መልካም ጉርብትና እና የጋራ ተጠቃሚነት ለሕዝቦች አብሮነት!

ሀገራችን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ባለቤት ነች። በነዚህ ረጅም ዘመናት ውስጥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም ከመኖር ባለፈ፤ በየትኛውም ሀገር ላይ ጦርነት አውጃ፣ ነጋሪት አስጎስማ እና ሰራዊት አሰልፋ ወደ ግጭት የገባችበት ወቅት የለም። በአብዛኛው ከውጪ ኃይሎች ጋር ያደረገቻቸው ጦርነቶች ራስን ከመከላከል እና ሉአላዊነትን ከማስከበር ጋር የተያያዙ፤ ስለ ነጻነት እና ፍትህ የተደረጉ ጦርነቶች ናቸው።

ሀገሪቱ ካለችበት ቀጣና ጂኦ- ፖለቲካ እና የሀገሪቱ ዕድገት እና መለወጥ ሁሌም የብሔራዊ ጥቅማቸው ስጋት አድርገው በሚያዩ ኃይሎች ጋር በተያያዘ፣ በየዘመኑ የተለያዩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ/የውክልና ጦርነቶችን ለማስተናገድ የተገደደችባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።

በአንድ በኩል ለነጻነት እና ለፍትህ፣ በሌላ በኩል ታሪካዊ ጠላቶቻችን በፈጠሯቸው የውክልና ጦርነቶች ሕዝባችን ከጦርነት ጋር በተያያዘ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል። በዚህም ከማንም በላይ የሰላም ዋጋው ምን ያህል ውድ እንደሆነ መገንዘብ ችሏል። ስለ ሰላም የሚዘምራቸውም ዝማሬዎች በሰላም እጦት ተፈትነው የጠሩ እና ከልብ የመነጩ እንዲሁም ተአማኒነታቸው ለጥያቄ የማይቀርብ ነው።

ለኢትዮጵያውያን የሰላም ጉዳይ ከስትራቴጂክ ተጠቃሚነት ጋር የሚያያዝ አይደለም፣ ከእያንዳንዱ ዜጋ ማኅበረሰባዊ ስነልቦና ጋር የተጋመደ፣ የሰላም እጦት ካስከፈለን እና እያስከፈለን ካለው ያልተገባ ዋጋ አኳያ የሚሰላ ኪሳራውም የከፋ እንደሆነ ከሌሎች ቁስል እና ስብራት ሳይሆን በራሳችን የሕይወት ትርክት ያረጋገጥነው እውነት ነው።

በተለይም አሁን ላይ የጀመርነውን ድህነትን ታሪክ የማድረግ እልህ አስጨራሽ የዚህ ትውልድ ትግል ስኬታማ እንዲሆን የሰላም አበርክቶ መተኪያ የሌለው እንደሆነ እንደ ሀገር ተረድተን እየተንቀሳቀስን ነው። የምናዜማቸው የሰላም ዝማሬዎች ግባቸው ነገን ብሩህ ከማድረግ እና ሀገርን ከትናንት ወደ ፊት የማሻገር የለውጥ እሳቤ ጋር የተንሰላሰለ ነው።

እንደሀገር የጀመርነው የመደመር የፖለቲካ -ኢኮኖሚ ሕሳቤ የዜጎችን፣ የሀገርን ከዛም አልፎ የጎረቤት ሀገራትን እና ዓለም አቀፍ ስትራቴጂክ አቅሞችን ደምሮ የመንቀሳቀስ እሳቤን መሰረት ያደረገ፤ ለግጭት እና ለጦርነት፣ ከዚህ ለሚመነጭ የትኛውም አይነት ሀገራዊም ሆነ አካባቢያዊ የሰላም እጦት የተጋለጠ አይደለም። ሰላም፣ መልማትንና መበልጸገን የጋራ እሴት አድርጎ የሚወስድ ነው።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያሉ ሕዝቦች እጣ ፈንታ ተመሳሳይ ነው በሚል፣ የሀገራቱን አቅሞች አስተባብሮ ቀጣናዊ ልማት እና የኢኮኖሚ እድገትን የመፍጠር ራእይን የሰነቀ፣ ለዚህ በሚቻለው ሁሉ ግጭት እና ጦርነት ቀስቃሽ አስተሳሰቦች እና ትንኮሳዎችን ተቋቁሞ መሻገር የሚያስችል የስነ ልቦና ዝግጁነት እና የዓላማ ቁርጠኝነት የተላበሰ ነው።

የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ያላቸውን አቅም አቀናጅተው በተሻለ ጉርብትና እና በወንድማማችነት መንፈስ፤ በሰጥቶ መቀበል መርኽ የጋራ ጠላታቸውን ድህነት እና ኋላ ቀርነትን በተባባረ የልማት ክንድ ማሸነፍ የሚችሉበትን የጋራ እሳቤ እና መተማመን በመፍጠር ወደ ተጨባጭ የዕድገት ጉዞ ተያይዘው የሚሄዱበትን ፍኖተ ካርታም ያበጀ ነው።

ይህ ኢትዮጵያውያን ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ካሳለፏቸው አስቸጋሪ ቀናቶች፣ ማንነታቸው ከተሰራበት መንፈሳዊ፣ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች፤ ከዚያም በላይ ዛሬ ላይ ድህነት እና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድረግ ከጀመሩት አዲስ የታሪክ ጉዞ አኳያ እያዜሙት ያለው የሰላም ዜማ ለሌሎች ስለ ሰላም መነቃቃትን እንጂ ስጋትን የሚፈጥር አይደለም።

የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ እና ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ መሆንን ተገንዝበው፣ ለዘላቂ የጋራ ልማት እራሳቸውን ማዘጋጀት፣ ለሕዝቦች ተጠቃሚነት የተሻለውን አማራጭ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ባልተገባ መንገድ እና ስሌት ጉርብትናን እና ወንድማማችነት የሚጎዱ ተግባራትን ከማድረግ መቆጠብም ብልህነት ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You