
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ታሪፍ በመጣላቸው ምክንያት በሌሎች ሀገራትና በአሜሪካ አክሲዮን ገበያ ከ2020 ወዲህ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ። በእስያ-ፓስፊክ ቀጣና አክሲዮን ገበያ ለሁለተኛ ቀን የወረደ ሲሆን፤ እኤአ በ2020 በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከወደቀ በኋላ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ገበያ አስጨናቂ ቀናት ገጥሟቸዋል።
ናይክ፣ አፕል እና ታርጌት ከትላልቅ ኩባንያዎች መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆኑ፤ ሁሉም ኩባንያዎች ከዘጠኝ በመቶ በላይ ሽያጫቸው መውረዱ ተነግሯል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዓለም አቀፍ ምርቶች ላይ በጣሉት ዝቅተኛ 10 በመቶ ታሪፍ የፌዴራል ገቢን በማሳደግ እና የአሜሪካን አምራቾች ወደ ሀገራቸው በመሳብ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት የአክሲዮን ገበያ ያሽቆለቆለ ሲሆን፤ በእንደዚህ አይነት አለመረጋጋት ወቅት ደኅንነቱ የተጠበቀ ጥሪት ተደርጎ የሚታየው ወርቅ ደግሞ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የዋሽንግተን የንግድ አጋር የሆኑትን ቻይና እና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ምርቶች ላይ የሚፈፀም ከፍተኛ ታሪፍ ጥለዋል።
በጥቅሉ 54 በመቶ ታሪፍ የተጣለባት ቻይና እና 20 በመቶ የተጣለበት የአውሮፓ ኅብረት አጸፋዊ ርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአውሮፓ ድርጅቶች በአሜሪካ ያቀዱትን ኢንቨስትመንት እንዲሰርዙ ጥሪ አቅርበዋል።
ታሪፍ ከሌሎች ሀገራት የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣል ታክስ ሲሆን፤ ረቡዕ እለት ትራምፕ ያሳወቁት ታሪፍም ከ100 ዓመታት በኋላ የምርቶች ዋጋ እንዲያሻቅብ ያደርጋል እየተባለ ነው። የዓለም የንግድ ድርጅት ርምጃው በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀ ሲሆን፤ ድርጅቱ በዚህ ዓመት የንግድ መጠን በአንድ በመቶ ሊቀንስ እንደሚችልም ግምቱን አስቀምጧል።
ነጋዴዎችም ታሪፉ የዋጋ ግሽበት እንደሚጨምር እና እድገትን ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ርምጃቸው የዓለምን የንግድ ሥርዓት የቀረፀው አሜሪካ መር ነፃ ንግድ ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ቁማር መሆኑን አጣጥለዋል። “በጣም በጥሩ መንገድ እየሄደ ይመስለኛል” ብለዋል።
“አንድ ታካሚ ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግለት አይነት ነው። እናም ትልቅ ነገር ነው። ይህ በትክክል በዚህ መንገድ ይሆናል” ሲሉ ገልፀዋል።” ገበያው እያደገ ይሄዳል። ስቶክ ገበያው ያድጋል። ሀገሪቱ ታድጋለች” ሲሉም አክለዋል። የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት አዲሱ ታሪፍ የድርድር ስልት አይደለም ቢሉም፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ከንግድ አጋሮች ጋር ለመነጋገር በራቸው ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሐሙስ ዕለት አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ሀገራቸው ከአሜሪካ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ በመጣል አፃፋ ትወስዳለች ብለዋል። ኩባንያዎች የታሪፉን ጫና ብቻቸውን መቋቋም፣ ከአጋሮቻቸው ጋር መጋራት አሊያም ለደንበኞቻቸው በማስተላለፍ ሽያጫቸውን አደጋ ላይ መጣል በሚሉ ምርጫዎች ተከበዋል።
ርምጃው ከዓለም ኢኮኖሚ ከ10 እስከ 15 በመቶ ድርሻ ባላቸውን የአሜሪካ ሸማቾች ላይ ግዙፍ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም