የመስተንግዶ ሠራተኞች አለባበስ- ኢትዮጵያዊ ባሕሎች ላይ አደጋ የጋረጡ ድርጊቶች

ኢትዮጵያ የበርካታ ባሕሎች መገኛ ነች። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በደስታ፣ በሀዘን እና በእለት ተእለት የኑሮ አጋጣሚያቸው ሁሉ የሚከተሏቸው ልምዶች፣ ባህሎችና የሥነ ምግባር ሕግጋቶችም ሀገር በቀልና ለዘመናት ሳይበረዙ ሳይከለሱ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ የቻሉ ናቸው። ማህበረሰቡ እንደየማንነቱና እንደሚከተለው ሃይማኖት ልዩ ልዩ ባህሎች ያሉት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን እነዚህን ልዩነቶች አጣምሮ መያዝ የሚያስችል የጋራ እሴቶች ባለቤት ናት። ከእነዚህ ሀገር በቀል እሴቶች መካከል እንግዳ ተቀባይነት፣ ደርዝ ያለው አለባበስ፣ በአደባባይ ላይ የሚታይ ቁጥብነትና (ጨዋነት) ደርባባ ማንነት መላበስ ቀዳሚና ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ እሴቶች ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ የሚያስመሰግኑ፣ የማህበረሰቡን የተገራ ባህሪ የሚያመላክቱና ለሀገር መልካም ገፅታ የሚያላብሱ ሆነው ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ እየተሻገሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲተገበሩ አይስተዋልም።

በዛሬው የሀገርኛ ዓምድ ላይ በስፋት ልንዳስሰው ከወደድነው ‹‹የመስተንግዶና የአለባበስ ሥነ ምግባር›› ጋር በተገናኘ በሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛ ስፍራዎች እየታዩ ያሉ ከኢትዮጵያዊ ባህልና ሥነ ሥርዓት ወጣ ያሉ አለባበሶችና የመስተንግዶ ልምዶች ከላይ ካነሳናቸው የማህበረሰቡ ማንነቶች ተቃራኒ እየሆኑ መምጣታቸውን መመልከት ይቻላል።

በተለይ ይህ አለባበስ በፍፁም ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት የምትታወቀውን የኢትዮጵያን መልካም ስም ለማጉደፍ ስሱ ጎን ባለው የሆስፒታሊቲ (የአገልግሎትና መስተንግዶ) ዘርፍ ላይ እየተስተዋለ መጥቷል። የማህበረሰቡን ባህልና ልምድ በቀላሉ ለመበረዝ እና ያልተገባ ትርጉም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሰጠት ዘርፉ የበለጠ ተጋላጭ ነው። ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች፣ በስብሰባና በልዩ ልዩ አጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች ከመስተንግዶ ባለሙያዎች ጋር በቀላሉ የመገናኘት እድል አላቸው። ይህ ደግሞ ለአጭር ጊዜ ቆይቶ ወደ ሀገሩ የሚመለስ ጎብኚ ስለኢትዮጵያ ባህል፣ አለባበስ፣ ሥነ ምግባርና መሰል እሴቶች የተዛባ ግንዛቤ ይዞ እንዲመለስና ተገቢ ባልሆነ መንገድ ልምዱን ለሌሎች እንዲያጋራ ጫና ይፈጥራል።

ከላይ ያነሳነውን የመስተንገዶ ሥነ ምግባር ክፍተት ተከትሎ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እንዳይጎዳ ዘርፉን የሚመሩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት እየሠሩ መሆኑን መረጃዎች እያሳዩ ነው። ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞም ቀዳሚውን ርምጃ ለመውሰድ ጥረት እያደረጉ ከሚገኙት መካከል የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ይጠቀሳል። ቢሮው በሆቴሎች የሚሠሩ ሴት የመስተንግዶ ባለሙያዎች ከሀገሪቱ ባህል ውጭ የሆነውን አለባበሳቸውን ለማስተካከል የሚያስችል የአለባበስ ኮድ መመሪያ ዝግጅት ከሰሞኑ ተጠናቋል፡፡

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶክተር) በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በመመሪያው መሠረት በአንዳንድ ሆቴሎች የሴት መስተንግዶ ሠራተኞች አለባበስ ከሀገሪቱ ባህል ወጣ ያለ ሆኖ ተገኝቷል። ይህን ለማስተካከል የሚረዳ የመስተንግዶ ባለሙያዎች የአለባበስ ኮድ መመሪያ ዝግጅቱ ተጠናቆ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲፀድቅ በመላኩ መመሪያው በከተማዋ ካቢኔ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ ይደረጋል።

‹‹ለቱሪስቶች መስተንግዶ ሲሰጥ የሀገራችንን ባህልና እሴት በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት›› የሚሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ በሆቴሎች ያለው የመስተንግዶ ባለሙያዎች አለባበስ ሥነ ሥርዓቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ይገልፃሉ። አሁን ላይ የመስተንግዶ ባለሙያዎች በተለይም ሴቶች በአንዳንድ ሆቴሎች አማካኝነት ሥነ ሥርዓቱን ያልጠበቀ አለባበስ እንዲለብሱ እንደሚገደዱ ጠቅሰው፣ ድርጊቱ ከሴት ልጅ መብት አኳያ ክብርን ያልጠበቀ እና አሳፋሪ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ መመሪያው ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል በሆቴሎች የሚሰሩ የመስተንግዶ ባለሙያዎች ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአለባበስ ኮድ እንዲከተሉ ይደረጋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ባህልና ወግ ያልጠበቀ የአለባበስ ሥነ ሥርዓትን ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ አሁን ላይ በአንዳንድ ሆቴሎች የሚታየውን ከባህል ያፈነገጠ የመስተንግዶ ባለሙያዎች አለባበስ መስተካከል እንዳለበት የከተማው ነዋሪዎች ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው። መመሪያው ሲፀድቅም የሁሉም ጥያቄ ይመለሳል።

‹‹ሕጉ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣትም ጭምር ያለው በመሆኑ መመሪያውን በሚተላለፉ ላይ ቅጣት ይጣላል›› ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ የአለባበስ መመሪያውን ለማውጣት ቢሮው ሁለት ዓመት ሲሰራ መቆየቱን ይናገራሉ። ሕጉ ከፀደቀ በኋላ ወደ ርምጃ እንደሚገባም አንስተዋል። ሕጉ እስኪፀድቅ የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፣ በሚደረገው ክትትልና ድጋፍም አሁን ላይ ለውጦች መኖራቸውን ተናግረዋል።

አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። ከመስተንግዶ የአለባበስ ሥነ ምግባር ጋር በተገናኘ እየታዩ ያሉ ክፍተቶችን በተመለከተ ለዝግጅት ክፍላችን ሙያዊ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።

‹‹በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ ከደንብ ልብስ ጋር ተያይዞ የሚገድብ ምንም ዓይነት ሕግ ባለመኖሩ በኢትዮጵያ ባህል ላይ ተፅእኖ እየተፈጠረ ነው›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ ባህልን ከማጥፋት ባሻገር በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ያለ ፍላጎታቸው ተገቢ ያልሆኑ አልባሳት እንዲጠቀሙ እንደሚገደዱ ይናገራሉ። ችግሩ በዚህ ሳያበቃ አገልግሎት ፈልጎ በቦታው የሚገኝ ደንበኛ ምቾትን ይነሳል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በሆቴሎች፣ መዝናኛ ስፍራዎች የሚታዩትን ከኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ድርጊቶች የሚቃወሙ ተደጋጋሚ ወቀሳዎች እንደሚቀርቡ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እነዚህን ወቀሳዎች ተቀብሎ መፍትሔ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን እንደሚያውቁ የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፤ እርሳቸው የሚመሩት የባለሙያዎች ማህበርን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻዎች የተሳተፉበት ረቂቅ ሕግ ፀድቆ በቅርቡ እንደሚወጣ ያስረዳሉ።

እንደ አቶ አሸናፊ ማብራሪያ፤ የከተማዋ ሥጋ ቤቶች እና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች በተለይ ሴት ሠራተኞቻቸውን ብርድና ዝናብ ባለበት ሰዓት ጭምር ከባህል፣ ከኢትዮጵያዊ ሥነ ሥርዓት ያፈነገጠ አለባበስ እንዲከተሉ ያስገድዳሉ። ይህ ተገቢ ባለመሆኑ በሕግ ለመገደብ ቢሮው ሕጉን አፅድቆ ለመሥራት በሂደት ላይ መሆኑ ተገቢ ነው። እርሳቸው የሚመሩት ማህበርም ለዚህ ግብዓት የሚሆኑ ሙያዊ አስተያየቶችን መስጠቱንና ለተፈፃሚነቱም በትብብር ለመሥራት መዘጋጀቱን ያስረዳሉ።

‹‹በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ምግብ ቤቶችና መሰል አገልግሎት ሰጪ መዝናኛ ስፍራዎች በሠራተኞቻቸው አለባበስ ገበያ ለመሳብ በሚል ድርጊቱን ይፈፅማሉ›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ ይህንን ተገቢ ያልሆነ ተግባር ማስተካከል እንደሚገባ ይመክራሉ። የመስተንግዶ ሙያ ለአገልግሎት ሰጪውም ሆነ ለተጠቃሚው ምቾት በማይነሳ መልኩ መሆን እንደሚጠበቅበት በመግለፅም ተፈፃሚ የሚሆነው ሕግ ያንን መሠረት ያደረገ መሆኑን ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች፣ ሥጋ ቤቶችና አንዳንድ መዝናኛ ስፍራዎች ከአለባበስ አንፃር እየታዩ የመጡ ተግባሮች በጊዜ ገደብ የማይበጅላቸው ከሆነ መዘዛቸው የከፋ መሆኑን የሚናገሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ድርጊቱ በዓለማችን ላይ የማይሆን ስም እንደተሰጣቸው ሀገራት ተገቢ ያልሆነ አመለካከት ለኢትዮጵያም እንዲሰጣት እንደሚያደርግ ይገልፃሉ። በመሆኑም ሕጉን በፍጥነት አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ። ኮኮብ ባላቸው ሆቴሎች ላይም ሕጉ እንዲተገበርና የአለባበስ ሥርዓቱ ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድም ባሻገር ሀገራዊ፣ ባሕላዊና ኢትዮጵያዊ እሴቶችንም ያካተተ እንዲሆን ቢደረግ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል የሚል ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።

‹‹ከተቻለ መስተንግዶ ላይ ሠራተኞች የሚጠቀሟቸው አለባበሶች ሀገርኛ ቢሆኑ መልካም ነው›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ባህሎች መኖራቸውን ይገልፃሉ። ይህ ሂደት የእለት ተእለት ሥራን በማያስተጓጉል መልኩ የኢትዮጵያን ባህላዊ የአለባበስ እሴቶች ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ጎብኚዎች ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ይናገራሉ። የሀገር ውስጥ ጎብኚ የማያውቃቸውን የሌሎች ባህሎች አለባበስ እንዲያውቅ፤ የውጭ ጎብኚውም የኢትዮጵያን እሴቶች ወደ ሀገሩ ሲመለስ አውቆ እንዲሄድና ለሌሎች እንዲያስተዋውቅ እንዲረዳው ለማድረግ እንደሚያስችል ይናገራሉ።

