
የትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ የናረውን የእንቁላልን ዋጋ ለማቃለል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንቁላሎችን ከቱርክ እና ደቡብ ኮሪያ ሊያስገባ ነው። የዋጋ ንረቱን በከፍተኛ ሁኔታ ለማቃለል በተጨማሪ ከሌሎች ሀገራት ለማስገባት በውይይት ላይ መሆኑን ባለሥልጣናቱ አረጋግጠዋል። “ለአጭር ጊዜ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንቁላሎችን ለማስገባት እየተነጋገርን ነው” ሲሉ የግብርና ጸሐፊ ብሩክ ሮሊንስ በዋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተከሰተውን የወፍ ጉንፋን (በርድ ፍሉ) ለመከላከል የአሜሪካ አስተዳደር አንድ ቢሊዮን ዶላር ማቀዱን ተከትሎ የአሜሪካ ገበሬዎች በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶሮዎችን ለመቀነስ ተገደዋል። ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የእንቁላል የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ቃል ቢገቡም ዋጋው ከባለፈው ዓመት 65 በመቶ በላይ ጭማሬ ያሳየ ሲሆን በዚህም ዓመት እንደገና 41 በመቶ እንደሚንር ተገምቷል።
ሮሊንስ መሥሪያ ቤታቸው አዳዲስ የእንቁላል አቅርቦቶችን ለማግኘት ከሌሎች ሀገራት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ቢገልጹም ሀገራቱን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።”የእኛ የዶሮ ርባታ እንደገና ሲመለስ እና ምናልባትም በሁለት ወራት ውስጥ የእንቁላል ኢንዱስትሪ ሲያብብ ወደ ራሳችን የእንቁላል ክምችት እንመለሳለን” ብለዋል።
የፖላንድ እና የሊትዌኒያ የዶሮ ርባታ ማኅበራት እንቁላል መላክ በሚቻልበት ሁኔታ ከአሜሪካ ኤምባሲዎች ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።”በየካቲት ወር ላይ በዋርሶ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፖላንድ ወደ አሜሪካ ገበያ እንቁላል መላክ ትፈልግ እንደሆነ ድርጅታችንን ጠይቋል” ሲሉ የብሔራዊ የዶሮ ርባታ እና መኖ አምራች ዳይሬክተር ካታርዚና ጋውሮንስካ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የአሜሪካ የግብርና ዲፓርትመንት የእንቁላልን ዋጋ ለማስተካከል፤ ክትባት፣ የአርሶ አደሮች እፎይታ ፕሮግራም እንዲሁም ባዮ ደህንነትን ፕሮግራሞችን ጨምሮ አምስት እቅዶች የተካተቱበት አንድ ሚሊዮን ዶላር በጀት ይዞ ነበር። የትራምፕ አስተዳደር ለንግድ የሚውሉ የእንቁላል ማምረቻዎች በነጻ የማማከር አገልግሎት እንዲሁም የወፍ ጉንፋን (የበርድ ፍሉ) ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እስከ 75 በመቶ የሚደርስ ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑ አስታውቀዋል።
አቪያን ፍሉ በአሜሪካ ውስጥ ለዓመታት ዶሮዎችን ቢጎዳም ከሶስት ዓመት በፊት የተከሰተው ወረርሽኝ ከ156 ሚሊዮን በላይ ዶሮዎችን እና ወፎችን ገድሎ የእንቁላል ዋጋን የማይቀመስ አድርጎታል። ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸው የሕዝቡን ብሶት በመንካት የእንቁላል ዋጋ አንደኛ አጀንዳቸው አድርገውት እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም