የሚወጣው ሁሉ የጥበብ ዘንባባ ነው። ወንድዬም ከዚህቹ ማህፀነ እርጥብ፣ በ1950ዓ.ም ተወለደ። ወረኢሉ እልል! ብላ፣ የታክሏ ካቤ በእቅፏ ተቀብላ፣ ፍሬውን ሕጻን ለጥበብ ልጅ ወለዱ። የወንድዬ የሕይወት አሐዱ፣ የልጅነት ጅምሩ ያማረና የሰመረ ይመስል ነበር። ያውም በልጅነት፣ የእናት ፍቅር እንደ መተንፈሻ ሳንባ ቢሆንም፤ ለወንድዬ ግን ከዚያም በላይ የሚመስል ነው። የቤቱ አምስተኛ ልጅ ሆኖ ቢወለድም፣ ቆፍጣናው ቁጡ አባቱም በልባቸው ለእርሱ የሚሆን ቦታ አላጡም። እንደ መቦረቅ እያለ የጀመረው መልካም ልጅነቱ ግን፤ እንዳይቀጥል ሆኖ ገና ሳይጠነክር ብርቱ ክንድ አረፈበት። ለዚህ ሁሉ ምክንያትም የእናትና አባቱ የትዳር ጎጆ መፍረስ ነበር። የሁለቱ መለያየት ወንድዬንም ከእናት ፍቅር ለየው። ከዚህ የከፋው ቀንም መጣበትና የእንጀራ እናቱን እቅፍ እሾህ አደረገበት። የሻገተን የእናትነት እንጀራ እየበሉ፣ በልጅነት መታወክ ውስጥ ከገቡ ብዙኃን መካከል አንደኛው እርሱ መሆኑን በራሱ አንደበት ገልጾትም ነበር፡፡
ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ወንድዬ ዓሊ፤ ደብተር ሙሉ የስንኝ እንጉርጉሮ፣ በብዕር እንዲያንጎራጉር ያደረገው፣ የእንጀራ እናቱ ነገር በስተመጨረሻ ድንቅ ገጣሚ አድርጎ ሠራው። የለመደውን የእናት ፍቅር አጥቶ፣ ጠረንዋ በናፈቀው ጊዜ፤ አባቱ ለትምህርት በገዙለት ደብተር ላይ ስንኝ አሰናኘበት። እንደማንኛውም ልጅ ሆድ እየባሰው ተከፍቶ ቢያለቅስ፤ እንደማንኛውም ልጅ ስሜቱ በእንባ አርግቦ ብቻ ለጨዋታ የሚሄድ አነበረም። በዚያ ልጅነቱ፤ የእንባ ዘለላውን ወደ ስንኝ አንጓ፣ ስሜቱን ወደ ግጥም ስለመቀየር ያስተማረችው፣ ራሷ ጥበብ ካልሆነች በቀር ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ወንድዬ በእናት ናፍቆት ሲጽፍ፣ በእንጀራ እናት ግልምጫ አሁንም ሲጽፍ፣ በአባቱ ቁጣም ቢሆን ብዕሩን ሲጨብጥ፤ አንድ ሙሉ ደብተር ፈጀና ከላይ በደማቁ “ሲከፉ” የሚል ርዕስ አኖረበት። ይሄኔ እኮ የእርሱ ጓደኞች ሽፋኑ ላይ ሒሳብ፣ አካባቢ ሳይንስ…ብለው የሚጽፉበት ደብተር ነበር።
የወንድዬ ልጅነት ከጥበብ ጋር የተቆራኘው ግጥሞቹን በመጻፍ ብቻም አልነበረም። ከዚህም ሌላ የሌሎችን የብዕር ጠብታዎች ለመቅሰም ቅርብ ነበር። የግጥምና የልቦለድ ሥራዎችን በማንበብ፣ ደራሲያኑን አርዓያ አድርጎ እንደነርሱ ለመሆን ይጥርባቸው ነበር። ወላጅ አባቱ ተምረው ቀለም የገባቸው ባይሆኑም፤ ልጃቸው ሙሉ ሰው እንዲሆንላቸው ከመታተር ግን ወደኋላ የሚሉ አልነበሩም። በየአጋጣሚው ቀያቸውን ለቀው ወደ ከተማው ወጣ ባሉ ቁጥር ሁሉ፣ ለልጃቸው መጽሐፍትን የመሸመት ልማድ ነበራቸው። በዚህ ምክንያትም፤ ወንድዬ ከአስኳላው ውጪ ያለውን ዕውቀትና ጥበብ ለመገናኘት አልተቸገረም። ከብሶትና ከዕንባ ተራራ መሐል የፈለቀችውን የገጣሚነት በረከቱን እንደ ውቅያኖስ ያሰፉለትም፤ እነኚሁ በልጅነት ያነበባቸው መጽሐፍት እንደሆኑ የተናገረው ብዙ ጊዜ ነው። በኋላ በ1965 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመቀጠል፣ ወደ ደሴ ስኅን ትምህርት ቤት ሲያቀና፤ ሲታገለው የነበረውን መከራ ተገላገለው። እፎይ! ያለበትን አዲስ ሕይወት፣ በአዲስ መንፈስ እንደገና ሌላ ኑሮ ጀመረ። ትምህርትና ሕይወትም ቀጠለ፡፡
