ከከበሩ ማዕድናት የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችለው ስትራቴጂ

በዓለም ላይ በርካታ ዓይነት የከበሩ ማዕድናት አሉ፡፡ ማዕድናቱ በተፈጥሮ ለሰው ልጆች የተሰጡ ገጸ በረከቶች እንደመሆናቸው ከጥንት ጀምሮ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ በተለይ እንደ ኦፓል፣ ሳፋየር፣ ሩቢ እና ኤመራልድ ያሉት የከበሩ ማዕድናት በጣም ተወዳጅ ከሆኑ የከበሩ ማዕድናት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ማዕድናቱ በተለያዩ የጌጣጌጥ ዓይነቶች በሚፈለገው ቅርጽና ዲዛይን ተሰርተው ለአንገት፣ ለጆሮ፣ ለጣት፣ ለእግርና ለሌሎችም ጌጣጌጥነት እንዲውሉ ይደረጋሉ፡፡ ጌጣጌጦቹም በስጦታ መልኩ የሚበረከቱ ውድ ቁሶች እንደመሆናቸው በሰዎች ዘንድ ልዩ ዋጋና ትርጉም ተሰጥቷቸዋል፡፡ የጌጣጌጥ ማዕድናቱ በውበታቸው ቀልብን የሚስቡ፣ ውስጣዊ ደስታን የሚፈጥሩ እንዲሁም ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅባቸው መሆናቸው ተፈላጊነታቸውና ተወዳጅነታቸው ይበልጥ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ የሩቅ ምስራቅ ሀገሮቹ ህንድ፣ ሲሪላንካና ቻይና በእነዚህ ማዕድናት ሀብቶቻቸው፣ ኢንዱስትሪዎቻቸውና ገበያዎቻቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያም በዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆኑት የእነዚህ የከበሩ ማዕድናት መገኛ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ፣ አጌት፣ ኳርትዝ እና ሌሎችም ለጌጣጌጥነት የሚሆኑ ማዕድናት መኖራቸውን እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ ማዕድናት መገኛ ሀገር ትሆን እንጂ ማዕድናቱን አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋልና የውጭ ገበያን በመሳብ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት እምብዛም ጥረት ሲደረግባትና ሲሰራባት ግን አትስተዋልም፡፡ እስካሁን ባለው ልምድ በሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናት ቢመረቱም፣ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬው ለውጭ ገበያ እንደሚላኩ ነው የሚታወቀው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መሻሻሎች እየታዩ ማዕድናቱ በጌጣጌጥ መልኩ ተመርተው እሴት እየተጨመረባቸው ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ። አሁንም ቢሆን ግን እሴት ተጨምሮባቸው ከሚላኩት ማዕድናት ይልቅ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬው የሚላኩት ይበልጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ተጠቅማ ከማዕድናቱ ማግኘት የሚገባት የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ እንቅፋት ሆኖባት መቆየቱን መረጃዎች ያስገነዝባሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ይህን ችግር ለመፍታት እየተሠራ ይገኛል፡፡ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ዘርፉ በስትራቴጂ እንዲመራ የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብስራት ከበደ (ዶክተር) ስትራቴጂው በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡ ዘርፉን በስትራቴጂ ለመምራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቷ እስካሁን ከማዕድናቱ እያገኘች ያለችው ገቢ በጣም አነስተኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩም ጠቅሰው፤ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ንቃት መፍጠር ከተቻለ ቢዝነሱ በራሱ ቴክኖሎጂዎችን እየገዛ መሥራት የሚቻልበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ዘለቀ በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የማርብል፣ ግራናይትና ጌጣጌጥ ማዕድናት ዴስክ ኃላፊ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ከ40 በላይ የከበሩ ማዕድናት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እጅግ በጣም የከበሩ በመባል የሚታወቁት የኮረንድም ፣ የቤሪል ፋሚሊን እንዲሁም ሳፋየር እና ኤመራልድ ጨምሮ በርካታ የከበሩ ማዕድናት ይገኙባታል፡፡

በሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናት በማምረት የሚታወቀው የወሎ አካባቢ ሲሆን፤ በዚህ አካባቢ ኦፓል ላይ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሀገሪቱ የሚገኙት እነዚህ ማዕድናት በተለያየ መልኩ ለዓለም ገበያ እየቀረቡ ቢሆንም፣ እንደ ሀገር ሲታይ እያስገኙት ያለው ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

በሀገሪቱ ዘርፉ ረጅም ጊዜ የቆየ አይደለም፤ በደንብ እየታወቀ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ማዕድን በዓለም ሀገራት ኢኮኖሚውን በሰፊው የሚያንቀሳቅስ እንደሆነም ያመላክታሉ፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት ፤ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያመላክተው በከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጥ ዘርፍ በዓመት ከ250 እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር ይንቀሳቀሳል፡፡ በኢትዮጵያም እንደ ሀገር ሰፊ የከበሩ ማዕድናት ሀብት ስላለ ዘርፉን በስትራቴጂ መምራት ከተቻለ ከዚህ ዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያም ድርሻ ሊኖራት ይችላል፡፡

ከዘርፉ የሚጠበቀውን ተጠቃሚ ላልተቻለበት ምክንያት ከሆኑት መካከል የመጀመሪያው ዘርፉ በስትራቴጂ ሳይመራ መቆየቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ማዕድናቱ ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይ እምብዛም አለመሠራቱ ነው፡፡

ይህ ዘርፍ ወደፊት እንዲወጣ ለማድረግ እሴት መጨመር ላይ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዘርፍ የታወቁት የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ናቸው፡፡ እነርሱ ዘንድ ያለውን ሀብት በብዛት ተጠቅመውበት እያለቀባቸው ናቸው፡፡ አሁን ሀብቱ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ናቸው፡፡ የዓለም ሀገራት ዓይናቸውን ወደ አፍሪካ አዙረዋል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት የማዕድን ሀብቱን በስፋት እያጋዙ እሴት በመጨመር ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ በማዕድን ሀብቱ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ሳይገጥመን ቀድመን መሥራት አለብን ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ለእዚህም ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ መሥራት እንዳለባት ይጠቁማሉ። ‹‹ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ የማዕድን ሀብት አላት፤ ጠንከረን ከሠራን ኢትዮጵያን ወደፊት የማዕድናቱ የግብይትና የእሴት መጨመሪያ /ፕሮሰሲንግ /ማዕከል እንድትሆን ማድረግ እንችላለን›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ለከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በመላክ እስከ እአአ 2029 ባሉት ዓመታት ውስጥ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙ የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች ይኖራሉ፡፡ የዓለም የመገበያያ ማዕከል የመሆን ከፍተኛ እድልም ሊፈጠር ይችላል፡፡

ስትራቴጂው በከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ በርካታ ሥራዎች መሥራትን እንደሚጠይቅ አመልክተው፣ ይህ ሥራም አልጋ በአልጋ ሆኖ የሚሠራ እንዳልሆነና በዙሪያው ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ በዘርፉ እሴት ሰንሰለት ከማዕድን ማውጣት ጀምሮ እስከ ግብይት ድረስ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ ማዕድን ማውጣት ላይ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ የበቃ ሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ማዕድኑ እየወጣ ያለው በዘፈቀደ (በባህላዊ አሠራር) በመሆኑ ይህን አሠራር ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ይህም በተወሰነ መልኩ ዘመናዊ በማድረግ የተሻለ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙና የተሻለ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ መሥራት ይገባል፡፡ ማዕድኑ ከወጣ በኋላም እንዲሁ እሴት የመጨመሩ (ፕሮሰስ የሚያደርጉ) ሂደት ብቃት ያለው የሰው ኃይል አስልጥኖ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡

አሁን በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ከህንድ፣ ሲሪላንካና ቻይና-ከመሳሳሉት ሀገራት ጋር የምንወዳደር እንደመሆኑ ልማቱ በእነሱ ደረጃ የበቃ የሰው ኃይል ማዘጋጀትን ይጠይቀናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ዘርፉን ወደፊት ለማውጣት ከዚህ በፊት በክልሎች ኮሌጆች በመክፈት የሰው ኃይል የማሰልጠን ሥራን የመሳሰሉ የተሞከሩ ጥሩ ጅማሮዎች እንዳሉም ጠቅሰው፤ ይህ ግን በቂ እንዳልሆነ አመልከተዋል፡፡ የተጀመሩትን ሥራዎች በደንብ አጠናክሮ በማስቀጠል በዘርፉ ከዓለም ሀገራት ጋር ለመወዳደር የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የጌጣጌጥ ማዕድናቱን ለማምረት የሰው ኃይል መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ተመራጭ የምርምር፣ የሰርተፌኬሽን ማዕከላት እና የመሳሰሉትን መገንባትንም ይጠይቃል።

‹‹ስትራቴጂው ለችግሮቹ መፍትሔ እንደሚሆን ታምኖበታል፤ በእነዚህ ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርገን በደንብ የምንሠራ ከሆነ የታቀደውን እናሳካለን›› ሲሉም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ስትራቴጂው በከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ ለታዩ በርካታ ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚያመላክት ከመሆኑ ባሻገር በቀጣይ ጊዜያት ዘርፉ በምን መልኩ መመራት እንዳለበት ማሳየት የሚያስችል ነው›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

የዘርፉን የአምስት ዓመታት የውጭ ገበያ መረጃዎች ወሰደን ምን ያህሉ ማዕድናት ላይ ነው እሴት ተጨምሮባቸው የተላኩት? ምን ያህሉስ በጥሬው ተላከ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ አብዛኛው የከበረና የጌጣጌጥ ማዕድን ወደ ውጭ የተላከው ምንም እሴት ሳይጨመርበት ጥሬውን ነው የሚል ይሆናል ብለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን 95 በመቶ ያህሉ በጥሬው (ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው) መላኩን ጠቅሰው፣ ቀሪዎቹ አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ መቅረባቸውን መረጃዎችን ዋቢ አድርገው አመልክተዋል፡፡

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ አምስት በመቶ ያህሉም ቢሆኑ ገበያው በሚፈልገው ደረጃ ተሰርተው የሚላኩ አይደሉም፡፡ እሴት መጨመር ስንል ለጌጣጌጥ በሚመች መልኩ ቅርጽ ሰጥቶ መላክ ማለት ነው። ነገር ግን ይህ እንዳይሆን የሚያደርጉ የክህሎት ክፍተት እና የመሠረተ ልማት ችግሮች ይታያሉ፡፡

ዘርፉ የሚፈለገው ብቁ የሆነ ክህሎት ይዞ መገኘት እና የመሠረተ ልማት (የከበሩ ማዕድናቱ ፕሮሰስ የሚደረግባቸው ማዕከላት ) መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ ባለመኖራቸው ምክንያት እሴት ጭመራ ላይ ብዙ መሥራት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት ሥራ በጣም ውስብስብ ቴክኖሎጂን የሚጠይቅ አይደለም፤ በትናንሽ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በቀላሉ መሥራት የሚቻልበት ነው›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ በዚህ ረገድ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉም ጠቁመዋል። የመጀመሪያው ሥራም የከበሩ ማዕድናቱ እሴት የሚጨመርባቸው (ፕሮሰስ የሚደረግባቸው) ማዕከላትን ማስፋፋት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁለተኛው ደግሞ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እና ፖሊሲ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡

የሕጉ ማዕቀፉ መላላት ማዕድናቱ እሴት ሳይጨመርባቸው በስፋት ወደ ውጭ እንዲላኩ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ችግሩ ማዕድናት እሳት ሳይጨመርባቸው ብቻም ሳይሆን በሕገ ወጥ መንገድም ጭምር ከሀገር እንዲወጡ ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሰለሞን እንዳብራሩት፤ ሰዎች እሴት ጨመረው ወደ መላክ እንዲመጡ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ወደ እሴት ጭመራ እንዲመጡ የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችና አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ስትራቴጂውም እነዚህን ጉዳዮች ይመልሳል። ከአምስት ዓመት በኋላ ቢያንስ 60 በመቶ ያህል የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት በጥሬው፤ 40 በመቶ ያህሉ ግን እሴት ተጨምሮባቸው እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡

አሁን ከዚህ ዘርፍ እየተገኘ ያለው ገቢ በዓመት ከ10 እና 12 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ኃላፊው ጠቁመው፡፡ በስትራቴጂው በመመራት ይህን እአአ በ2029 ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ሲሆን በዘርፉ ለበርካታ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጠር አስታውቀው፣ በዚህም ብዙ ያልተነኩ ማዕድናት እንዲዳሰሱና ወደ አሠራሩ እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናል ሲሉ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በጥሬው ወደ ውጭ የተላኩት 125ሺ ኪሎ ግራም የሚደርሱ የጌጣጌጥ ማዕድናት ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከአምስት ዓመት በኋላ ይህን አሃዝ ወደ 250 ሺ ኪሎ ግራም ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአንድ ጊዜ መቶ በመቶ እሴት ጭመራ ላይ እንግባ ብንል አይሆንም ሲሉም አመልክተው፣ ወደዚህ ቀስ በቀስ እንደርሳለን›› በሚል በእሴት ጭምራ ላይ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አቶ ሰለሞን አመላክተዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You