ጋሽ አሰፋ ጉያ፡- የጥበብ አድባር

ደራሲና ሰዓሊ ናቸው፤ በቱሪዝም ዘርፍ ለ40 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል። ብዙዎች በተፈጥሮ፣ በባህል፣ በማኅበራዊ ትርጉማቸው ጥልቅ በሆኑ በፍልስፍና የተቃኙ ግጥሞቻቸው ያውቋቸዋል። በኢኮኖሚክስና ቱሪዝም ኢኮኖሚክስ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ዘልቀዋል። በሞዛይክ አርት፣ በሰዓሊነት እና በሥነ ጽሑፍ ዐሻራቸውን አንጋፋነታቸውን አስመስክረዋል። በደርግ ዘመነ መንግሥት ወጣቶች በንቃት በተሳተፉበት ፖለቲካ ውስጥ ከፊት መስመር ተሰልፈው ለእስር እስከመዳረግ ደርሰዋል። እኚህ ታላቅ የጥበብ ሰው የዛሬው «የሕይወት ገጽታ» እንግዳችን የራህማቶ፣ የሰምና ወርቅ፣ የከንፈር ወዳጅ ደራሲ የሞዛይክ አርቲስትና ሰዓሊ አሰፋ ጉያ ናቸው።

ትውልድና እድገት

ወይዘሮ ማሬ ጎበና ትጉህ የነበሩ የገጠር ነጋዴ ነበሩ። የመጨረሻና አስራ አንደኛ ልጃቸውን ነብሰጡር በነበሩበት ወቅት ለንግድ አህዮቻቸውን ላይ እቃቸውን ሸክፈው ራቅ ወዳለ የገበያ ቦታ ለመሄድ ወንዝ ሲሻገሩ በአጋጣሚ ደራሽ ወሰዳቸው፤ ነገር ግን ከአደጋው በተዓምር መትረፍ ቻሉ። በድንገት መትረፋቸውን ለማሳየት የልጃቸውን የቀድሞ ስም ‹‹ታምሩ›› (ዛሬ በዚህ ስያሜ ባይጠሩበትም) በሚል ሰየሙት። አጋጣሚውን ለማስታወስ ከመኖሪያ አካባቢያቸው በብዙ ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው ዝቋላ ተራራ ላይ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ልጃቸውን ክርስትና አስነሱ።

በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር የዛሬው አንጋፋ የጥበብ ሰው ጋሽ አሰፋ ጉያ በ1948 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ከቢሾፍቱ /ደብረዘይት/ 7 ኪሎ ሜትር እርቃ በምትገኘው ዶሎ የገጠር መንደር የተወለዱትና ለቤተሰቡ 11ኛ የልጅ በረከት የሆኑት። በዚህ ምክንያት በእናታቸው ማሬ ጎበና በስስት አይን እየታዩና ከስር ስራቸው እያሉ አደጉ።

በጋሽ ጉያ ገመዳ ቤተሰብ ውስጥ ጥበብ አድባሯን አጥልታለች። ጋሽ አሰፋ በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው የታዋቂውና አንጋፋው ሰዓሊ የክቡር ዶክተር ለማ ጉያ ወንድም ናቸው። በሁለቱ የሀገር ባለውለታ ወንድማማቾች መካከል የ28 ዓመታት የእድሜ ልዩነት አለ።

የጉያ ቤተሰብ በኢትዮጵያ በታላላቅ የጥበብ ሥራቸው ታዋቂ ነው። ይህ ቤተሰብ ከታዋቂው አርቲስት ለማ ጉያ ጀምሮ እስከ ወንድሙ ቱሉ ጉያ እና እህት ወንድሞቻቸው ድረስ በኢትዮጵያ ጥበብ ላይ ትልቅ ዐሻራን ያሳረፈ ነው። የፈጠራ ችሎታቸው በጠንካራ የቤተሰብ ትስስር ስሜት የኢትዮጵያን ባህል፣ ተፈጥሮ፣ እና ማንነት የሚገልፁ ተወዳጅ ሥራዎችን አበርክተዋል።

ለጋሽ አሰፋ በተለየ መልኩ ወደ ሞዛይክ አርትና የሥነ ጽሑፍ ሥራ መሳብ የእናታቸው ተፅዕኖ ጉልህ ነው። በታዳጊነታቸው እናታቸው ሰፌድና የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ሲሰፉ፣ በእርሻ ሲሳተፉ፣ የሸክላ ሥራዎችና ልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎችን ሲያከናውኑ በቅርበት የመመልከት አጋጣሚው ነበራቸው። ‹‹ልዩ ሰው ነበረች፤ ሞፈር ቀንበር ጠምዳ ታርሳለች፤ ከብቶች ማሳ እንዳያበላሹ በዙሪያው የሱፍ አበባ ስትተክል እና በእሾሁ ስትከላከል አስታውሳለሁ›› በማለት በአካባቢው ልዩ ባሕሪ የነበራቸው ብልህ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

ጋሽ አሰፋ እህት ወንድሞቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ከእናታቸው ጋር ገበያ አብሮ የመሄድ ዕድል ነበራቸው። ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ በደማቁ የገጠር ገበያ ውስጥ ከሀገሬው ሰው ጋር እየተጋፉና ከእናታቸው ስር ስር ይላሉ። አባታቸው ገና በ8 ዓመታቸው በሞት ስለተለዩ የእናትና ልጅ ቅርበት ጥብቅ ነበር።

አስኳላን አሀዱ ብለው የጀመሩት በቄስ ትምህርት ቤት ነበር። ፊደል ቆጥረው፣ ዳዊት ደግመው፣ ውዳሴ ማሪያም አጥንተውና ዝማሬ ላይ ተሳትፈው ወደ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅንተዋል። ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከወንድማቸው የክብር ዶክተር ለማ ጉያ አስተባባሪነት ባቋቋሙት ከታ የሚባል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የቀለም ትምህርትን የጀመሩት። በዚህ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ዘልቀዋል፤ በአፄ ልብነ ድንግል ደግሞ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀዋል፤ በንግሥት ተናኜ ወርቅ ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተለዋል። ጋሽ አሰፋ በትምህርታቸው ንቁና ጎበዝ ነበሩ። በጊዜው በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) አየር ኃይል በመኖሩ የጦር አውሮፕላን የማብረር ሕልም እንዲኖራቸው ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል።

‹‹ሐረረ አካዳሚ ተወዳድሬ አልፌ ነበር፤ የኤርፎርስ ፓይለት ልሆን ነበር። ወንድሜ ነው ትምህርትህን አርፈህ ተማር ብሎ ያስቀረኝ›› ይላሉ በጊዜው የነበራቸውን አብራሪ የመሆን ፍላጎትና ጥረት ሲናገሩ። በትውልድ መንደራቸው አካባቢ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ተራሮችን እየሰነጠቁ ልምምድ ሲያደርጉ ማየታቸው የጋሽ አሰፋ የዘወትር ምኞት አብራሪነት እንዲሆን ምክንያት ነበር።

‹‹አባቴ ጉያ ገመዳ ልጅ እያለሁ ፀጉሬን እያሻሸ ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ ይለኝ ነበር›› የሚሉት አንጋፋው አርቲስት ጋሽ አሰፋ፤ የእናታቸው ተፅዕኖና ከአባታቸው የወረሱት ራዕይ የዛሬውን መሠረት የጣለ እንደነበር ይናገራሉ። የክቡር ዶክተር ለማ ጉያ መጽሐፍቶችን (በተለይ በራሺያ ደራሲዎች) የተፃፉትን ማንበባቸው በትምህርት ቤት ከጓደኞቻቸው ጋር ጥልቅ ውይይቶችን ማድረጋቸው አመለካከታቸው ከቀረፁት የልጅነትና የወጣትነት ትዝታዎቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ። ለእግር ኳስ ጨዋታ ልዩ ፍቅርም ነበራቸው፤ ከትምህርት መልስ በደብረዘይት በነበረ ክለብ ውስጥ የ10 ቁጥር አጥቂነት ሚናን ወስደው ተጫውተዋል።

የፖለቲካ ተሳትፎ

ጋሽ አሰፋ የአስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሻሸመኔ ጦራ በሚባል አካባቢ እድገት በኅብረት ዘመቱ። በጊዜው የነበረውን ሥርዓት በመቃወምም በቀጥታ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ የገቡት በዚያው ጊዜ ነበር። ነገር ግን ጥረታቸው ብዙም ሳይሳካ ለእስር ተዳረጉ። ብዙም ሳይቆዩ ሲፈቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በኮተቤ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በኮተቤ ለመምህርነት በዩኒቨርሲቲው ደግሞ በኢኮኖሚክስ ነበር የሚማሩት። ከኮተቤ ሲመረቁ ግን ዩኒቨርሲቲውን አቋርጠው ወደ ጎጃም ደብረ ማርቆስ (ቢቸና) በመሄድ የሂሳብ መምህር ሆኑ።

‹‹በጊዜው የፖለቲካ ተሳትፎ ንቁ ነበርን፤ ኢሕአፓ አባል ሆነን ነዋሪውን እናደራጅ ነበር›› የሚሉት ባለታሪካችን በዚህ ምክንያት ለእስር ተዳርገው ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ (ቶርች) ማስተናገዳቸውን ያስታውሳሉ። ለሦስት ዓመታት ፍርድ ቢወሰንባቸውም በእስር ቤት ውስጥ በነበራቸው ማኅበራዊ ተሳትፎና የጥበብ ውጤቶችን በዓውደ ርዕይ ያቀርቡ ነበር፤ ተሳትፏቸውና መልካም ሥነምግባራቸው ከተፈረደባቸው ጊዜ ቀደም ብለው እንዲፈቱ አድርጓል። ከእስር እንደወጡ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት በሀገር ውስጥ የመቆየት ፍላጎት የነበራቸው ባይሆንም ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዳግም በመቀጠል በኢኮኖሚክስ ተመርቀዋል።

ለፖለቲካ ተሳትፏቸው ዋነኛ ምክንያት ለገበሬው የመቆርቆር እና መወገን መነሻ ነበር። የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴ፤ የወንድማቸውና የጄኔራል ታደሰ ብሩ ተፅዕኖ፤ በወቅቱ በነበረው ርዕዮተ ዓለም ላይ ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉ እርሳቸው ላይም ተፅዕኖ ነበረው። በእነዚሀ ምክንያቶች በወጣትነታቸው በተለይ በትምህርት ቤትና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ብዙ ትግል አጋጥሟቸዋል። በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ሆነዋል። በውጤቱም በደርግ ተይዘው ለዓመታት በእስር አሳልፈዋል።

እንደ ሰዓሊና ደራሲ

አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ፖለቲካ ውስጥ ብቻ አልነበረም ተሳታፊ የነበሩት። ይልቁንም በጊዜው ይተላለፍ በነበረው የለገዳዲ ራዲዮ ጣቢያ ሥነ ጽሑፎችን በመፃፍና በመላክ ይታወቁ ነበር። አለፍ ሲልም የሞዛይክ አርት፣ የስዕል ሥራ ይሠሩ ነበር። ከራሳቸው ጋር ጥሞናን ሲይዙ በጥበብ ሥራዎች መጠመድ ምርጫቸው ነበር። ስዕልና ሥነ ጽሑፍን በትምህርት ሳይሆን ራሳቸውን ነበር ያስተማሩት። በእርግጥ ቀጥተኛ ባይሆን የወንድማቸው ተፅዕኖ ነበረበት። ልክ እንደ ወንድማቸው ሰዓሊ ቱሉ ጉያ የአርት ስኩል ተማሪ ባይሆኑም የቤተሰቡ መገለጫ የሆነውን እውቀት ግን ራሳቸውን በማስተማር ተክነውታል። በጊዜው በኢትዮጵያ የስነ ጥበብ ዘርፍ ላይ አሁን በሕይወት የሌሉት ወንድማቸው ሰዓሊ ለማ ጉያ (ዶክተር) የገዘፈ ስምና ዝና ነበራቸው።

‹‹ጋዜጦች ላይ እጽፍ ነበር፤ ስዕሎቼንም በዓውደ ርዕይ ማሳየት የጀመርኩት ተማሪ እያለሁ ነበር›› ይላሉ ጋሽ አሰፋ ጊዜውን መለስ ብለው እያስታወሱ። የመጀመሪያ ሥራቸውን በጎጃም ደብረ ማርቆስ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር ለእይታ ያቀረቡት።

ትዝታቸውንና ቀደምት ሥራዎቻቸውን በማስታወስ በፃፉት ሰምና ወርቅ የተሰኘ መጽሐፍ ላይ የመጀመሪያውን ዓውደ ርዕይ ያቀረቡበትን ጊዜ በዚህ መልኩ ያስታውሱታል። ‹‹በግልም ሆነ በቡድን ከቀረቡት የስዕል ትዕይንቶች ላይ መሳተፍ አሀዱ ያልኩበት ብቻ ሳይሆን፣ ለሥነ ጥበብ ሕይወቴ እርሾ የሰነቅሁበት፣ የእስራትና የእስር ቤቱን አይረሴ ሕይወት የሚያስታውሰኝ የሥዕል ዓውደ ትርዒት በትውስታ መልክ ለመዘከር ወሰንኩ፡፡ ዘመኑ 1971 ዓ.ም ሲሆን፣ ቦታው ደግሞ ጐጃም ክፍለ ሀገር ደብረ ማርቆስ ከተማ በተለምዶ ‹‹ደመላሽ›› ተብሎ ይጠራ ከነበረው ወህኒ ቤት እስራት ላይ ሳለሁ በአጭሩ ከተቀጨውና ዛሬ በሕይወት ከሌለው ሰዓሊና ክራር ደርዳሪ ውድ ጓደኛዬ ከአርቲስት ዘውዱ ባይሌ ጋር በጋራ የሥዕል ኤግዚቢሽን አቅርበናል›› ይላሉ።

ጋሽ አሰፋ በጥበብ ሥራቸው ተወዳጅ ናቸው። ሥነ ጽሑፎች ላይ ከመሳተፍ፣ ግጥሞችን ከመፃፍ ባሻገር ከወንድማቸው አንጋፋው ሰዓሊ ለማ ጉያ እና ቱሉ ጉያ ጋር በጋራ ያቀረቡት ዓውደ ርዕይ በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል። በተለይ በሞዛይክ ጥበብ ይታወቃሉ። የድንጋይ፣ የወረቀት፣ የከሰል ድንጋይ እና ብረት በመጠቀም ለስሜት የቀረቡ፣ ጥልቅ ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸው ለዓይን ማራኪ የሆኑ የጥበብ ሥራ ይሠራሉ። ልዩ ተሰጧቸው እና ትጋተቸው በኢትዮጵያ ጥበብ ውስጥ ትልቅ ሰው አድርጓቸዋል።

‹‹ከሁለቱ ወንድሞቼ ጋር (ለማ ጉያ ዶክተር እና ቱሉ ጉያ ጋር) ዓውደ ርዕይ በ1975 ዓ.ም አቅርቤ ነበር›› በማለት በትዝታ ወደኋላ የሚወስዱን ጋሽ አሰፋ፤ በስዕል ትርዒቱ ሻምበል አርቲስት ለማ ጉያ (የክቡር ዶክተር) 29 ሥራዎች የሰዓሊ ቱሉ ጉያ 40 ሥራዎች እንዲሁም የእርሳቸው 11 ሥራዎች ለአንድ ሳምንት ያህል በአዲስ አበባ የከነማ ምክር ቤት የቲያትር ባህል አዳራሽ ለእይታ ቀርቦ እንደነበር ይናገራሉ።

ጋሽ አሰፋ የስዕልና የሞዛይክ ሥራዎችን በጥረታቸው በመማር ከተሰጥዖ ጋር በማዋሓድ ነው የሚሠሯቸው። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ ተጠቅመው በርካታ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር። ‹‹እንቅልፍ ብዙም አልተኛም ነበር›› ይላሉ ጊዜውን መለስ ብለው እያስታወሱ። ከሞዛይክና ስዕል ባሻገር ሌሊት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ጭምር ይሠሩ እንደነበር እየተናገሩ።

ጋሽ አሰፋ ከሰዓሊነታቸው በተጨማሪ ደራሲና ገጣሚ ናቸው። በኪነጥበብ ውስጥ ጥልቅ ተሳትፎ ካለው ቤተሰብ የተገኙ እንደመሆናቸው የእርሳቸውም ዐሻራ በዚህ ረገድ ጉልህ ነው፤ መጽሐፎችን እና ግጥሞችን ጽፈው አሳትመዋል። በተለይ ራህማቶ የተሰኘው መጽሐፋቸው ብዙ ጊዜ ታትሞ የወጣ ሲሆን ሁለት የግጥም መድብሎችንም (የከንፈር ወዳጄ እና ሰም እና ወርቅ) አሳትመዋል። ራህማቶ በ1981 ታትሞ ለገበያ ሲቀርብ ሁለት ጊዜ 10 ሺህ ኮፒ መሸጥ የቻለ በጥቅሉ 20 ሺህ ኮፒ የተሸጠ ተወዳጅ የድርሰት ሥራ ነው።

እንደ ሞዛይክ ጥበቡ፣ አሰፋ መጽሐፎቹም ተወዳጅ ናቸው። በተለይ በዚያን ዘመን ሰም እና ወርቅ በኢትዮጵያ የአብዮቱ ትውልዶች በሚያስተላልፈው መልዕክት እና ቅኔ በብዙ ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ ነበር። የጋሽ አሰፋ ጽሑፎች በ1974 ዓ.ም የኢትዮጵያ አብዮት እና የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ያሳደረ ነበር። በወቅቱ ሥነ ጽሑፍ ትልቅ ሚና እንደነበረው ያስታውሳሉ። ተማሪዎች መልዕክቶችን ለማሰራጨት እና ድጋፍ ለማግኘት ጋዜጣዎችን፣ ግጥሞችን እና በራሪ ጽሑፎችን በስፋት ይጠቀሙ ነበር። ይህንን ጊዜ መለስ ብለው የሚያስታውሱት ባለታሪካችን ‹‹በእነዚያ ጊዜያት ለመቃወም ከምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ሥነ ጽሑፍ አንዱ ነበር›› በማለት ጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበሩ መጣጥፎችንና ግጥሞችን እንዴት እንደፃፉት ያስታውሳሉ፤ የዚህ ውጤት ለደራሲነታቸው ትልቁን እርሾ የጣለም ነበር። ከ1966 ጀምሮ በጥበብ ዙሪያ ለነበራቸው ዐሻራ ፖለቲካ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየም ውስጥ ሦስቱን ጨምሮ የአሰፋ ሞዛይክ የጥበብ ሥራዎች በወሳኝ ስፍራዎች ተቀምጠዋል። ሥራዎቹ በመኖሪያ ቤታቸውና በክቡር ዶክተር ለማ ጉያ ፋውንዴሽን የአርት ኤግዚቢሽን ማሳያ ውስጥ አሁንም ድረስ ይገኛሉ። በሥነ ጽሑፉ ረገድ አሁንም ታትመው ለአንባቢያን ያልደረሱ ሥራዎች በእጃቸው ላይ ይገኛል። ጊዜው ሲፈቅድ ለኅትመት እንደሚበቁም ነግረውናል።