በ1971 ዓ.ም ወንድዬ ደብረ ዘይት ላይ ተገኘ። ወደዚህ ያመጣው ምክንያትም የኮሌጅ ትምህርቱን ፍለጋ ነበር። በእንስሳት ሕክምና ዘርፍ እየተማረም፤ በጎን መንፈሳዊ ግብር መንቀሳቀስ ጀመረ። በዚያው በደብረዘይት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኳየር ዘማሪነት ተቀላቀለ። በኳየሩ ውስጥም ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ግጥምና የዜማ ሥራዎችን ለማበርከት እንደቻለ ገልጾትም ነበር። “እነርሱ እኮ ግጥሞቼ ሳይሆኑ፤ የዓውደ ዕለት ማስታወሻዎቼ ናቸው። ግጥሞቼ ታሪኮቼ ናቸው” በማለት ነበር የሚገልጻቸው። በጊዜው ወንድዬ ዓሊ የእንስሳት ሕክምናን ለማጥናት በደብረ ዘይት ኮሌጅ ውስጥ መገኘቱ፣ ይህን ወዶና እንስሳት ሐኪም ለመሆን ሽቶ አልነበረም። ይህን ያደረገው በወቅቱ ከነበረውን የቀይ ሽብር መዓት ራሱን ለማስመለጥ በማሰብ ብቻ ነበር። ነገር ግን፤ አንዳንድ ጊዜ ለሰላምታ ከገቡበት ቤት ውሎ ማደር ይኖራል። ወንድዬም ከቀይ ሽብር ለመደበቅ ብቻ በገባበት ትምህርት ተመርቆ፣ በእንስሳት ሐኪምነትና በእንስሳት እርባታ ማኔጀርነት ሲያገለግል ወደ አሥር ዓመታት ያህል ዘለቀ።
ምንም እንኳን ወንድዬ በሥራ ዓለም ውስጥ ተጠምዶ የከረመ ቢሆንም፤ በአርሲ ተመድቦ ሲሠራ በነበረባቸው ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የነብሱ ጥሪ ከሆነችው የብዕር ጥበብ ጋር አልተለያየም። እንዲያውም ብዙ ነገሮቹ ነብስ የዘሩት በእነዚያ ዓመታት ውስጥ በነበረው ቆይታ መሆኑን ይናገር ነበር። “ወፌ ቆመች” በኩር የመድብል ሥራው ስትሆን፤ በመጽሐፉ ውስጥ ያካተታቸውን በዛ ያሉ ግጥሞችን የጻፋቸው በአርሲ ሳለ እንደነበር ገልጾታል። ከጥበብ አፍቃሪው ጋር ያስተዋወቀችውን የመጀመሪያ የግጥም መድብሉን ያሳተማትም በ1984ዓ.ም ነበር። እንግዲህ በእንስሳት ዓለም ውስጥ ሲያክምና ፈር ሲያሲዝ የነበረው ሰው የጻፋት የግጥም ሥራ፤ በግዙፉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኮተቤ ኮሌጅ፣ እንዲሁም በሌሎችም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለማስተማሪያነት ለመጠቀም በቃች። ሲጎርፉለት የነበረው ዝናና አድናቆትም፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጠቅልሎ ወደ ሥነ ጽሑፍ ምሽግ ውስጥ እንዲገባ አደረገው። ከዚህ በኋላም፤ የሥነ ጽሑፍ ባሕታዊ ሆኖ በጥበብ መነነ፡፡
ወንድዬ ዓሊ ስሙ ገኖ ከሚነሳባቸው የግጥም ሥራዎቹ ባሻገር፤ በጎን በነበረው የመንፈሳዊ የጥበብ ጉዞው፣ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ስሙ አይረሴ እንዲሆን አድርጎታል። በዚያ በነበረው የሥነ ጽሑፍ ድርጅት ውስጥ ባልደረባ ከመሆኑም፤ “በመከራ ያበበች” እና “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” የተሰኙ ባለሁለት ቅጽ መጽሐፍ ጽፏል። እነኚህ ሥራዎችም በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ በአማርኛ የተጻፉ የመጀመሪያዎቹ እንደሆኑ ይነገርለታል። ከመጽሐፍ ሥራዎቹ በተጨማሪም፤ በጊዜው ሲያዘጋጀው የነበረ አንድ መጽሔትም ነበር። ወንድዬ በሥነ ጽሑፍ ርቆ እንዲሄድ ያስቻለው ይሄው መጽሔት እንደሆነ ተናግሯል። ወንድዬ ከዚህም ከዚያም የቻለውን ሁሉ በተቻለው መጠን ሲሠራ የነበረው ብዙ ነበርና በዚህና በሌሎችም ተግባራቱ የተደሰቱበት አለቆቹም፣ ለትምህርት ወደ ኬኒያ ሰደዱት። ያኔ ታዲያ ዕድሜው አርባ፣ የነበረው የትምህርት ደረጃም ዲፕሎማ ነበር። እዚህ ጋር ታዲያ፤ ናይሮቢ ውስጥ በኖረባቸው አራት ዓመታት ውስጥ ለብዙዎች የተዓምር ያህል የሚያስደምማቸውን አንድ ነገር ፈጸመ። ዲግሪውን ለመማር የሄደው ወንድዬ፤ በሦስት ዓመታት ውስጥ የማስተርስ ዲግሪውንም ይዞ መጣ። የአዕምሮው ብስለትና ፍጥነት የተለየ ነው በማለትም ብዙዎች አድናቆትን ችረውታል፡፡
ከግጥሞቹና ከሚወደው ብዕር ጋር ለአፍታ ባይለያዩም፣ ሁለተኛውን መድብሉን ለኅትመት ለማብቃት ግን ከመጀመሪያው በኋላ 15 ዓመታትን ጠብቋል። “ውበትና ሕይወት” የተሰኘው ሁለተኛው መጽሐፉ፣ የ“ወፌ ቆመች” ቅጽ-2 ሲሆን፤ ለንባብ የበቃውም በ1998ዓ.ም ነበር። የመጀመሪያ ሥራው የነበረችውን “ወፌ ቆመች”ን አብዝቶ ከመውደዱ የተነሳ ሊቋጫት አልወደድምና ከ2ኛው ቅጽ በኋላ እንደገና 3ኛውን ቅጽ ለማውጣት ሽር ጉድ ማለት ጀመረ። የሦስተኛውን ቅጽ ግጥሞችን፣ በየማኅበራዊ ሚዲያ ሲያጋራቸውና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያነባቸው ቢከርምም፤ ከሁለተኛው በኋላ ለ17 ዓመታት ያህል በመጽሐፍ ለመታተም ሳይችሉ ቀርተዋል። ይሁንና በእነዚህ 17 ዓመታት ውስጥ ሌሎች አራት የግጥም መድብሎችን አሳትሟል። በዚህ መሐል የጤናው ሁኔታም ጥሩ ስላልነበረ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ነበር። የወፌ ቆመች ሦስተኛ ቅጽ መጽሐፍ ሆና ለመመልከት የጓጉ ወዳጅ አድናቂዎቹ ብዙ ጠብቀው አሁንም አለመቻሉን ሲመለከቱ፣ ይጠይቁትና እንዲያሳትመው ያበረታቱም ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርበት ከነበሩ ወዳጆቹ ጋር በቀልድም ሆነ በቁም ነገር ስለ 3ኛዋ ቅጽና ስላለበት ሁኔታ ካነሱ የሚላቸው እንዲህ ነበር፤ “እየታመምን እንጽፋለን፣ እየጻፍን እንታመማለን” በማለት ቀልድ ቢጤ እውነታውን ጣል ያደርጋል። ከእነዚያ ሁሉ ዓመታት በኋላ ግን፤ የጓጉለትን እንደምንም ሊያስነብባቸው ሆነ።
ከሁለት ዓመታት በፊት በጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት፤ ለታላቁ ገጣሚ አክብሮት ለመግለጽ የተደረገ አንድ ልዩ መሰናዶ ተሰናድቶ ነበር። ወዳጅ የጥበብ አጋሮቹ፣ የሚያደንቁትና የሚያደንቃቸው በርካቶችም ታድመውበታል። ይህ ሳይሆን ሞት ቀድሞ ቢሆን ኖሮ ለሁሉም እጅግ የሚያስቆጭ ይሆን ነበር። ምክንያቱም፤ ሞት ከሕይወት ላይ ነጥቆ ለመውሰድ ሲያንዣብብበት የነበረበት ጊዜ ነበር። በዚያ የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት መድረክ ላይ፣ ስለ ወንድዬ ዓሊ ብዙ ተነግሮለታል። የዘመን ዐሻራ የሆኑ በርካታ የግጥም ሥራዎቹ ተነበውለታል። ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከታክልዋ ከካቤ መንደር እስከ ደብረ ዘይትና አዲስ አበባ የተጓዘበትን የሕይወትና የጥበብ መንገድ ተቃኝቷል። በዚህ ሁሉ መንገድ ላይ የነበረ ታሪኩን በብዕር አሰናስኖ፣ በዕለቱ ታዳሚው ፊት ቆሞ የተረከለት አረጋ ጋሻው ነበር። “የዚህን ሰው እና የዚህን ብዙ ሰው አጭር የሕይወት ታሪክ ለመጻፍ የተነሳሳሁት…” በማለት የከተበለትን ድንቅ የታሪክ ሰነድ ይገልጠዋል፡፡
የወንድዬ ታላቅነት በግጥም ሥራዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በሚያውቁት ሁሉ ልብ ውስጥም ጭምር ነው። “አባት ወንድዬ” ብለው ከሚጠሩት ቤተሰቦቹ ባሻገር ሌሎች ብዙዎችም አሉበት። በዕድሜ የሚያንሱት ብቻ ሳይሆኑ፣ የሚበልጡትና እኩያዎቹ ሳይቀሩ በዚህ ስም የሚጠሩበትን ምክንያት አንዳንዶች ሲገልጡት፤ መንፈሱ ስለሚገዝፍባቸው ነው ይላሉ። በሕይወት ሳለም ሆነ በሞት ከተነጠቀ በኋላ፤ ስለ እርሱ ሲያወሩ የሚደመጡ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም መሐል አንደኛው ደረጀ በላይነህ ነው። “ወንድዬ ዓይናፋር ገጣሚ ነው። ገጣሚ ብቻ ሳይሆን፤ ደራሲ፣ አርታዒ፣ ባዮግራፈር፣ የምርምር ሰው፣ የፊልም ስክሪፕት ጸሐፊ…ወዘተም ነው” ሲል ገልጦ የማይጨርሰው ተሰጥዖ እንደነበረው ይናገራል።
ብዙዎች እርሱን እንደተመለከቱት አድርገው መልኩን ይገልጹታል። ራሱን ወንድዬን እስቲ ራስንህን በቃላት ግለጸው ቢሉት፤ በአጭሩ “የሥነ ጽሑፍ ወዛደር” የሚል ነው። ራሱን እንዲህ ሲል የሚገልጸው፣ አንድ ምክንያት ስላለውም ነው። ወዛደርነት የመሸከም ግብር ቢሆንም፤ ወዛደር ግን የማይሸከመው ነገር የለም። ለመሸከም የምፈልገው ይህንን ነው ብሎ ጉልበቱን የሚገድብበት ነገር የለውም። ያገኘውን እህል ቢሆንም እንጨት፣ ሻንጣ ቢሆን ስልቻ፣ ፌስታልም ይሁን ዘንቢል የትኛውንም ከመሸከም ወደኋላ አይልም። ወንድዬም ራሱን በሥነ ጽሁፍ ወዛደርነት መመሰሉ፤ ብዕሬን ጨብጬ የቀለም ጉልበቱ እስካልተሟጠጠ ድረስ የትኛውንም ነገር ከመጻፍ የምገታና ራሴን በአንድ ዘርፍ የምገድብ አይደለሁም ለማለት ነው፡፡
