
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማክሰኞ ዕለት ከአቻቸው ትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ሩሲያ የዩክሬንን የኃይል ማመንጫ እንደማትመታ አሳውቀዋል:: ፑቲን የኃይል ማመንጫውን ላለመምታት ከትራምፕ ጋር መስማማት ላይ ቢደርሱም በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ እንቅስቃሴ የተጀመረለትን የተኩስ አቁም ስምምነት ግን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል::
በቅርቡ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት በሳዑዲ ዓረቢያ የመከሩበት የአንድ ወር ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ፕሬዚዳንት ፑቲን ከትራምፕ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል:: ፑቲን እንዳሉት ይህ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊተገበር የሚችለው የውጪ ኃይሎች ለዩክሬን የሚያደርጉት የመሣሪያ እና የመረጃ አቅርቦት ሲቆም ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል:: የዩክሬን አጋር የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ከዚህ ቀደም ይሄን የፑቲንን ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበሉት አስታውቀው እንደነበርም አይዘነጋም::
በሳዑዲ መዲና ጅዳ በዩክሬን ጉዳይ የሚደረገው ንግግር እንደሚቀጥል በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዑክ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ተናግረዋል:: ሩሲያ ከስድስት ወራት በፊት በዩክሬን ቁጥጥር ስር ውሎ የነበረውን የኩርስክ ግዛት በቅርቡ ባካሄደችው ዘመቻ ማስለቀቅ መቻሏ አይዘነጋም::
ማክሰኞ እለት ትራምፕ እና ፑቲን ካደረጉት የስልክ ልውውጥ በኋላ አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ይዛው የነበረውን አቋም ማለዘቧ ሲሰማ በቀጣይ ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን ለመግታት ተጨማሪ ንግግሮች እንደሚያስፈልጉ መስማማታቸው ተሰምቷል:: ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እለት ጅዳ የተገኙት የአሜሪካው ልዑካን የዩክሬን ባለሥልጣናት በፍጥነት ተግባራዊ የሚደረግ ያሉትን የሠላሳ ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ ማሳመናቸው ይታወቃል::
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ለኦፊሻላዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ፊንላንድ መዲና ሄልሲንኪ ያቀኑ ሲሆን ዩክሬን የኃይል አማራጮችን ያካተተ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ተናግረው ሆኖም ግን ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚፈልጉ ተናግረዋል:: እንደዚሁም ከሰሞኑ በዩክሬን ላይ የበረታ የአየር ላይ ጥቃት እያደረሱ ያሉት የሩሲያ ወታደሮች ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነት ያለመፈለጉ ምልክት ነው ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል::
ከሰሞኑ ሩሲያ ባካሄደችው የድሮን ጥቃት ዒላማ ከተደረጉት መካከል ሱሚ የሚገኝ ሆስፒታል እና በስሎቭያንስክ የሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች ይገኙበታል:: ይሄን የሞስኮ ዒላማ በተመለከተ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ‹‹በሚያሳዝን ሁኔታ ዒላማ የተደረጉ ቦታዎች አሉ:: በተለይ ደግሞ ለሰላማዊ ዜጎች አገልግሎት የሚውሉ መሠረተ ልማቶች:: ዛሬ ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል›› ሲሉ ጽፈዋል::
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ከፑቲን ጋር ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ በጣም መልካም እና ውጤታማ እንደነበር ገልጸው ለጊዜው የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር ከስምምነት እንደተደረሰ፣ በቀጣይ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ውይይት እንደሚቀጥል ጽፈዋል::
ሰማኒያ በመቶ የሚሆኑት የዩክሬን የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶች በሩሲያ የቦምብ ጥቃት መውደማቸውን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ባሳለፍነው መስከረም መናገራቸው ይታወሳል:: ሩሲያና ዩክሬን የገቡበት ጦርነት በአሜሪካ አሸማጋይነት መቋጫ እንዲያገኝ እየተኬደበት ያለው ርቀት መልካም የሚባል ቢሆንም ብዙ የቤት ሥራዎች እንደሚቀሩትም ይነገራል::
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከገቡት ቃል አንዱ የሩሲያ እና የዩክሬንን ጦርነትን ማስቆም እንደሆነ ይታወቃል:: ኋይት ሐውስ በገቡ የመጀመሪያው ሰሞን ጀምሮ ሰላም ስለሚወርድበት የሁለትዮሽ ምክክር እየሠሩ ይገኛል:: የማክሰኞው ከፑቲን ጋር የተደረገው የስልክ ልውውጥም የዚህ አንዱ አካል ሲሆን በቀጣይ ጦርነቱ በሰላም ተቋጭቶ ሁለቱ ሀገራት ወደነበሩበት ሰላም ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል:: መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል::
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም