
ቻይና በአደንዛዥ እጽ ወንጀል ሳቢያ አራት ካናዳውያንን በሞት መቅጣቷን የካናዳ ባለሥልጣን አስታወቀ። የተገደሉት ሁሉም ግለሰቦች ጥምር ዜግነት የነበራቸው ሲሆን ማንነታቸውም ይፋ እንዳልተደረገ የካናዳ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ መናገራቸው ተሰምቷል።
በሀገረ ካናዳ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ‹‹ካናዳ ሃላፊነት የጎደላቸው አላስፈላጊ አስተያየቶችን ከመስጠት እንድገትቆጠብ ማሳሰባቸው ሲገለጽ ለዓመታት ግንኙነታቸው ሻክሮ የነበረው ሁለቱ ሀገራት የበለጠ ውጥረት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ እየተባለ ይገኛል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ርምጃ መውሰዱን የገለጸ ሲሆን ኤምባሲው በበኩሉ ግለሰቦቹ ለፈጸሙት ወንጀል ጠንካራ እና በቂ ማስረጃ አለው ሲል ምላሽ ሰጥቷል። በማከልም ካናዳ የቻይናን የፍትህ ሉዓላዊነት እንድታከብር ጠይቋል።
ቻይና የጥምር ዜግነትን ጽንሰ ሃሳብ የማትቀበል ሀገር ስትሆን በአደንዛዥ እጽ ወንጀሎች የተከሰሱ ሰዎችን በከባዱ የምትቀጣ ሀገር መሆኗም ይታወቃል። ሆኖም የውጪ ሀገር ዜጎችን በሞት መቅጣት ለቻይናም ቢሆን ከዚህ ቀደም የተለመደ ድርጊት እንዳልነበር ነው የተገለጸው። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ የግለሰቦቹን ክስ ለወራት በቅርበት ሲከታተል እንደነበር እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ጨምሮ ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የሞት ቅጣቱን ለማስቆም መሞከራቸው ተገልጿል።
ግለሰቦቹ ምህረት እንዲደረግላቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የጠየቁ ቢሆንም ከሞት እንዳልታደጋቸው ነው የተገለጸው። በማንኛውም ክስ የሞት ቅጣት ተግባራዊ እንዳይሆን ካናዳ መወትወቷን እንደምትቀጥል ግሎባል አፌይርስ ቃል አቀባይ ሻርሎት ማክሊየድ ለካናዳ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
ቻይና ከባድ የምትላቸውን ወንጀሎች እንደአደንዛዥ እጽ፣ ሙስና እና ስለላ ለመሳሰሉት የሞት ቅጣት ፈጻሚ ሀገር ናት። የሞት ቅጣት በሚስጢር የሚያዝ ቢሆንም የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቻይና በዓለም ላይ ከፍተኛ የሞት ፍርድ ከሚፈጸምባቸው ሀገራት አንዷ ናት በማለት ይገልጻሉ።
‹‹የቻይና ባለሥልጣናት በካናዳ ዜጎች ላይ የፈጸሙት ኢ ሠብዓዊ የሞት ቅጣት ለካናዳ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል›› ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ካናዳ ኬቲ ኒቪያባንዲ መተቸታቸው ሲሰማ ‹‹ለተጎጂ ቤተሰቦች ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶናል። እናም በዚህ በማይታሰብ ሁኔታ ኀዘን ላይ የወደቁ ቤተሰቦች ልባችን ከእናንተ ጋር ነው›› ማለታቸው ተሰምቷል። አክለውም ‹‹በቻይና የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሊሆንባቸው ያሉ የካናዳ ዜጎች እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ የት እንደደረሱ ለማይታወቁ ሃሳባችን ከእናተ ጋር ነው የሚል›› መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 የካናዳ ዜግነት ያለው ሮበርት ሎይድ ሼለንበርግ በቻይና በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል። የካናዳ መንግሥት ይህንን ያወገዘ ሲሆን ጉዳዩም መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም። ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት የሞት ቅጣት ሰለባ ከሆኑ ካናዳውያን መካከል አለመካተቱ ታውቋል።
የካናዳ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆሊ ‹‹በጠንካራ ማውገዛችን ከመቀጠላችን በተጨማሪ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ላሉ ካናዳውያን ምህረት እንጠይቃለን›› ማለታቸው ተሰምቷል። ካናዳ የቻይናን የቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ ሜንግ ዋንዙን የአሜሪካ አሳልፋችሁ ስጡኝ ጥያቄ በአውሮፓውያኑ 2018 መያዟን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ቅራኔ መፈጠሩ ይታወሳል። ብዙም ሳይቆይ በወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ካናዳውያንን በቁጥጥር ስር ያዋለች ሲሆን አሁን ላይ ሁለቱም ተለቀዋል። ቀደም ብሎ የሻከረው የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት የሞት ፍርድ በተፈረደባቸው አራት ካናዳውያን የበለጠ መሻከሩ ታውቋል። መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም