
“ከቃል እስከ ባህል” የጉባዔው መሪ ሃሳብ ነበር:: ይሄ መሪ ሃሳብ ደግሞ ዝም ብሎ የተቀመጠ አይደለም:: ይልቁንም ቃልን ገልጦ መገኘት፤ ቃልን አልቆ መፈጸም፤ የመፈጸም ልምምድን አሳድጎ ባህል ማድረግ፣ ብልፅግና ፓርቲ እንደ መንግሥት ከምርጫ ማግስት በተጓዘበት መንገድ ሁሉ እያሳየ የዘለቀበት መርሑ በመሆኑ እንጂ::
እናም ፓርቲው ሁለተኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ይሄንን መሪ ሃሳብ ሲመርጥ፤ የፓርቲ እሳቤና የተግባር ልምምድ የወለደውን ባህል በሁሉም አመራርና አባላቱ ለማስረጽ፤ ወደ ሕዝቡም ለማውረድ ካለው መሻት አኳያ፤ በቀጣይ መንገዱም ሊፈጽም ካስቀመጠው አቅጣጫ አንጻር በመቃኘት ነበር::
ቃልን በተግባር በመግለጥ ሂደት የተፈጠረው የመፈጸም ልምምድና ባህል ታዲያ፤ ፓርቲው እንደ መንግሥት እየፈጸማቸው የመጡት ተግባራት ውጤታማነትን የገለጡ ብቻ ሳይሆን፤ የቀጣይ መንገዱንም ያሳለጡ መሆናቸው ግልጽ ነው:: ለዚህም ነው የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው መክፈቻ ንግግራቸው፤ “ቀጣዮቹ ወራት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሥራት የምናደርስባቸው ይሆናሉ፤” ሲሉ መደመጣቸው::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው መክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፤ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጓዝንበት መንገድ ከጥልቅ እንቅልፍ እና ከብዙ ዕዳ የተነሳንበት ምዕራፍ ነው:: በዚህ ምዕራፍ የታሰረ ይፈታ፣ የተሰደደ ይመለስ፣ ያኮረፈ ይታረቅ፣ የተባረረ ይመለስ፣ የተከፋፈለ ይደመር፣ ቶርቸር ይብቃ፣ አቧራ ይራገፍ፣ ፀጋ ይገለጥ ብለን በተግባር ይሄንኑ አሳይተናል:: ይሄ የመነሳት ምዕራፍ ነበር:: አሁን ግን ይሄን ሁሉ የፈጸምንበት የመነሳት ምዕራፍ አብቅቶ የማንሰራራት ዘመን ተተክቷል:: ይሄ የማንሰራራት ዘመን ደግሞ ብሥራትን ይዞ የሚመጣ ነው::” ሲሉ፣ ያለፈውን አብራርተዋል:: የወደፊቱንም አመላክተዋል::
አያይዘውም፣ “የማንሰራራት ዘመን ሲባል የቁልቁለትና የጎንዮሽ ጉዞ የሚያበቃበት ዘመን ማለት ነው:: በመሆኑም ከጉባዔው በኋላ ያሉት ወራት ፕሮጀክቶችን የምናስመርቅበት፣ ሪቫን የምንቆርጥበትና ዐሻራ የምናስቀምጥበት፤ በጥቅሉም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሥራት የምናደርስባቸው ናቸው፤” በማለት በማንሰራራት ዘመን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሥራት የሚያሰሙባቸውን መንገዶችና ዓውዶች ጠቆም አድርገው፤ ለቀጣይም ቃል ገብተው ነበር::
እርግጥ ነው፤ ቀደም ሲል ቃልን በተግባር እየገለጠ አሳይቷል:: አሁንም መሰል ነገርን እንዲያውም አልቆ ለመግለጥ በሁለተኛው ጉባዔው በፕሬዚዳንቱ አማካኝነት ሌላ ቃል ገብቷል:: ስለዚህ በጉባዔው ማግስት ባሉ ወራቶች ቃል የሚገለጥባቸውን ዓውዶች ሕዝቡ መጠበቁ አይቀሬ ነበር:: ይሄን የሚገነዘበው ገዢ ፓርቲም፣ የገባውን ቃል ለመግለጥ፤ የሕዝቡን መሻት ለመፈጸም ጊዜ አልወሰደም:: ቃልን በተግባር በመግለጥ የማንሰራራት ዘመኑን ብሥራት በየተራ ማሰማትም ጀመረ::
ከጉባዔው ማግስት ጀምሮም የበርካታ ፕሮጀክቶች ሪቫን ተቆረጠ፤ የበርካታ ፕሮጀክቶችም የአፈጻጸም ከፍታ ተገለጠ፤ የበርካታ ፕሮጀክቶችም ሀገራዊ ብሎም ሕዝባዊ ፋይዳቸው እየተብራራ ሕዝቡ እንዲያውቃቸው፤ እንዲመካባቸውና እንዲጠብቃቸው የባለቤትነት ኃላፊነቱን የሚወስድበት ዕድል ተፈጠረ::
በዚህ በኩል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት፣ እንደ ሀገር ወደተሟላ ሉዓላዊነት የሚያሸጋግሩ፤ እንደ ሕዝብም የልማት፣ የሰላምና ደኅንነት ጥያቄዎቹን መልስ ያስገኙ ግዙፍ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ አሟልተው እና ተጠናቅቀው የተመረቁበት ነበር::
ከእነዚህ አንዱ የ“ሆሚቾ የተተኳሽ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ” ሲሆን፤ ይሄ ፋብሪካ፣ ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን መሣሪያዎች እንዲሁም ተተኳሾችን የሚያመርት ነው:: በዚህም ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ተተኳሽ ጥይቶችን ለማምረት የነበሩ ሙከራዎችን ያላቀ፤ በዘርፉ የነበረውን የውጪ ጥገኝነት (ከውጭ በማስገባት ላይ የተመሠረተውን የመሣሪያ እና ተተኳሽ ፍላጎት የማሟላት ሂደት) የቀየረ፤ ፍላጎትን በራስ አቅም ከመሸፈን አልፎም ወደውጭ የመላክ አቅም የፈጠረ ነው::
እንደ “ሆሚቾ የተተኳሽ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ” ሁሉ “የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ” ለኢትዮጵያ የተሟላ ክብርና ሉዓላዊነት ፀንቶ መዝለቅ ትልቅ አቅም የፈጠረ የማንሰራራቱ ዘመን ብሥራት ነው:: ይሄ ኢንዱስትሪ ታዲያ ለኢትዮጵያውያን ብሥራት፤ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ መርዶን ይዞ ነው ሪቫን የተቆረጠለት::
ኢንዱስትሪው፣ ከፍ ያለ ቴክኖሎጂን የሚጠቀምና ከዘመኑ ጋር የተዋደዱ ድሮኖችን ከማምረት ባለፈ፤ ድሮኖችን በራስ አቅምና ባለሙያዎች ዲዛይን አድርጎ የማምረት አዲስ ታሪክ የተመዘገበበት ነው:: እነዚህን መሰል ፕሮጀክቶች ደግሞ እንደ ሀገር ከፍ ያለ ግዝፈትን የሚያጎናጽፉ ሲሆን፤ ግጭት የሚፈልጉ ተዋንያንም ደጋግመው እንዲያስቡ በማድረግ ግጭትን ለማስቀረት እና ሰላምን ለማፅናት የሚደረገውን ጉዞ የሚያሳልጡ ናቸው::
ሌላኛውና ከእነዚህ ለየት ያለው ደግሞ፣ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት፣ አዲስ አበባንም የዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ እና ቱሪዝም መዳረሻነት፤ የአፍሪካ መዲናነት ገጿን ከፍ አድርጎ የሚገልጠው “የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል” ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ነው::
የዚህ ማዕከል ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ደግሞ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ ይሄንኑ አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “የአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የስብሰባ፣ የኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ዘርፍን (MICE) ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት አንድ ተጨማሪ አቅም ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደጠበቀ ተቋምነቱ የንግድ ቱሪዝምን በማሳደግና ዓለምአቀፍ ኹነቶችን በመሳብ ሀገራችንን የስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል” ሲሉም ነበር ከፍ ያለ ፋይዳውን ያስረዱት::
እነዚህን ለአብነት ለመጥቀስ ተሞከረ እንጂ፣ በማንሰራራት ዘመኑ ወራት እየተገለጡ ያሉ ሥራዎች ዘርፍም፣ መልክም ብዙ ናቸው:: በኢንዱስትሪውም፣ በግብርናውም፣ በምግብ ዋስትና የማረጋገጥ መስኩም፣ በጤናና ትምህርት ዘርፉ፣ በቤት ልማት እና በመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ በሰላም እና በዲፕሎማሲው ዓውዶች፣… የተገለጡ አቅሞች፤ የተከናወኑም ሥራዎች የበዙ ናቸው::
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የድንጋይ ከሰል ምርት ከማሻሻል ባሻገር ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የፈጠረው የኢቲ ማዕድን ልማት አ.ማ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ፤ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በስኬት መጠናቀቅ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የነበረው የሁለትዮሽና የባለ ብዙ መድረክ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች፤ የሰላም ጥሪዎች እና የሰላም ስምምነቶች፤… የእነዚህ ተግባራት ከብዙ አብነቶች ጥቂቶቹ ናቸው::
ከአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ከግብርና ስኬቶች፣ ከዲፕሎማሲያዊ ድሎችና ሌሎችም የማንሰራራት ዘመን ብሥራቶች ጋር አብሮ የሚነሳው ሌላኛው አብነት፣ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው:: እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ አንደኛ፣ ሰው ሰኮር ፕሮጀክቶች ናቸው:: በዚህ ረገድ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ፣ በሐረር፣ በጅማ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሃዋሳ፣ … ከተሞች የተከናወኑት እና እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፤ በአንድ በኩል የከተሞችን ገጽታ የቀየሩ፤ በሌላ በኩል፣ የነዋሪዎቻቸውን የሕይወት ዘይቤ ያሻሻሉ፤ አለፍ ሲልም የቱሪዝምና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅምን ከፍ ያደረጉ ናቸው::
ሁለተኛው የፕሮጀክቶቹ መገለጫ፣ የማድረግ አቅም መገለጫነት፤ በችግር ውስጥ ተሆኖም የመፈጸምን ልዕልና ገላጮች መሆናቸው ነው:: ለዚህ ደግሞ የሰላም ችግር ባለባቸው ክልሎች፣ በተለይም በአማራ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አብነቶች ናቸው:: በደሴ፣ በጎንደር፣ በኮምቦልቻ እንዲሁም ባሕር ዳርን በመሳሰሉ የክልሉ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች አብይ ማሳያዎች ናቸው::
ለምሳሌ፣ የባሕር ዳር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን እናንሳ:: ይሄ ፕሮጀክት እንደ ሀገር የከተሞችን ገጽታ የመቀየር፤ የሀገርን ሀብትና አቅም አውጥቶ የመግለጥ፤ የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ፤ የከተማ ነዋሪዎችን ምቹ የመኖሪያ ከባቢን የመፍጠር አንድ አካል ነው:: ይሁን እንጂ የባሕር ዳሩ ሥራ ከሌሎች ከተሞች አኳያ ሲታይ በፈተና ውስጥም ሆኖ ሕልምን የመፈጸም ቁርጠኝነትና ትጋት የታየበት፤ በዚህም በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ ሆነው ሥራውን ለሚያከናውኑ እና ውጤት እያሳዩ ላሉ ሌሎች ከተሞች ለላቀ ሥራ እንዲነሳሱ ምሳሌ የሚሆን ጭምር ነው::
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱን ከጎበኙ በኋላ “የባሕር ዳር ልምድ” በሚል ሃሳብ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ “ዛሬ የባሕርዳርን ከተማ የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ተመልክቻለሁ። ተፈጥሮ እና የሰው ጥበብ ተዋሕደው ባሕርዳርን ይበልጥ ውበቷን እያወጡት ነው። ከተማዋን የንግድና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ አመራሩ ከሚያደርገው ጥረት የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤” ሲሉ የገለጹትም ለዚሁ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ የባሕርዳሩ የኮሪደር ልማት ልዩ ባሕሪያት ያሏቸውን ስድስት ነጥቦች አስፍረዋል:: ከነዚህ ውስጥ አንደኛው፣ ባሕር ዳር በፈተና ውስጥ የመጽናት ምሳሌነት ነው:: ምክንያቱም፣ ከተማዋ ባለፉት ዓመታት የነበረውን ፈተና ምክንያት አድርጋ ሥራዋን አላቋረጠችም፤ ይልቁንም በፈተናው ውስጥ ሥራዋን ቀጥላ የኮሪደር ልማቱ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጋለች:: ፈተናው እያለፈ ከመሆኑ አኳያም በቀጣይ የተሻለ ነገር የም ታሳይ ይሆናል::
ሁለተኛው የባሕርዳር ኮሪደር ልማት መገለጫ፣ የኮሪደር ልማቱ የጣና መከፈት የማስተሳሰር(ኮኔክቲቪቲ) መርሕ መገለጫ መሆኑን ነው። ይሄንንም ሲያብራሩ፣ “ለብዙ ዘመናት ከከተማው ተለያይቶ የነበረው ጣና ወደ ስምንት በሚደርሱ ቦታዎች ከኮሪደሩ ጋር ተገናኝቷል። ይሄም ከመዝናኛነቱ ባሻገር ከተማዋን ነፋሻማ አድርጓታል፤” ብለዋል።
ሦስተኛው የባሕርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት መገለጫ፣ ነባር ዕሴት ላይ አዲስ ዕሴት የመጨመር ጉዳይ ነው:: አራተኛው ደግሞ፣ የአካባቢው ተቋማት ፈጠራ እየጨመሩ ልማትን እንዲያሳልጡ ማድረግ ሲሆን፤ በባሕርዳር ኮሪደር የለበሱት ንጣፎች እና የቆሙት መብራቶች በአካባቢው ተቋማትና ባለሙያዎች የተዘጋጁ መሆናቸው ነው::
አምስተኛው ነጥብም፣ ባሕርዳርን የስፖርትና የቅርስ ቱሪዝም መዳረሻ አቅምን ማሳደግ መቻሉ ሲሆን፤ ይሄም የ22ኛው ክፍለ ዘመን የንግድና ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ከሚያደርጓት አቅሞች አንዱ ነው:: ስድስተኛው ነጥብ ደግሞ፣ የአመራር አርአያነት ነው:: ምክንያቱም አመራሩ በክልሉ ያለውን ችግር እንደ ሥራ ማስተጓጎያ ምክንያት ሳይቆጥር ሠርቶ ማሠራት በመቻሉ የተገኘ አርአያነት ያለው ውጤት ነው::
በእነዚህ እና መሰል ጉዳዮች፣ ባሕርዳር ከዚህም በላይ መሥራት የምትችል መሆኗን ገልጣለች:: አዲስ አበባን፣ ሐረርን፣ ጅማን፣ አርባ ምንጭን፣… የመሳሰሉ ከተሞች ያሳዩትን ከፍ ያለ የኮሪደር ልማት አፈጻጸምም በፈተና ውስጥም ሆና መግለጥ ችላለች:: ከዚህ አኳያ ሲታይ፤ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እንደ ሀገር የተቀመጡ እቅድና አቅጣጫዎችን በመፈጸም ሂደት፤ አንድም ሥራዎች ሰው ተኮር መሆናቸውን፤ ሁለትም፣ ሥራዎች በፈተና ጫና ቸል የማይባሉ፣ ይልቁንም በታላቅ ትጋት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያስቻሉ ናቸው::
ይሁን እንጂ፣ ከዚህ በተቃራኒው ጥቂት በሞቅታ ተጀምረው በመሐል ደብዛቸው የጠፉ የኮሪደር ልማት ጅምሮች መኖራቸው እሙን ነው:: እነዚህም በሚገልጣቸው መልኩ መወቀስና መታረም ይኖርባቸዋል:: ለዚህ አንዱ ምሳሌ የሚሆነው የሸገር ከተማና አካባቢው የኮሪደር ልማት ሥራዎች ናቸው:: ምናልባት በእነዚህ አካላት እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ምክንያት ተብለው የሚቀርቡ “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” አይነት ጉዳዮች ይኖራሉ::
ምንም ይባል ምን ግን፣ በዚህ አካባቢ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ እንቅስቃሴ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ ነው ለማለት አያስደፍርም:: ለምሳሌ፣ መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ፣ ወደ ሰሜን አቅጣጫ እና በሌሎችም መስመር ለሚጓዝ መንገደኛ፤ በከተማዋ ውስጥ ባሉ ከተሞች የመንገድ ግራና ቀኝ እስከ ሃያ አምስት ሜትር የሚታየው ፍርስራሽ እንኳን በወጉ ተጠርጎ አካባቢው እንዲፀዳ አልተደረገም::
ይሄ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ ከተቀመጠለት ዓላማ አኳያ ተገቢነት የሌለው፤ በጀት የለኝም በሚልም ሆነ በሌላ ውሃ በማያነሳ ምክንያት የከተሞቹን ገጽታ በሚያጠለሽ እና ለነዋሪዎቻቸውም ምቾት በማይሰጥ ብሎም የደኅንነት ስጋትን በሚደቅን መልኩ ተዝረክርከው መቀመጣቸው ተገቢነት የለውም::
በተለይ መጪው ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሚፈጥሩት ተፅዕኖ አኳያ እየታየ በሸገር እና ሌሎችም አካባቢዎች ፈርሰው የቀሩ እና በጅምር ያሉ ሥራዎችን ማጠናቀቅና መስመር ማስያዝ የሚቻልባቸው አግባቦች ሊታሰብባቸው ያስፈልጋል:: ምክንያቱም፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታየው ሁኔታ ፈጽሞ ብልፅግና እንደ ፓርቲ ካስቀመጠው አቅጣጫም ሆነ፤ አሁን ላይ እንደ መንግሥት የተገባውን ቃል በተግባር በመግለጥ በኩል ባህል ሆኖ እየተገለጠ ያለውን እውነት የማይመጥኑ ናቸው::
በጥቅሉ ሲታይ፣ ብልፅግና ፓርቲ በሁለተኛው ጉባዔው ወቅት ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ከመፈጸምም ሆነ፤ በቀጣይ ይሆናል በሚል በፓርቲው ፕሬዚዳንት እና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት “ቀጣዩ ዘመን የማንሰራራት ነው፤ የማንሰራራት ዘመኑ ወራትም የብሥራት ናቸው፤” ሲል የገለጠውን እውነት እነሆ ቃልን በተግባር እየገለጠ፤ የማንሰራራቱን ዘመን አብነቶች ሪቫን እየቆረጠ ይገኛል::
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ታላቅ ሕዝብ ያለባት ታላቅ ሀገር ናት፤ ብዝኃነት የነገሰባት የብዝኃ ሀብታም ምድር ናት፤ ተፈጥሮ አድልቶ የሠራት የብልፅግና አብነት መገለጫ ለመሆን እየታተረች ያለች ሀገር ናት፤ ይሄን ሁሉ በልኩ ተገንዝቦም የሚተጋና የሚለፋላት ሕዝብ እና መሪም ባለቤት ናት::
ይሄ በመሆኑም ነው በለውጡ ዘመን መንገድ ተጉዞ ወደ ብልፅግናው ማማ ለመድረስ እየተደረገ ባለው ሂደት ውስጥ፤ መልካሙን ይዞና መጥፎውን አርሞ፣ የደበዘዘውን አቧራውን አራግፎና አስውቦ፣ ያረጀውን አድሶና አልቆ፣ ያልነበረውንም ከዘመኑ ጋር በማስማማት እንዲኖር አድርጎ፤ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ፣ ኢትዮጵያውያንንም ወደ ሀብት ማማ፤ በጥቅሉም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሉዓላዊነት እና የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ውጥናቸው እየተገለጠ ያለው:: ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም