
ሃንጋሪ፤ የኔታንያሁን ጉብኝት ተከትሎ ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደምትወጣ አስታወቀች:: በሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ገርግሊ ጉልያስ፤ ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለመንግሥታዊ ጉብኝት ወደ ሀገሪቱ ከገቡ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ገርግሊ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ጽሑፍ፤ “ሃንጋሪ ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ትወጣለች” ብለዋል። “መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ እና ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በመከተል ሐሙስ ዕለት [ከፍርድ ቤቱ አባልነት] የመውጣት ሂደቱን ይጀምራል” ሲሉ የሀገሪቱ መንግሥትን ውሳኔ አስታውቀዋል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርባን፤ ለኔታንያሁ የጉብኝት ግብዣ ያቀረቡት የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኅዳር ወር ላይ ማዘዣ እንደወጣባቸው ነበር። ኦርባን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሀገሪቱ ውስጥ “ምንም ተፈጻሚነት” እንደማይኖረው ተናግረው ነበር። የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዳኞች ኅዳር ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡት ኔታንያሁ በጋዛ ጦርነት ተፈጽመዋል ለተባሉ የጦርነት ወንጀሎች እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች “የወንጀል ኃላፊነት” እንዳለባቸው ለማመን የሚያስችሉ “ምክንያታዊ መሠረቶች” መኖራቸውን በመግለጽ ነው።
ኔታንያሁ፤ ይህንን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “ፀረ-ሴማዊነት” ሲሉ ተቃውመውታል። ሃንጋሪ ከ125ቱ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት መሥራች አባል ሀገራት አንዷ ነች። አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ቻይና እና እሥራኤል እንዲሁም ሌሎች ሀገራት ፍርድ ቤቱ በግዛታቸው ውስጥ ሥልጣን እንዲኖረው እውቅና አልሰጡም።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የተመሠረተበት የሮም ስምምነት አባል በሆኑ ግዛቶች ውስጥ በሚፈጸሙ የዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም የጦርነት ወንጀሎች የተወነጀሉ አካላትን የመክሰስ ሥልጣን እንዳለው ይታወቃል።
እሥራኤል ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በግዛቷ ውስጥ ሥልጣን አትቀበልም። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ እ.አ.አ በ2021 ባሳለፈው ውሳኔ በወረራ ስር ባለው ዌስት ባንክ፣ ምሥራቅ እየሩሳሌም እና ጋዛ ሥልጣን እንዳለው ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ፍልስጤማውያን በአባልነት በመቀበላቸው ነው ተብሏል።
ሃንጋሪ ከፍርድ ቤቱ የአባልት ስምምነት ለመውጣት መወሰኗን በጽሑፍ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ማሳወቅ ይጠበቅባታል። ፍርድ ቤቱን ባቋቋመው የሮም ስምምነት አንቀጽ 127 መሠረት ከአባልነት የመውጣት ጥያቄ ተፈጻሚ የሚሆነው ከአንድ ዓመት በኋላ ነው። በእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ማዘዣው የወጣ በመሆኑ በተለመደው አሠራር መሠረት የሃንጋሪ ባለሥልጣናት ኔታንያሁን አስረው በሄግ ለሚገኘው ፍርድ ቤት መስጠት እንደነበረባቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ አባል ሀገራት ሁልጊዜም ፍርድ ቤቱ የሚያስተላልፋቸውን ትዕዛዞች ላይፈጽሙ ይችላሉ። የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን እንደማይቀበለው ያስታወቀ ሲሆን ኔታንያሁም ከኅዳሩ እስር ማዘዣ በኋላ ሀገሪቱን ጎብኝተዋል። ኔታንያሁ ትናንት በሃንጋሪ ያደረጉት ጉብኝት ከዚህ ትዕዛዝ ወዲህ ወደ አውሮፓ ያደረጉት የመጀመሪያው ጉዞ ነው። የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃንጋሪ ሲደርሱ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ክሪስቶፍ ሳላይ ቦብሮቭኔትስኪ በቡዳፔስት አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ ወታደሮች በቀይ ምንጣፍ ዙሪያ ተደርድረው ነበር። ኔታንያሁ፤ ከወታደራዊው አቀባበል በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርኣብንን ለማግኘት ወደ ወታደራዊው ቤተ መንግሥት አምርተዋል። የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ኔታንያሁን እና የቀድሞውን መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንትን ለማሰር ያወጣውን ትዕዛዝ እና ክሱን በጽኑ የተቃወመችው እሥራኤል፤ አቤቱታዋን አቅርባለች። ሁለቱ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤቱ ያለውን ሥልጣን እና የትዕዛዙን ቅቡልነት ተቃውመዋል።
የፍርድ ቤቱ ዳኞች ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፉ እሥራኤል እንደሞተ በምትገልጸው የሀማስ ወታደራዊ አዛዥ መሐመድ ዴኢፍ ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥተዋል። ኔታንያሁ በሃንጋሪ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት እሥራኤል ሀማስ ላይ ጫና ለማሳደር በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ባጠናከረችበት እና አዲስ ወታደራዊ ኮሪዶር እየመሠረተች ባለበት ወቅት ነው። እሥራኤል በፍልስጤም ግዛት ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውም እየተዘገበ መሆኑን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም