ዘላለማዊ ኃሠሣ

ጥንታዊቷን ከተማ ነዋሪዎቿ ‹‹የነቢያት ሀገራቸው›› በማለት ይጠሯታል፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ ከሚኖሩት በርካታ ጠቢባን መካከል አንዱ ፈላስፋ በየጊዜው ከጥንታዊቷ ከተማ በፀሐይ መውጫ በኩል ወደሚገኘው ከፍተኛ ተራራ በመሄድ አንዲት ገነታዊ አፀድ ውስጥ ተቀምጦ በፀጥታ የማሰላሰል ልማድ አለው፡፡ አንድ ማለዳም እንደ ልማዱ ከአውራ ዶሮ ቀድሞ ነቅቶ ወደዚህች ስፍራ አመራ፡፡ እንደ ወትሮው በዚያች ፀጥተኛ ገነታዊ አፀድ ውስጥ ግማሽ ቀን ያህል በተመስጥኦ ሲያሰላስል ከቆየ በኋላ ወደ ከተማ ለመመለስ ተነሳ፡፡ በመንገዱ ላይ ሳለ ፊቱ ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አዲስ አይነት የደስታ ስዕል ደምቆ ይታይ ነበር፡፡ የደም ስሮቹም ፊደላት ሆነው የውስጡን ሐሴት ገፁ ላይ አስነበቡ፡፡

ከረጅም ዓመታት የማሰላሰል ጉዞ በኋላ አምላክ ወይም ፈጣሪ ስለሚባለው ኃይል መኖር አለመኖር ጉዳይ አንድ እውነት ላይ መድረስ በመቻሉ ውስጡ በነበልባላዊ ፍስሃ ተሞቶ ይንቀለቀል ጀመር፡፡ ፋላስፋው በመጨረሻ ያረጋጠው እውነት የሚከተለው ነበር፡፡ ‹‹አምላክ ወይም ፈጣሪ የሚባል ኃይል የለም!››

የከተማዋን አማካኝ አልፎ በምዕራብ በኩል ወደምትገኘውና ተወልዶ ወደአደገባት መንደር ሲገባ ግን የአስር ዓመታት ሚስቱ ማለዳ ዶሮ ሲጮህ ሞታ በመንደሩ ሰዎች ፍታትና ፀሎት ግብዓተ-መሬቷ ከተፈፀመ ሰዓታት አልፈው ነበር፡፡ ፈላስፋው የሚስቱን እረፍት እንደተረዳ ለመሞቷ ሳይሆን በውትፍትፍ ፀሎትና ፍታት ለመቀበሯ ህዋሳቱ ሁሉ ሟሙተው ወደ ፈሳሽነት የተቀየሩ እስኪመስል ድረስ ብዙ እንባ አፈሰሰ፡፡

ጥቂት ቆይቶ ግን ህሊናውን መግዛት እንደቻለ ዶማ፣ አካፋ፣ ክብሪት እና ነዳጅ ይዞ ወደ ሚስቱ መቃብር ገሰገሰ፡፡ የሚስቱን አስከሬን ከትኩስ መቃብር ስር ፈልፍሎ አውጥቶ በክብር ለማቃጠል ሲሄድ ከረጅም ዓመታት በኋላ በጠንካራ የማሰላሰል ኃይል ያረጋገጠውን አንድ ታላቅ እውነት በህይወቱ ስለመግለጥና በገሃድ ስለመኖር እያሰበ ልቡ በታላቅ ተዓብዮ ተሞልታ ነበር፡፡

ከሰዓታት የእግር ጉዞ በኋላ የሚስቱ መቃብር ላይ ደረሰ፡፡ መቃብሯን ሲመለከት ግን በርካታ ዓመታት በፈጀ የሃሳብ ምርምር ካረጋገጠው ታላቅ እውነት በላይ ‹‹የአስር ዓመታት ፍቅሬ›› የሚላት የሚስቱ ሞት ገዝፎ ታየው፡፡ መሞቷን፣ ጥቁር አፈር መከናነቧን፣ አንገቷ ተሰብሮ የድንጋይ ክምር መሸከሟን አምኖ መቀበል ቸግሮት ተወርውሮ መቃብሯ ላይ በግንባሩ ተደፋ፡፡ አናት የሚበሳ የፀሐይ ጨረር ብቻ ገኖ የሙታን መንደር በፀጥታ ተውጦ ነበር፡፡ ፈላስፋው ግን የሚስቱ መቃብር ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ድምፁ የአካባቢውን ፀጥታ እስኪገስስ ድረስ ይንሰቀሰቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥልቅ ሃዘን ውስጥ ገብቶ ሲሰቃይ ከህሊናው ርቆ ግማሽ ሰዓት ያህል አሳለፈ፡፡ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ወደ ህሊናው ተመልሶ ካጎነበሰበት ቀና ሲል ግን ዙሪያ ገባውን ለማየት ሞክሮ አቃተው፡፡ አይኑ እስከ ሰማይ ጥግ ድረስ ማየት ቢፈልግም አፅናፈ-ዓለሙ በጭጋግ ተጋርዷል፡፡ ለወትሮው በቀን በብርሃን ያየው የነበረው ሰማይ በዙሪያው ካሉት ተራሮች ጋር የሚሳሳምበት አድማስ አሁን በጥቁር መጋረጃ ተሸፍኗል፡፡ ምድር በዕኩለ ቀን በድቅድቅ ጨለማ ተወርራለች፡፡

ልቡ በፍርሃት ቀለጠች፡፡ መንፈሱ ተሰበሰበ። ሀሞቱ ፈስሶ ጥንካሬውን ተሰለበ፡፡ ህሊናው የለም ብሎ የካደው አምላክ የተባለው ኃይል በእሱ በደል ምክንያት በምድር እና በፍጥረቷ ላይ ምፅዓት የላከ መሰለው፡፡ በልቡም ከፍርሃቱ ጋር እየታገለ አብዝቶ ምህረት ይለማመን ጀመር። ‹‹አባት ሆይ ይቅር በለኝ! እኔን የክህደት አለቃ ባሪያህን ማረኝ! በእኩለ ቀን አፅናፈ-ዓለሙን በጨለማ ሠራዊት ከበህ፣ የፀሐይን ብርሃን ጋርደህ ህልው መሆንህን አስረድተኸኛልና ከእንግዲህ ዳግም አልስትም፡፡ ማረኝ! ይቅር በለኝ!›› እያለ በእንባው ጭምር ምህረት ጠየቀ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ ግን ምድር በትንሽ ትንሹ መንጋት ጀመረች፡፡ ቀድመው በአየሩ ላይ ደመናዎች ሲተራመሱ ታዩ፡፡ የዛፍ ቅርንጫፎችም በንፋስ ባህር ላይ በቅጠሎቻቸው እየቀዘፉ ሲዋኙ ተገለጡ፡፡ የፀሐይ አይኖች ተከፈቱ፡፡ ፈለከ-ዓለሙ በብርሃን ፈገግታ ተሞላ፡፡ ሰማይም የተራሮችን ከናፍር ይስም ጀመር፡፡ የፈላስፋው መንፈስ በፍርሃትና ድንጋጤ ቢታወክም አምላክ ህልው መሆኑን በገሃድ ስለገለጠለት ልቡ በምስጋና ረካች፡፡ ድንጋጤው ሲያልፍለት ግን ራሱን በረጅም ዓመታት ኃሠሣ አምላኩን ፈልጎ ማግኘት የቻለ የሃሳብ ተጓዥ አድርጎ ቆጠረ፡፡

አመሻሽ ላይ ወደ ከተማዋ ሲመለስ በልቡ ለፈጣሪው ቀሪ እድሜውን በሙሉ ተዓምራቱን ሲያስረዳ ፣ አምላክነቱን ለሰው ልጆች ሁሉ ሲመሰክር እንደሚኖር ቃል እየገባ ነበር፡፡ ከተማዋን አልፎ ወደ ሰፈሩ መናገሻ እንደዘለቀ ግን አንድ የሕፃናት እና የወጣቶች ትምህርት ቤት በር ላይ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አንድ ኮከብ ቆጣሪ ከበው በጥያቄ ሲያጣድፉት ይመለከታል፡፡ ፈላስፋው ሁሉንም ሰዎች አልፎ ወደ መሃል ገባ። የኮከብ ቆጣሪውን ጠቢብነት ጠንቅቆ ያውቅ ነበርና ከከበቡት ሰዎች መካከል ነጥሎ ለብቻው ይዞት ሄደ፡፡ አንድ ሰወር ያለ ቦታ ሲደርሱም የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበለት፡፡

‹‹በዛሬው እለት ፀሐይ በእኩለ ቀን የጠፋችበትና ጨለማ በህልቁ ላይ የሰፈረበት ምክንያት ምንድን ነው?››

ኮከብ ቆጣሪውም የፈላስፋውን ትከሻ ጨበጥ አድርጎ ‹‹እነሆ ከዘመናት ቆይታ በኋላ በዛሬው እለት የፀሐይ ግርዶሽ በምድራችን ላይ ሆነ›› ሲል መለሰለት፡፡

‹‹የፀሐይ ግርዶሽ፣ የጨረቃ ግርዶሽ፣ ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀንና ሌሊት፣ ክረምትና በጋ፣ የብስና ባህር፣ ጫካና ምድረ-በዳ፣ ሸለቆና ተራራ፣ ሰው፣ እንስሳትና እፅዋት፣ ቁርና ሀሩር፣ ጀንበርና ጥላ፣ ዝናምና መብረቅ፣ ጎርፍ እና ማዕበል፣ እሳትና ውሃ፣ ሰማይ እና ምድር… ይህ ሁሉ ምንድን ነው?›› ፈላስፋው የኮከብ ቆጣሪው እጅ ይሁን የራሱ ሃሳብ ባይገባውም ትከሻውን አንዳች ነገር እንደ ወፍጮ ድንጋይ ተጭኖ እየከበደው ባዶ ቤቱ ውስጥ ገብቶ ያልተሟላ እንቅልፍ ተኛ፡፡

በማግስቱ ግን እንደልማዱ ማለዳ ከአውራ ዶሮ ቀድሞ ነቅቶ በጥንታዊቷ ከተማ በምሥራቅ በኩል ወደሚገኘው ተራራማ ቦታ አመራ፡፡ እዚያች ገነታዊ አፀድ ውስጥ ተቀምጦም በአርምሞ ያሰላስል ጀመር፡፡ ‹‹አምላክ የሚባለው ኃይል አለ ወይስ የለም?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፡፡

እዩኤል ወርቁ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You