አቶ አሸናፊ በቅርቡ ሥራ ላይ የሚውለውን ሕግ ወደ መሬት ለማውረድ ስልት ተነድፎ ሊሰራ ይገባል ይላሉ። አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጎች ቢወጡም ማስፈፀሙ ላይ ግን ክፍተቶች አሉ ሲሉ ያስገነዝባሉ። በዚህኛው ጉዳይ ላይም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚኖርበት ያሳስባሉ። ሕጉ ተግባር ላይ ከዋለ በኋላም ክትትል በማድረግ ተፈፃሚ እየሆነ ያለበትን ደረጃ መገምገም የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር በቅርቡ ለሚወጣው ሕግ ተፈጻሚነት ሙያዊ ትብብር እንደሚያደርግ አቶ አሸናፊ ይናገራሉ። ለተፈፃሚነቱ የሚረዱ ስልጠናዎችን፣ ምክረ ሃሳቦችን፣ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማሰናዳት በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ የሚወጣው የመስተንግዶ አለባበስ ሕግና ደንብ እንዲሰርፅ እንደ አንድ ባለድርሻ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንደ መውጫ

አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማነቷ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቢሮዎች፣ ዲፕሎማቶች መቀመጫ ነች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለቱሪዝም በተለይ ደግሞ ለማይስ ቱሪዝም (ኢንዱስትሪ) ምቹ መናኸሪያ እንደሚያደርጋት በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ያመለከታሉ። የማይስ ዘርፍ የጉባኤ፣ የአውደ ርዕይና ባዛር፣ የንግድ ውይይትና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ዋና ማጠንጠኛው መሆኑን በመጥቀስም፣ ሀገሪቱ ምጣኔ ሀብቷን እንድታሳድግ፣ ተመራጭ የስብሰባ ቱሪዝም ከተማ እንድትሆንና ያንን ተከትሎ ዜጎች በሚፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ እድል ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆኑ እሴቶችን ለማስተዋወቅና የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለመገንባትም ትልቅ አጋጣሚ ይፈጥራል።

ሆኖም ከዚህ እድል ተጠቃሚ ለመሆንና ኢትዮጵያንና መዲናችንን አዲስ አበባን የማይስ መዳረሻ ለማድረግ ሥራዎች ሲሰሩ ጎን ለጎን ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መዘንጋት የለባቸውም። ከእነዚህ መካከል ዛሬ በስፋት የዳሰስነው የመስተንግዶና የአለባበስ ሥነ ምግባር ነው። ኢትዮጵያን የማይስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መንግሥት በጀት መድቦ፣ ከፍተኛ ጨረታዎችን አሸንፎ፣ የገበያና የማስታወቂያ ሥራዎችን ሰርቶ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጡ በመስተንግዶ ረገድ ጥንቃቄ የማይደረግ ከሆነ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚያበላሹ አጋጣሚዎች መፈጠራቸው አይቀርም።

አንድ ጎብኚ ወይም እንግዳ በከተማዋ በሚኖረው ቆይታ በምግብ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች እና መዝናኛ ስፍራዎች መገኘቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ጊዜ ከእኛ እሴቶች ያፈነገጡ ተግባራትን ተመልክቶ አሉታዊ እሳቤ ይዞ ወደ ሀገሩ ሊመለስ ይችላል። ይህ እጅግ አደገኛና ለገፅታ ግንባታ እንቅፋት ነው። በመሆኑም የመስተንግዶ ባለሙያዎች አለባበስ ቢቻል ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው ካልተቻለ ደግሞ ጨዋነትና ሥነ ሥርዓትን የተላበሰ እንዲሆን ተደርጎ መሠራት አለበት። ይህ የሥነ ምግባር ጥሰት በሕጎች በጊዜ ካልተገታም እያደገ መጥቶ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ገፅታና ምስል እንዳያጠፋ በቅርቡ ሊተገበር የታሰበው ሕግ በፍጥነት መሬት ላይ እንዲወርድ መሠራት አለበት።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You