
እሥራኤል ከሰሜን ጋዛ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች መጠለያ ሆኖ በማገልገል በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 27 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ዳር አል አርቃም በተሰኘው ትምህርት ቤት በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ በርካቶች መቁሰላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር የአካባቢውን ሆስፒታል ዋቢ አድርጎ ጠቅሷል።
የእሥራኤል መከላከያ በበኩሉ ትምህርት ቤቱን ሳይጠቅስ የሐማስ የትዕዛዝ እና የቁጥጥር ማዕከልን መምታቱን ገልጿል። የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ቀደም ብሎ እሥራኤል በ24 ሰዓታት ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት 97 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቆ ነበር። ከአየር በተጨማሪ የምድር ላይ ጥቃት የጀመረችው እሥራኤል በበኩሏ ሰፋ ያለ የፍልስጤምን ግዛት እንደምትወር ተናግራለች።
የጋዛ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማሕሙድ ባሳል በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል ብለዋል። ቃል አቀባዩ አክለውም መንታ ልትወልድ የተቃረበች ነፍሰ ጡር ከሦስት ልጆቿ፣ ከባለቤቷ እና ከእህቷ ጋር እንደጠፋች ተናግረዋል።
የእሥራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ በጋዛ ከተማ ጥቃት የደረሰበት ስፍራ የሐማስ ተዋጊዎች ጥቃቶቻቸውን የሚያቀነባብሩበት ስፍራ መሆኑን ነው። በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል በርካታ ርምጃዎች መወሰዳቸውንም መግለጫው አክሏል።
የእሥራኤል መከላከያ በተጨማሪ በጋዛ ምሥራቃዊ ሸጃያ አካባቢ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የሲቪል መከላከያው ገልጿል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የዓይን እማኝ እንደተናገሩት “ድንገተኛ ኃይለኛ ፍንዳታ” ከእንቅልፋቸው እንደቀሰቀሳቸው ተናግረዋል። ፍንዳታውም የተሰማው አያድ በተሰኙ ጎረቤታቸው ቤት ነው ብለዋል።
ከእሥራኤል መከላከያ በኩል ወዲያውኑ ምላሽ ባይሰጥም ሐሙስ ጥዋት የሸጃያ እና አራት አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው በአስቸኳይ ወደ ምዕራባዊ ጋዛ ከተማ እንዲሄዱ አስገዳጅ መመሪያ አስተላልፏል። “የአሸባሪዎችን መሠረተ ልማት ለማውደም፤ በከፍተኛ ኃይል እየሠራን ነው” የሚል ማስጠንቀቂያም የታከለበት መሆኑን ቢቢሲ ጠቅሶ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም