የወጣቱ በጎ ተግባር

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰዎች መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ተግባር ነው፡፡ ቀስቃሽ ሳያስፈልጋቸው፣ ማንም ሳያስገድዳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት የተጎዱትን በማገዝ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ ለወገን የሚደርሱ ናቸው፡፡ በጎ ፈቃደኞች በሚሰጡት ነፃ አገልግሎት ከህሊና እርካታ በስተቀር የተለየ ጥቅም አያገኙም፡፡ ለበጎ ፈቃድ ተግባር የሚያውሉት ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን ጭምር ነው፡፡ ሌሎችም እንዲተባበሩና እንዲሳተፉ በማድረግም ይንቀሳቀሳሉ፡፡

በጎ ፈቃደኞች በዚህ መልኩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል ማህበረሰቡን ያግዛሉ፡፡ ይረዳሉ፡፡ በጎ ፈቃደኞች እየሰጡ ያለው የነፃ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር ደረጃም ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በበጎ ፈቃድ በሚሰጠው የነፃ አገልግሎት የሚሳተፉት ያለገደብ ማንኛውም ሰው ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ግን የወጣቶች ሚና ጎልቶ ይታያል፡፡ ወጣቶች ተባብረው በሚሰጡት የበጎ አገልግሎት ተግባር አብሮነታቸውን፣ አንድነታቸውን፣ መተሳሰባቸውንና ፍቅራቸውንም በአጠቃላይ ማህበራዊ ትስስራቸውንም ያጠናክሩ በታል፡፡

በጎነት የሚታይ ፍሬ ነው። በተለያየ መልኩም ይገለጻል፡፡ ለግለሰብና ለሀገር የሚተርፍ ከማሰብ በዘለለ፤ አብዝቶ ከመልካም ሥራዎች ጎን መሰለፍን፣ ሌሎችን ማገዝ ላይ ማተኮርን ከሰው ምላሸ ሳይጠብቁ ከራስ በላይ ለሌሎች ማድረግን የሚጠይቅ የንፁህ ልብ ክዋኔ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡ ይህን ተግባር ብዙዎችም እየፈፀሙትና እየኖሩትም ነው፡፡

እንዲህ ባለው መልካም ተግባር ውስጥ ከተሰለፉ ወጣቶች መካከል ወጣት አውታሩ ተስፋዬ አንዱ ነው። ተወልዶ ያደገው በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ ነው። እንዲህ ያለው በጎ ተግባር ውስጥ የገባበትን አጋጣሚ እንዳጫወተን፤ በትውልድ አካበቢው የትምህርት መማሪያ ግብዓት አሟልተው ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ በቁጥር አምስት ለሚሆኑ ልጆች እስክርቢቶና ደብተር በራሱ ወጪ ገዝቶ በመስጠት ነበር፡፡ ባደረገው ጥቂት የበጎ ተግባር በሕፃናቱ ገጽታ ላይ ያየው ደስታና የወላጆቻቸው የእፎይታ ስሜት የበጎ ሥራ ተግባሩን እንዲገፋበት እንዳደረገው ይናገራል፡፡

ወጣት አውታሩ፤ ከራሱ አልባሳት፣ ከእለት ምግቡ ቀንሶ ለሌላቸው ማካፈል የእለት ተግባሩና ደስታም የሚሰጠው ሆነ እርሱ እንደሚለው፤ የበጎ ሥራ ሁሉ ከእለት ተእለት ሕይወቱ በእጅጉ ተቆራኘ፡፡ የጀመረውን የበጎ ሥራ በስፋት ለመከናወን ይረዳው ዘንድም ‹‹ሄኖን›› የሚል ስያሜ ያለው የበጎ አድራጎት ማህበር ስድስት አብሮ አደግ ጓደኞቹን በማስተባበር አቋቋመ፡፡

ማህበሩን ማቋቋም ያስፈለገው፤ ድጋፉን በማስፋት በኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቻለው አቅም ሁሉ ለመደገፍ ነው፡፡ ጊዜንም በዋዛ ፈዛዛ ከማሳለፍ ለዜጎችና ለሀገር የሚጠቅም ቁም ነገር ማድረግን በመምረጡ ጭምርም ነው፡፡ በተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች ሻይ፣ ቡና በማለት፣ አላስፈላጊ ቦታ በመዋልና ሱቅ ዳር ተቀምጠው ለሚውሉ ለአንዳንዶችም አርአያ ለመሆንም አስቦ ነው፡፡

‹‹ሄኖን›› የበጎ አድራጎት ማህበር ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያን፣ ልጆቻቸውን በሞት ያጡና ልጆች ያላፈሩ ብቸኛ የሆኑትን ጭምር የሚያስፈልጋቸውን ያሟላል፡፡ ማህበሩ በብዙ መልኩ ለብዙዎች የሚተርፍ የበጎነት ቤት ሆኗል ማለት ይቻላል።

ወጣቱ አውታሩ እንደገለጸው፤ የማህበሩ እገዛ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ለአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ይገነባል፡፡ የጤና ችግር አጋጥሟቸው ከፍለው መታከም ላልቻሉ ወገኖች ለመታከሚያ የሚውል ገንዘብ በማሰባሰብ ይረዳል፡፡ በደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላና የፅዳት ዘመቻ ላይ ይሳተፋል፡፡ ማህበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወናቸው የተለያዩ ተግባራትም 21 መኖሪያ ቤቶችን በከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ 21 ሰዎች መኖሪያ ቤት ገንብቶ ሰጥቷቸዋል፡፡ ለሕክምና በሚያሰባስበው ገንዘብም በሀገር ውስጥ በውጭ ብዙዎች ሕክምና እንዲያገኙም አድርጓል፡፡ በ13 ዙር ባካሄደው የደም ልገሳ መርሀ ግብርም ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ ዩኒት ደም በማሰባሰብ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ ችሏል።

“የወጣበት ማህበረሰብ ለትምህርት የሚሰ ጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው” የሚለው አውታሩ፤ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት የትምህርት መረጃ ቁሳቁስ በቤተሰቦቻቸው ተሟልቶ ትምህርት መከታተል እንደማይችሉ ይገልጻል። መማር እየፈለጉ አስፈላጊ የትምህርት ግብዓት ባለማግኘት ከትምህርት ገበታ የሚቀሩ ሕፃናት ሁኔታ አሳዛኝ እንደሆነም ይናገራል። ማህበሩ እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች ለመሙላት በሚችለው ሁሉ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው ያስረዳው፡፡

ወጣት አውታሩ፤ እንዲህ እያከናወነ ያለው የበጎ አድራጎት ሥራ የተለያዩ ትችቶች እንደ ገጠመው ይገልጻል፡፡ አንዳንዶች እንደ ብክነት እንደሚያዩት፣ አንዳንዶች ደግሞ ገንዘብ ማግኛ ዘዴ አድርገው እንደሚያዩት፣ የሚያሾፉበትም እንደነበሩና በተሳሳተ ግንዛቤም እንደተረዱት ይናገራል፡፡ ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶች ሌሎችን ለበጎ ተግባር ለማነሳሳት እንቅፋት ፈጥሮበት እንደነበርም ተናግሯል፡፡ ሆኖም ግን የተሰነዘሩበት አስተያየቶች ሁሉ ከበጎ አገልግሎት ተግባሩ ወደኋላ እንዳላስቀሩትና ሁሉንም ተቋቁሞ ማህበሩን በማጠናከር ላይ ትኩረት እንዳደረገ ያስረዳል፡፡

ማህበሩ ‹‹ዓሳ ከመስጠት ይልቅ ማጥመጃውን መስጠት›› የሚለውን እንደ መርህ አድርጎ የሥራ ዕድል በመፍጠር ላይም እየሠራ መሆኑን የሚናገረው አውታሩ፤ ‹‹ለሰዎች ዓሳ ብቻ የምንሰጥ ከሆነ ዓሳው ሲያልቅ ተመልሰው የሰው እጅ ተመልካች ይሆናሉ፤ ማጥመጃውን ካገኙ ግን ተመልሰው ርዳታ አይፈልጉም›› ይላል፡፡ እስካሁንም በማህበሩ ለ46 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመልክቷል፡፡

ወጣት አውታሩ፤ አሁን ላይ ከሚያስተውለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አንጻር የሚደ ረገው ድጋፍ በቂ ነው ብሎ አያምንም። በእርሱ አቅም ብቻ መሆን እንደሌለበትም ይገልጻል፡፡ የግለሰቦች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልግም ተናግሯል፡፡

ሌሎችን ላለማስቸገርና በራስ አቅም የበጎ ሥራ ተግባሩን ለማከናወን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን እንደሚሠራ የሚናገረው ወጣት አውታሩ፤ ለአብነት የእግር ኳስ ውድድር፣ የጥበብ ምሽቶችን መሰል ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ማህበሩ የገንዘብ አቅም እየፈጠረ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

ማህበሩ ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው የሚናገረው ወጣት አውታሩ፤ ሕጋዊ መሆኑ ድጋፍ በሚያደርጉ ሰዎች ተአማኒነትን እንደፈጠረለትም ይገልጻል፡፡ እርሱ እንዳለው የሚሰራው በጎ ተግባር በክልሉና በዞኑ ይታወቃል፡፡ በተለያየ ጊዜም ላከናወነው ሥራ ከክልሉና ከዞኑ ከ19 በላይ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል። እንዲህ ያለው ማበረታቻ የበለጠ እንዲሠራ አቅም ፈጥሮለታል። የሚቀረው የቤት ሥራም እንዳ ለበት አስገንዝቦታል። ‹‹በጎነት ሽልማት የሚያሻው አይደለም፡፡ ለበጎነት የሚሰጥ ሽልማት ደግሞ ብዙ የቤት ሥራ የመስጠት ያህል ነው›› ሲልም ይገልጻል፡፡ ‹‹ከእናንተ ብዙ እንጠብቃለን ስንባል የሚሰማኝ አደራ እንደተሰጠኝ ነው›› ይላል፡፡

በጎ ማድረግን በተመለከተም ወጣት አውታሩ እንደገለጸው፤ ህብረተሰቡ ያለው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው። በማህበሩ አማካኝነት ከተማ ላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከህብረተሰቡ የሚያገኘው ምላሽ በጎ በመሆኑ ይሄ ሰው ባለው አቅም ለተቸገሩ ሰዎች ለመርዳት ያለውን ፍላጎት ያሳያል፡፡ እንዲህ ያለው ለበጎ ሥራ መነሳሳት ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ሄኖን የበጎ አድራጎት ማህበርን እርሱ ቢመሰርተውም፤ የብዙ ቅንና በጎ አድራጊ ሰዎች ተሳትፎ ያለበት መሆኑን ያስረዳል፡፡

ማህበሩ በተለይም በበዓላት ወቅት ብዙ ሰዎችን ለማገዝ ጥረት እንደሚያደርግም ይገል ጻል፡፡ እርሱ እንዳለው፤ ሰዎች ለበዓል መዋያ የሚሆን ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአቅም ማነስ ማሟላት ያልቻሉ ሰዎች ደግሞ ሌሎችን በማየት ማሳለፍ የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ማህበሩ በዚህ ወቅት ለበዓል መዋያ የሚሆን ለማሰባሰብ ይንቀሳቀሳል፡፡ ወጣት አውታሩ፤ በተለይም በትውልድ አካባቢው በድምቀት የሚከበረው የብሔረሰቡ ዘመን መለወጫ (የመሰላ በዓል) ሲደርስ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ደጋጎችን በማስተባበር በቁጥር ከ50 እስከ 100 የሚሆኑ ሰዎችን ወጪ ሙሉ በሙሉ በመሸፈን በዓልን በሙሉ ደስታ እንዲያሳልፉ ሲያደርግ እንደቆየ ይናገራል።

ለ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓልም ከ50 በላይ አቅመ ደካማ ወገኖችን በዓልን በባዶ ቤት እንዳያሳልፉ ማዕድ ለማጋራት ከሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ግለሰቦች በዚህ የበዓል ስጦታ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሆነም ተናግሯል፡፡ በዚህ አጋጣሚም በማዕድ ማጋራቱ ላይ ሰዎች በአቅማቸው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሄኖን በጎ አድራጎት ማህበር ከሚያደርገው በጎ ተግባር ጎን ለጎን ለወጣቶች የሥራ ዕድል በፍጠር ላይም ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ውጥን እንዳለው የሚናገረው ወጣት አውታሩ፤ ወጣቶች ካሉበት አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ወጥተው አምራችና ብቁ ሆነው፤ ለራሳቸው ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው የሚጠቅሙ ሆነው ማየት ፍላጎቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በትውልድ አካባቢው በተለያየ የትምህርት ደረጃ የተማሩ ወጣቶች መኖራቸውንና ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብቻ ሥራ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ይገልፃል፡፡ ማህበሩ ከመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት ለወጣቶች የመሥሪያ ቦታ፣ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት የሥራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመልክቷል፡፡

የበጎነት ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሀገራቸውን ለማቅናት መንገድ መሆን እንዳለባቸው የሚናገ ረው ወጣት አውታሩ፤ የወጣትነት ትኩስ ጉልበት ለበጎነት ቢውል እንደ ሀገር ትርጉሙ ብዙ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ወጣቶች የተሻለች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

‹‹ለመልካም ሥራ ረፍዶ አያውቅም፡፡ አንድ ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ በጎ ነገር ማድረግ አይችልም፤ መልካም ነገር ማድረግ ከመልካም አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። በጎነትን ዛሬ መጀመር ይቻላል። ካለን ነገር ለማካፈል የግድ ሀብታም መሆን ወይም ሚሊየነር መሆን አያስፈልገንም፤ ማንኛውም ሰው በጎ ነገር ማድረግ ይችላል። ስለዚህ የወደቁትን ለማንሳትና ጠያቂና አጋዥ የሌላቸውን ሰዎች አለንላችሁ ለማለት ሁሉም ሰው በተለይ ወጣቱ እጁን መዘርጋት አለበት›› ሲልም መልእክት አስተላልፏል፡፡

በመጨረሻም ሄኖን የበጎ አድራጎት ማህበር እስከ አሁን በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ ከማህበሩ ጋር አብረው ለነበሩ፣ ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር በስደት ላይ ሆነው ለወገኖቻቸው ድጋፍ በማድረግ ከማህበሩ ጎን ለቆሙ በጎ ፈቃደኞች በሙሉ ምሥጋና አቅርቧል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You