አንጋፋው የጥበብ ሰው የበርካታ ሰዓሊያንና ደራሲያን ወዳጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከአንጋፋዎቹ ሰዓሊ ታደሰ መስፍን፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጋር በቅርበት ተገናኝቶ የመጨዋወት ዕድል ነበራቸው። ከደራሲዎችም ጋሽ ስብኅት ገብረእግዚአብሔር፣ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን እና ሌሎች አንጋፋ ደራሲዎች ጋርም ደጋግሞ ይገናኙ ነበር። ከእነዚህ ታላላቅ የጥበብ አድባሮች ጋር ሲገናኙ ስለራሳቸው ከማውራት ይልቅ ማዳመጥን እና ልምድ መውሰድን ምርጫቸው ያደርጉ ነበር፤ በዚህም በብዙ መማራቸውን ይገልፃሉ።

ብዙውን ጊዜ የጥበብ ሥራዎቻቸው የግል ፍልስፍና ነፀብራቆቻቸው ናቸው። አብዝተው ተፈጥሮን ይሞግታሉ፣ ይመራመራሉ። ለሰዎች ቀላል የሚመስሉ ግን ምላሽ ስለሚፈልጉ ጥያቄዎች በስዕል ሸራዎቻቸው ላይ፣ በሞዛይክ ጥበብ ላይ እንዲሁም በግጥሞቻቸው ላይ ርዕሰ ጉዳይ አድርገው ያነሳሉ። በአንድ አካባቢ አሊያም ሀገር የታጠረ ምልከታ የላቸውም ዓለም አቀፋዊ ይዘት፣ ጠንካራ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይበልጥ ይስባቸዋል። ይህንን እይታቸውን ደግሞ ወደ ሕዝብ ሲያደርሱት ግርምትን የሚያጭር ‹‹እንዴት በዚህ መልኩ አየኸው›› የሚል ጥያቄን የሚያስነሳ ሕይወትን ተላብሰው ይቀርባሉ። ለዚህ ምሳሌ አንጋፋውና ተወዳጁ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ከወንድሞቻቸው ጋር ባቀረቡት ዓውደ ርዕይ ላይ ተገኝቶ የሰጠው አስተያየት ምሳሌ ሊሆን ይችላል። እይታው እንደሚከተለው ይነበባል።

‹‹ከስዕል ወደ ሥነ ግጥም፤ ከግጥም ወደ ሥነ ስዕል በመሸጋገር ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለማንሳት የመጣርህን ያህል እንደ ከባድ ርዕሶችህ ሁሉ የሥራህም ፍሬ በዚሁ ክብደት ውስጥና ስር ተውጠዋል። ጥረትህ በጣም ጥሩ ነው። የውስጣዊ ዓላማህን ግዝፈት በብሩሽህ ለመቀመር የሚፈጅብህ እድሜና ልምድ ግን እሩቅ በመሆኑ ሙከራህን አታቋርጥ›› የሚል ይዘት አለው። አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ አሰፋም ይህንን ምክር ገንዘባቸው አድርገው አያሌ ተወዳጅ የሞዛይክና የስዕል ሥራዎችን ለሀገራቸው ማበርከት ችለዋል።

የሎሬቱ ጥያቄና የጋሽ አሰፋ ቁጭት

‹‹በርካታ የሚያስቆጩ ዕድሎች ሳልጠቀምባቸው እንደ ዋዛ ያመለጡኝ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቶቹ መካከል ሁለቱ ከአዕምሮዬ፤ ደጋግመው ይመላለሱብኛል›› ይላሉ አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ አሰፋ። ከዚህ መካከል ከሎሬቱ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በቀዳሚነት ያነሳሉ። ስለቁጭታቸው ምክንያትም ከዚህ እንደሚከተለው ያብራራሉ።

እንዲያው እግር ጥሎን ከሎሬት ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረ መድኅን መንገድ ላይ ሳይቀር ድንገት ስንገናኝ መኪናውን ያቆምና በቅድሚያ ‹‹ጃርሲ አካም?›› (አዛውንቱ እንዴት ነው?) ይለኝ ነበር፡፡ ስለ ታላቅ ወንድሜ ጋሽ ለማ ጤንነትና ሥራ መጠየቅን የሰላምታው መክፈቻ በማድረግ፡፡ ከዚያ ሰላምታውን ወደ እኔ የሚመልሰው ‹‹የት ደረስክ?›› በማለት ነበር፡፡ ‹‹በርታ እያለኝ ነው›› ከማለት ባለፈ ለጥያቄው ትኩረት ሰጥቼ፤ በተገናኘን ቁጥር ‹‹የት ደረስክ?›› የሚለኝ ምን ተስፋ ጥሎብኝና ምንስ ከኔ ጠብቆብኝ እንደነበር ሳልጠይቀው ቀረሁና የልቡን ሳያጫውተኝ አለፈ በማለት ስለምክንያቱ ይናገራሉ።

‹‹ታዲያ ዛሬ ዛሬ ምነው ጊዜ ወስጄ በቁምነገር ጠይቄው በነበርና ከዚያ አልፎ ተርፎም፡ ስለልምዱና ስለአተያዩ አዋይቼው ከሕይወት ልምዱና ከባሕረ-ሃሳቡ የሚቻለኝን ያህል ዝቄ ቢሆን ኖሮ እያልኩ እቆጫለሁ›› በማለት በተለይም ከሁለቱ ታላቅ ወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባቀረቡት የሥነ ስዕል ትርዒት ወቅት ከአስተያየት መስጫ መዝገብ ላይ ያሰፈረውንና ኮፒው በመጽሐፋቸው የተካተተውን መልዕክቱን ባነበቡ ቁጥር የቁጭት ስሜቴ ይበልጥ እንደሚያይልባቸው ይገልፃሉ፡፡

ሌላኛው የሕይወት ገጽ

ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ ባለቤት ነች፤ ምድረ ቀደምትና ቁጥር ስፍር የሌላቸው የቱሪዝም ሀብቶችን የያዘች ምድር። ጋሽ አሰፋ ስለሚኖሩባት ምድር ጠንቅቀው ያውቃሉ። መስሕቦቿን፣ ታሪኳን እና የቱሪዝም መዳረሻነቷን የተመለከቱ ጉዳዮችም በተማሪ ቤት ሆነው በሥነ ጽሑፍ መልክ ለባህልና ቱሪዝም ይጽፉ ነበር። ይህንን ተከትሎ በወቅቱ በነበሩት የቱሪዝም ኮሚሽነር ጥያቄ መሠረት የተመረቁ ተማሪዎች ወደ ሥራ ገበታ ይመድብ የነበረውን ማዕከላዊ ፕላን ርሳቸውን ወደ ኮሚሽኑ እንዲመድባቸው ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ የትምህርት ታሪክ ያላቸው የኢኮኖሚ ምሩቅ፣ ደራሲና ሰዓሊ ጋሽ አሰፋ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ቀጥሎም ከሮም ትምህርት ቤት በቱሪዝም ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን፣ የያዙት የያኔው ወጣት ትምህርት እና ሁለቱንም ጥበባዊ ሙያዊና ሥራቸውን በሚዛን አስቀምጠው ሀገራቸውን በርካታ ዓመታት ማገልገል ችለዋል።

አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ አሰፋ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ድርጅት የሽያጭ ተቆጣጣሪ ሆነው ነበር መሥራት የጀመሩት ። ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የሥራ መደቦች ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን ከነዚህም መካከል የግዥ ኃላፊ፣ የቢዝነስ ፕሮሞሽን፣ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። የቱሪዝም ንግድ ሥራ ድርጅት የተመሠረተው በ1957 (የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) በስድስት ሠራተኞች እንደነበር እኚሁ አንጋፋ ባለሙያ አጫውተውናል። የዚህ ድርጅት ዋና ዓላማው ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት መስጠት እና የኢትዮጵያን የጥበብ እና የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ለገበያ ማቅረብ ነው።

አንጋፋው የጥበብ ሰው በቱሪዝም ንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ የራሳቸውን ዐሻራ አኑረዋል። የኢትዮጵያን የዕደ ጥበብ ሥራዎች፣ ፊደላት፣ ባህላዊ ቁሳቁሶች እና ለቱሪዝም መስሕብነት የሚያገለግሉ ሀብቶች በገበያ ውስጥ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር ሠርተዋል። በዚህ ተፅዕኖ ድርጅቱ ከውጭ ካምፓኒዎች ጋር ትብብር እንዲፈጥር አስችለዋል። የኢትዮጵያ የቱሪዝም ምርቶች ወደ ገበያ እንዲወጡ እና እውቅናን እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት ውስጥ በርካታ ሽልማቶችንም ማግኘት ችሏል።

ቤተሰብ

ጋሽ አሰፋ ከወይዘሮ መስከረም ብዙአየሁ ጋር በ1980ዎቹ ትዳር መሥርተው። በረከት አሰፋና ጋሻው (በሥጋ ባይወልዱትም ልጄ የሚሉት) ጨምሮ ሁለት ወንድ ልጆች አሏቸው። ከድሮም ከልጆች ጋር መጫወት እና ከቤተሰብ ጋር መልካም ጊዜን ማሳለፍ ምርጫቸው ነው። ለልጃቸው ስንኝ የመቋጠር ተሰጥዖን ተጠቅመው ‹‹ኩኩ በረከቴ›› የሚል ግጥም ጽፈውለታል። ለበርካታ ዓመታት የገና ልደት በዓል ሲመጣ የገና አባት በመሆን ከወዳጅ ዘመዶች ጋር ተወዳጅ ጊዜ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። ባለቤታቸው አሁን ላይ በንግድ ሥራ ተሠማርተው እንደሚገኙ አጫውተውናል።

ወጣቶች ይህንን ቢማሩ

አንጋፋው የጥበብ ሰው ለዚህ ትውልድ የሚያቀብሉት መልዕክት አለ። በልጅነታቸው ዛሬ ያሉበትን ዝንባሌ እና ተሰጥዖ በቀላሉ እንዳልለዩት ይገልፃሉ። ለዓመታት የሠሩበትንና ጉልህ ዐሻራ ያሰፈሩበትን የሥነ ጥበብና ድርሰት ሙያ በውስጣቸው እንዳለ የተረዱት ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት የወጣትነት ዘመናቸው እንደሆነ ይገልፃሉ።

ጋሽ አሰፋ እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮ፣ ከቤተሰብና ከማኅበረሰብ ተፅዕኖ የሚመነጭ ተሰጥዖ አሊያም መክሊት እንደሚኖረው ያምናሉ። ከዚህ ተነስተው ወጣቶች ተሰጥዖን መለየት ቢችሉ በዚያ ላይ ቢሠሩ ብዙ ሳይለፉና ጊዜ ሳያባክኑ የሚፈልጉት ስኬት ላይ መድረስ እንደሚችሉ ይናገራሉ። እያንዳንዱ ሰው ማስተዋል ቢችል፣ ከመጽሐፍትም ከሰዎችም መማር ቢቻል ልኅቀት ላይ መድረስ ይቻላል ይላሉ። ‹‹ተፈጥሮ ብዙ ታስተምራለች›› የሚል እምነት ያላቸው ጋሽ አሰፋ ክረምት ከበጋ ሲለዋወጥ ሌሎች የተፈጥሮ ዑደቶችም የሕይወት ክህሎት የሚያስተምሩ በመሆኑ ማስተዋል እንደሚያስፈልግ ለወጣቶች ይመክራሉ። በመሆኑም ማሰላሰል፣ ማስተዋል እና ከታላላቆቻችን መማር የጥበብ መጀመሪያ ይሁን በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበራቸውን ቆይታ ይቋጫሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You