ወንድዬ የእውነትም የሥነ ጽሑፍ ወዛደር እንደነበር ከሚያረጋግጡልን ነገሮች አንዱ፤ ለ22 ዓመታት ያህል ያለምንም ተጨማሪ ሥራ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ የነበረ መሆኑ ነው። በቀደመውም ሆነ በአሁኑ ዘመን የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆኖ መኖር የማይታሰብ ቢሆንም፤ እርሱ ግን ለተወለደበት ጥበብ ያለ ስስት ራሱን የሰጠ እንደነበረም የሚያሳይ ነው። ታዲያ በኪራይ ቤት ውስጥ ተቀምጦና የአብራክ ክፋይ ልጆቹንና ቤተሰቡን ይዞ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ እንድናደንቀው ያደርገናል። እርሱ ግን ከዚህም ባሻገር ለብዙ ችግረኞች ደራሽ አባትም ጭምር ነበር። “በሀገራችን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ፤ ለድፍን 22 ዓመታት የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆኖ የኖረ ከወንድዬ ሌላ ማንም የለም” በማለት አንዳንዶች ሲናገሩም እንሰማለን።
ወንድዬ አሊ ማለት ከቬነስ በላይ የሚያብረቀርቅ፣ ከሜርኩሪ በላይ የሚያንጸባርቅ ደማቁ የጥበብ ኮከብ ነበር። ነገር ግን፤ የችሎታውን ያህል ሳይታይለት፣ የሠራውን ግማሽ እንኳን ሳይነገርለት ኖሯል። የእርሱን ሥራዎች ለመማሪያነት ያዋሉ ግዙፍ የትምህርት ተቋማት ቢሆኑም፣ እርሱ ግን ገዝፎ ሳይወጣ ቀርቷል። የችሎታውን ልክ ለመግለጽ የተቸገሩ አድናቂና ወዳጆቹ ብቻ ሳይሆኑ፤ በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሊቅ የምንላቸውም ጭምር ናቸው። ከእነዚህም አንደኛው ዘሪሁን አስፋው ሲሆን፤ “የሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ሥራዎቹን እየጠቀሱ፣ ስለ ውበታዊና ሥነ ጽሑፋዊ ቀለማቸው ብዙ ብለዋል። የወንድዬን ግጥሞች የሥነ ጽሑፍ ልኬት አድርገው “የሥነ ግጥም ማኑዋል” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደማሳያ የዘረዘሩት ሁለተኛው ሰው ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ ናቸው። ሊሒቃኑ ብቻ ሳይሆኑ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በእርሱ ሥራዎች ላይ ያደረጉ ተማሪዎቻቸውም ከ15 በላይ እንደደረሱ ይነገራል፡፡
ወንድዬ ዓሊ ጥበብን እንደ ወዛደር ሁሉን ተሸክሞ፣ በማያርጥ የብዕር ጉልበቱ ግጥምን አነገሣት። ሥነ ጽሑፍን አወደሳት። እንደ ዓይናፋርነቱ ሁሉ ከዓይን ተከልሎ ባይዘመርለትም፤ የጥበብ ዓይኖች ከዓይኖቹ አፍታም ሳይነቀሉ ወደ መቃብር ተሰናብተውታል። የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ወንድዬ ጨርቄን ማቄን ሳይል ጥበብን አኑሮ ጥበብን ይዟት ሄደ፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም