ባቡር ዘመኑ ከፈጠራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዱ ነው። ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂው እየዘመነ በምቾትና በፍጥነት አየር ላይ እየቀዘፈ ብዙ ሺህ ማይሎችን አቋርጦ ከሚያልፈውና የዘመኑ የመጨረሻ ፈጣን የመጓጓዣ ቴክኖሎጂ ውጤት ከሆነው አውሮፕላን ቀጥሎ ባቡር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሀገራችን የባቡር አገልግሎት ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ቢሆንም የእድሜውን ያህል የዘመነ የትራንስፖርት አቅርቦቱና ተደራሽነቱ እምብዛም ነው።
አሁን ያለው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትም ሀገሪቱ ካላት የቆዳ ስፋትና የትራንስፖርት ፍላጎት ማደግ ጋር ተያይዞ ገና ጅምር ላይ ያለ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል። በባቡር ትራንስፖርት የዘመነ አገልግሎትና ምቹ መደላደል የፈጠሩ ሀገራት በባቡር ቴክኖሎጂ ርቀው ለሌላ መትረፍ ችለዋል። ሀገሪኛ ቴክኖሎጂያቸውን ከውጪና ይበልጥ ከዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር አዛምደው ያላቸውን አቅም በሙሉ ዛሬ ላይ ለደረሱበት ውጤት ግኝት ላይ አብቅቷቸዋል።
በሀገር ደረጃ ጅምር በሆነው የባቡር ቴክኖሎጂ ላይ የሚደረጉ ሀገራዊ ምርምሮች ለባቡር ትራንፖርት የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ሀገራዊ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ስራዎች መበራከት ይህንን ተከትሎ የሚመዘገቡ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚና የሰው ሃይል ልማት ውጤቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ዛሬ ከባቡር ቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ ምርምር ያደረጉ፤ በምርምራቸውም አመርቂ ውጤት አስመዝግበው ሀገር አቀፍ እውቅናና ሽልማት ያገኙ ተመራማሪና የምርምር ስራቸውን ምንነት እናቀርብላችኋለን።
ተመራማሪና መምህር ዘውዴ ሞገስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሲቪል ምህንድስና፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ተከታትለው በስኬት አጠናቅቀዋል። የሁለተኛ ዲግሪያቸው ያጠኑበት የባቡር ቴክኖሎጂ መሰረት ያደረገው ትምህርት ለምርምር ስራቸውና በመጨረሻም ስኬታማ ሆኖ ለተጠናቀቀው ግኝታቸው መሰረት ሆኗቸዋል።
የምርምር ስራ ለሀገር ማበርከት ከሚፈልጉት በጎ ስሜት የሚመነጭ መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው በባቡር ሀዲድ ስራ አገልግሎት ላይ የሚውል “ሪስለንት ፓድ” የተሰኘ መሳሪያ አሁን ካለውና ከውጪ ከሚገባው በተሻለ ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሳያ አሮጌ ጎማዎችን በመጠቀም በምርምር መስራት ችለዋል።
የመምህር ዘውዴ የምርምር ስራ ውጤታማነት በተለያዩ ተቋማት ማረጋገጫ የተሰጠው ሲሆን ከውጪ ሀገር በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ሀገር እየገቡ አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩት መሰል አገልግሎት ከሚሰጡት በተሻለ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ መቀየር የሚያስችልና ሀገራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ከውጪ የሚገባው መሳያን እዚህ ማምረት፤
ከዚህ በተጨማሪም አሁን ላይ በባቡር ሀዲድና በባቡሩ መሄጃ ጎማና በሀዲዱ ፍትጊያ የሚከሰት ንዝረት ድምፅ ወይም መዋቅር ወላድ ድምፅና ንዝረት የሚፈጥረው ከፍተኛ ድምፅ አካባቢን የሚበክል ነው። ነገር ግን የተመራማሪው ግኝት ይህን የሚያስቀርና መፍትሄ ይዞ የመጣ ነው። በመሆኑም በፍትጊያው ምክንያት የሚከሰተውን የሀዲዱ እድሜ መቀነስም የሚከላከልና ረጅም እድሜ ማገልግል እንዲችል የሚያደርግ ነው።
አገልግሎት የሰጡ ጎማዎችና የላስቲክ ውጤቶችን በመጠቀም በምርምር አገልግሎት እንዲሰጥ የፈጠሩት ተመራማሪው ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥ ተመሳሳይ ስራ የተሰራ አለመኖሩንና የሳቸው የምርምር ውጤት አዲስ ስለመሆኑ አረጋግጦ የፈጠራ ስራ ባለቤትነት መብት ከኢትዮጵያ አዕምሮዓዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
መሳያውን ለማምረትና ለአገልግሎት እንዲውል ለማድረግ የመስሪያ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩና እዚሁ ተመርቶ በስፋት ማቅረብ ቢቻል የውጪ ምንዛሬ በማስቀረት አሁን ካለው ረጅም ጊዜ ማገልገል የሚችል ሀገራዊ ምርት በማቅረብ ለሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ መፍጠር ይቻላል ይላሉ።
ለሀገር ትልቁ ሀብት የሰው ልጅ አዕምሮ መሆኑን የሚናገሩት መምህርና ተመራማሪው፤ ለምርምር ስራዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የፈጠራ ስራዎችን ማበረታትና ተግባር ላይ የሚውሉበትን መንገድ ማማቻቸት ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳል። የፈጠራና የምርምር ስራዎች ተግባራዊ ሆነው የሀገርን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መቅረፍ ካልቻሉ መገኘታቸው ብቻ ጥቅም የሌለውና ትርፉ ድካም ብቻ ነው የሚሉት ተማራማሪዎች ለዚህ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የምርምር ስራዎች በተመራማሪዎች ተሰርተው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚመለከታቸው አካላት፤ በተለይም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ተቋማት ትኩረት ሰጥቶ መስራትና የፈጠራ ስራዎቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የግኝት ውጤታቸው ተግባራዊ የሚያደርጉበት የገንዘብ ድጋፍ መነሻ የሚሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል። እንደ ተመራማሪው ገለፃ፤
በምርምር ስራቸው የ2011 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ሽልማት ያገኙ ሲሆን ከኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት የተበረከተላቸው የፈጠራ ስራው የባለቤትነት መብት በተጨማሪ በተለያዩ ኮንፍረንሶች ላይ የጥናት ስራቸውን ምንነት የሚያመለክት ፅሁፍ በማቅረብ እውቅና አግኝተዋል።
በምርምር ስራቸው ወቅት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድርጅት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገላቸው የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ወደ ምርት ሂደት ለመግባትና ከምድር ባቡር ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት በምድር ባቡር በኩል የአሰራር ህጉ የማያመችና ለዚህ የሚሆን በጀት ሊመድብ የሚያስችለው አለመሆኑ እስካሁን ወደ ምርት መግባት አለመቻሉን ይናራሉ።
ሳይንሳዊ ምርምርና የፈጠራ ስራ የሰው ልጅ የሚገጥመውን አካባቢያዊና ማህበራዊ ችግር መፍቻ መንገድ መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ለዚህ ዘርፍ ትኩረት መስጠት ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ያስችላል ይላሉ። ሀገራዊ የምርምርና የፈጠራ ስራ ማበረታታት ደግሞ ለዚህ ቁልፍ ተግባር ዋነኛ መነሻ ነው።
ምርምር ማድረግ የማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መቅረፊያ መንገድ መሆኑና ለዚህም ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እንደሚገባም አፅንዖት በመስጠት ይናገራሉ። በተጨማሪም የምርምር ውጤት አካባቢያዊ ችግር የሚቀርፍ፤ በደንብ ከተሰራበት ደግሞ የውጪ ምንዛሬ በመቀነስ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችል የፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ምርምሩን በሚያደርጉበት ጊዜ የሚጠቅሱት የጎላ ችግር ባይገጥማቸውም የምርምር ውጤቱን ግን ተግባራዊ ለማድረግና ወደ ምርት ለመሸጋገር የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ አለማግኘታቸው ለምርምር ስራቸው ውጤታማነት እንቅፋት ሆኗል። ለዚህ ሀገራዊ ፋይዳው የበዛ የምርምር ውጤት ተግባራዊነት የሚመለከተው አካል ድጋፍ ቢያደርግና ወደ ምርት ስራው ቢገባ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተመራማሪው ይገልፃሉ።
ተመራማሪና መምህር ዘውዴ ሞገስ አሁን እያደረጉት ካለው የምርምር ስራ በተጨማሪ ለወደፊት በባቡር ቴክኖሎጂ ላይ ምርምሮችን ለማድረግና በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማምጣት በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከውጪ እየገቡ ለዘርፉ ግልጋሎት የሚውሉ መሳሪያዎችን እዚሁ አምርቶ መጠቀም የሚያስችል ምርምርና ጥናት በማድረግም የራሳቸውን አስተዋፅዖ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ለምርምር አዲስ በሆነ ማህበረሰብና ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ለሚካሄደው ስራ ለሚሰማሩ አዲስ ተመራማሪና የፈጠራ ባለሙያዎች ጠንካራና ብርቱ መሆን እዳለባቸው የሚመክሩት ተመራማሪና መምህር ዘውዴ ከምርምር ተሞክሯቸው ያገኙትን ልምድ በሚከተለው መልኩ ለተመራማሪዎቹ ያስተላልፋሉ። የዘርፉ ጀማሪ ባለሙያዎች ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋትና መልካም ውጤት በመመኘት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
በተጨማሪም፤ የምርምር ስራዎች በተፈለገው መልክ ተግባር ላይ ውለው ጥቅም እንዲሰጡ ለምርምር ስራዎቹ እውቅና ከመስጠት ባለፈ የምርምርን ስራ ምቹ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በመንግስት በኩል ሊመቻቹ እንደሚገባና አሁን በሳይንስ ዘርፍ እምርታ ለማስመዝገብ ተመራማሪዎች ያገኙትን ውጤት ወደ ስራ እንዲገባ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ለዚህም የመንግስትን እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የጋራ ስራና ጥረት እንደሚጠይቅና ለስራው መሳካት መጣር ተገቢ መሆኑን ያስረዳሉ።
የርሳቸውን የምርምር ውጤት ተግባራዊ ለማድረግ ያልተቻለበት ዋነኛ ምክንያት የገንዘብ እጥረት መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም ያለው ችግር መፈታት ይገባዋል ባይ ናቸው። የምርምርን ስራ ተግባራዊ ማድረገንና ማህበራዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ የገጠማቸውን ችግር በማሳያነት በማንሳት ተመራማሪዎች በሞራልና በተሻለ መንፈስ ስራቸው መስራት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተመራማሪው ይገልፃሉ።
እኛም የምርምር ስራ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለው ሚና ከፍተኛ ነውና ለተመራማሪዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለስራው ውጤታማነት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፤ መልዕክታችን ነው። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2011
ተገኝ ብሩ